ባለፈው ግዜ መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም የሳንሱርን ትንሳኤ ሊያመጣው እንደሆነ ፍንጭ አግኝተናል ብለን አንዳንድ ጩኸቶችን ጮኸን ነበር። በጩኸታችን ማግስት የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በመላው አለም ተከበረ። ከመላው አለም አክባሪዎች ውስጥ “ወጉ ለምን ይቀራል” ብላ ኢትዮጵያም አንዷ ሆና ነበር።

በክብረ በዓሉ ላይ አቶ ሽመልስ ከማል ካልታሰሩ ጋዜጠኞች ጋር አንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው ነበር አሉ። ታድያ አንድ ጥያቄ ተወነጨፈባቸው። “መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱርን ድጋሚ እያመጣው ነው፤ ይኸው “ብርሃንና ሰላም የምታሳትሙትን አይቼ ቀልቤ ካልወደደው እንቢ የማለት መብት አለኝ” የሚል ውል እያስፈረመን ይገኛል።” ብለው ነግረዋቸው ነበር። ታድያ አቶ ሽመልስ ምን አሉ?

“ይሄ የብርሃንና ሰላም ድርጅት ያወጣው ህገ ደንብ ነው እኛ በዚህ ላይ የለንበትም!” ብለው እርፍ! እኛስ ምን እንላቸዋለን…

አቶ ሽመልስ በመጀመሪያ እንኩ ሰላምታ፤ የት ጠፍተው ከረሙ…? እኔ የምልዎ… ከዚህ በፊትም እንዲህ የማይሆን ንግግር ሲናገሩ የሰሙ ወገኖች እና ወገኞች “አቶ ሼም የለሽ” ብለው ስም አውጥተውልዎ ነበር። ስሙ እንደተጠበቀ ይቆይ ካሉ ጥሩ፤ አለበለዛ ግን ይሄ ትልቅ የሆነ ህገ መንግስትን የመናድ ተግባር ነው። ታድያ እንዴት አፍዎን ሞልተው በዚህ ጉዳይ እኛ የለንበትም ይላሉ። በህገመንግሰቱ ጉዳይ ከሌላችሁበት በምን ጉዳይ ላይ ነው የምትኖሩት? የምሬን ነው የምልዎ ተሸወዱ! እኔ እርስዎን ብሆን ምን እንደማደርግ ያውቃሉ…? እርግጠኛ ነኝ አያውቁም። ስለዚህ እራሴው እነግርዎታለሁ።

መጀመሪያ ብርሃንና ሰላም አዘጋጀ ስለተባለው ውል ከጋዜጠኞቹ ስሰማ ምንም እንኳ ቀድሜ የሰማሁት ቢሆንም፤ አውቄ ድንግጥ እላለሁ። ድንግጥ ቢሉዎት ደግሞ ዝም ብሎ ድንግጥ ብቻ አይደለም። ክው! ከዛ ንግግሬን እቀጥላለሁ “ይሄ ስህተት ነው! ድርጅቱ ህገመንግስቱን እየናደ ስለሆነ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰንበት ጉዳዩን ወደ ህግ እንወስደዋለን!” እላለሁ።

እውነቴን ነው የምልዎ አቶ ሽመልስ፤ እንኳንስ ሌላ ቀርቶ እነ እስክንድር ነጋን እና ስንቱን ምስኪን ሰው… “ህገ መንግስቱን ሊንዱ ሲሉ  በህብረተሰቡ ትብብር ተያዙ!” ብለውን የለ እንዴ!? (በምን አቅማቸው ሊንዱት እንደሞከሩ ባይታወቅም)  ታድያ ስለ ብርሃንና ሰላም ላይ ይህንን የመሰለ ጥቆማ ሲደርስዎ ከዚህ የበለጠ የህብረተሰብ ትብብር ከየት ይመጣል!? አረ “ሼ” ይኑር “ሼም” …ነውር እንወቅ… ስማችንንም እናድስ! እስከ መቼ ሼም የለሽ እንባላለን!?

ምናልባት ህገ መንግስቱን ረስተውት ከሆነ እንደሚከትለው አስታውሶታለሁ፤

“ሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ላይ እንዲህ ይላል፤ “ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ፤ ልማዳዊ አሰራር፤ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገመንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም።” ይላል። ይህ ደግሞ ብርሃንና ሰላምንም ጨምሮ ነው። አረ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይጨምራል። ሄደው ሄደው ሄደው አንቀፅ 29 ላይ ሲደርሱ ደግሞ ስለ ፕሬስ ነፃነት ያወራ እና “ሀ” ላይ ገና በመጀመሪያው ማለት ነው “የቅድመ ምርመራ በማነኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን…” ይደነግጋል።

ታድያ ብርሃንና ሰላም “የሚታተመውን ፅሁፍ አይቼ  ውቃቤዬ ካልወደደው አላትምም” የሚለው በምን ህግ ነው? ይህ ህገ መንግስቱን መናድ አይደለምን?

አቶ ሽመልስ ከሰሙኝም  ካልሰሙኝም እንኩ ሰላምታ… ! (በምን ልምታህ እንዳይሉኝ ብቻ!) እንኩ ወቀሳም! ወቀሳው ግን ከመብዛቱ የተነሳ ለልጅ ልጅ ሁሉ የሚያወርሱት ሆኖሎታል አሉ! (አሉ ነው)

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

2 responses »

  1. […] አቶ ሽመልስ ከሰሙኝም  ካልሰሙኝም እንኩ ሰላምታ… ! (በምን ልምታህ እንዳይሉኝ ብቻ!) እንኩ ወቀሳም! ወቀሳው ግን ከመብዛቱ የተነሳ ለልጅ ልጅ ሁሉ የሚያወርሱት ሆኖሎታል አሉ! (አሉ ነው) Posted by abetokichaw on May 7, 2012 […]

  2. በለው! says:

    “አቶ ሽመልስ ከማል ካልታሰሩ ጋዜጠኞች ጋር አንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው ነበር ከዚህ በፊትም እንዲህ የማይሆን ንግግር ሲናገሩ የሰሙ ወገኖች እና ወገኞች “አቶ ሼም የለሽ” ብለው ስም አውጥተውልዎ ነበር …
    ይህንን ሥም ባይሰጧቸው ይገረም ነበር ፤ የስብሰባው ውይይት የተጀመረው “ምላስ በማውጣት” ወይስ ሐሳብ መማዋጣት ምን የሞቱ ጋዜጠኛች ነበሩ? ? በኢህአዴግም ይሁን በሌላ የሥልጠና ክበብ ምን አይነት ትምህርት እንዳላቸው አልታወቀም የአቶ መልስ አፍቃሪ ካድሬዎች ከማስፎገር በቀር ሥራ የላቸውም? በአሸባሪው አዋጅ ላይ የሰጡት አስተያየት “ከማናቸውም አሸባሪ ድርጅት ወይም አባል ጋር የተገናኘ፣ አብሮ የተቀመጠ ቡና ሻይ ያለ ሁሉ ወንጀለኛ ነው ሲሉ የወያኔ አሸባሪው አዋጅ አንቅፅ 5-ድጋፍ ስለመስጠት (ሀ-ረ) አንቀጽ 6-ድርጊትን ማበረታታት (፩-፪) አንቀፅ 7- ስለመሳተፍ (፩-፪) ሻይ አትጠጡ የሻይ ቤቱ ባለቤት እና አስተናጋጅ ወንጀለኛ ይሆናሉ የሚል የትም ሀገር የትም ቦታ አልተጸፈም።
    እንኩ ወቀሳም! ወቀሳው ግን ከመብዛቱ የተነሳ ለልጅ ልጅ ሁሉ የሚያወርሱት ሆኖሎታል አሉ!
    “ይሄ የብርሃንና ሰላም ድርጅት ያወጣው ህገ ደንብ ነው እኛ በዚህ ላይ የለንበትም!”
    የሕገ መንግስትዎ አንቀፅ ፱ እንደተጠበቀ ሆኖ ..አንቀፅ ፳፱ (፩-፬) በጣም ያንፏችራል የተፃፈው አድናቂ እና ደጋፊ የምዕራብ ሀገሮችን ሆድ የሚያባባ ይመስላል። አንቀፅ ፳፱ (፭) “ለብርሃንና ሰላም” ሳይሆን “ለጭለማ እና ለነውጥ”
    “ገዢው መንግሰት በሚመቸውና በፈለገው ሁኔታ የሌሎችን ሐሳብ እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው በገንዘቡ ለሚአስተዳድራቸው ወይም በቁጥጥሩ ሥር ላሉ መገናኛ ብዙሃን መመሪያን ይሰጣል”።ይልና አንቀፅ ፳፱ (፮) አርቃቂውም፣ ፀሐፊውም፣ ሳንሱር የሚያደርገው፣ የሚወስነው መንግስት ይሆናል።ለወጣቶች፣የሰውን ክብርና መልካም ሥም ለመጠበቅ…
    ” ከላይ በሰጠናችሁ መብቶች ላይ ሕጋዊ ገደቦች ሊደነገጉ ይችላሉ”!ይቺ ናት ጨዋታ በለው!

Leave a comment