በ1998 ዓ.ም አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ፤ ለአንድ ስታስቲክሳዊ ስራ ወደ ወደ አርማጭሆ አካባቢ ሄጄ ነበር። በወሬ ደረጃ ስንሰማው የነበረ “አርበኞች ግንባር” በመባል የሚታወቅ የታጠቀ ቡድን እዚህ አካባቢ “በህይወት” መኖሩን ሰማሁ። ለስታስቲክሳዊ ስራው የገጠሩን መንደር መንገድ እንዲመሩን የተመደቡልን የመንግስት ታጣቂዎች ነበሩ። እኔ እና ሌሎች ከአዲሳባ ለስራ ወደ እዚህ የመጣን ልጆች ስለ አርበኞች ግንባር በደንብ ለማወቅ ጉጉት አድሮብናል። ነገር ግን የመንግስት ታጣቂን ስለ ተቃዋሚ ለዛውም ስለ ሸማቂ ሃይል መጠየቅ እየፈራን እየተባን በአካባቢው ስለሚኖሩ ሽፍቶች በመጠየቅ እናሟሙቅ ጀመር።

“እዚህ አካባቢ ሽፍታ አለ ይባላል እውነት ነው?”  አልነው አጃቢያችንን፤

“እንዴ ጋሼ ሽፍታማ ሃገሩ ነው!” አለን በኩራት። (በነገራችን ላይ አርማጭሆ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ክፍለ ሀገሮች ቢሄዱ በእድሜ የሚበልጥዎም ሰው እንኳ “ጋሼ” ብሎ በአክብሮት ነው የሚጠራዎት። እናውቃለን ባክህ… ካሉኝ “እኮ…” ብዬ ቀጥላለሁ!)
ጥያቄያችን ቀጥሏል።
“ሰዉ ምን ሆኖ ነው የሚሸፍተው…?” አልነው።
“ሰበቡማ ብዙ ነው ምሰሌ፤ በመንደር ግጭት የተጠቃ እንደሆነ፤ አኩርፎ ጥቃቱን ለመወጣት ይሸፍትና በዛው ሽፍታ ሆኖ የሚቀር አለ…” ልክ ይህንን ምላሽ እንደሰማሁ፤ መቼም ያን ጊዜ ቀልጣፋ ነበርኩ፤ ለማወቅ ወደፈለግነው ዋና ነጥብ ቀልጠፍ ብዬ ገባሁ፤

“በመንግስት ላይ አኩርፎ የሚሸፍትስ የለም?” ብዬ ጠየቅሁ…!

ይሄኔ መንገድ መሪያችን የመንግስት ታጣቂ ያነገታትን አሮጌ ክላሽ ከፍ ከፍ እያደረገ፤
“እሱማ ምን ይጠፋል!?” ብሎ በጥርጣሬ እያየን ዋናው ጨዋታችንን በአጭሩ ሊቀጨው ፈለገ። ስለ አርበኞች የማወቅ ጉጉት የሁላችንም ነበርና አንዱ ወዳጃችን፤

“አርበኞች የሸፈቱት በመንግስት ላይ አኩርፈው አይደል እንዴ!?” ብሎ ሌላ ጠቋሚ ጥያቄ አመጣ። በሆዳችን ጎ…በዝ ብለን ወዳጃቸንን አደነቅን!
ይሄን ጊዜ የገጠሩን መንገድ ሲመራን የነበረው የመንግስት ታጣቂ  ቆም አለና፤ ትክ ብሎ አየን፣ ከዛም በሆዱ “የመጣው ይምጣ!” ያለ በሚመስል መልኩ፤
“ጋሼ አትሳሳት አርበኛማ ሽፍታ አይደለም። አርበኛ የአላማ ሰው ነው!” ብሎ መንግድ መምራቱን ቀጠለ።

በእውነት በጣም ነበር የተደነኩት። በወቅቱ የሄድነው ለመንግስት ስራ ነበር። መንገድ የሚመራን የመንግስት ታጣቂ ነው። ይህ የመንግስት ታጣቂ ስለ ሸማቂው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር በአድናቆት ሲናገር መስማት በእውነቱ ያስገርማል። ግንባሩ እውነትም በህዝብ ልብ ውስጥ የገባ ስለመሆኑ ማስረጃ ነው።

ከዛ በኋላ በይፋ ድጋሚ ስለ አርበኞች ግንባር የሰማሁት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነበር። “ሀገር ጫታ ሆነ!” በሚል ርዕስ በ2001 ዓ.ም አካባቢ (ነው መሰለኝ) መንግስታችን ከዛ በፊት አንድም እንኳ፤ በዛ አካባቢ ስለነበረው እንቅስቃሴ ያልነገረን ለግንባሩ እውቅና ላለመስጠት ነበር ለካ!

“ሀገር ጫታ ሆነ” በሚለው እና ስለ አርበኞች ግንባር የሚዳስሰው የኢቲቪ ፕሮግራም  ስለ አርበኞች ግንባር ተጨማሪ ማወቅ ቻልን…! “ለካስ እነዚህ ሰዎች በዚህ ደረጃ መንግስታችንን አስጨንቀውታል!?” እኛኮ መንግስታችን ዝም ሲል ግንባሩን ከቁብም አልቆጠረውም ብለን ነበር። ለካስ የሆዱን በሆዱ ችሎ ነው ፀጥ ያለው…? ምስኪን መንግስታችን! ብለን አዘንን።

ከዛ በኋላ ለረጅም ጊዜ ስለዚህ ግንባር በቅጡ ሰምቼ አላውቅም ነበር። አሁን በቅርቡ ደግሞ ሌላ ወሬ ሰማሁ።

በዋልድባ ገደም ህልውና ላይ እየተገነባ ያለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ባለፉት ሰሞናት ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። ኢቲቪም ትንሽ “ፎገር ፎገር” አድርጎ ነገሩን አንደተረሳ አድርጎታል። የአካባቢው ህዝብ መነኮሳቱ እና ምዕመኑ ግን ዝም አላሉም ለፈጣሪም ለህዝቡም አቤት እያሉ ነበር። ቢሆንም ግን መንግስት አካባቢውን በጦር ከቦ ቁፋሮውን ተያይዞታል። እሰይ የኔ አንበሳ! ብለን አድንቀን ሳንጨርስ ታድያ ሌላ ነገር ሰማን፤ ምን…? አዲስ መስመር ላይ አለልዎት

አርበኞች ግንባር፤ “በአካባቢው የህዝቡን ተቃውሞ ችላ ብለው በቁፋሮ የተሰማሩ መሳሪያዎችን አወደሜያለሁ” የሚል መግለጫ አወጣ።
ከላይ እንዳልነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር። ልክ እንደ ኢህአዴግ ብሶት የወለደው፤   በኢህአዴግ አመራር ተማሮ ጫካ የገባ የታጠቀ ሃይል ነው።
ባለፈው ጊዜ ደጀ ሰላም የተሰኘ ድረ ገፅ በዋልድባ ገዳም መነኮሳት መታሰራቸውን እና ለተቃጠለው ዶዘር እና ለተሰነዘረው ጥቃት ሃላፊነቱን ትወስዳላችሁ። መባላቸውን ዘግቦልን ነበር። እስከ አሁንም መነኮሳቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አልሰማንም። ልብ አድርጉ ሸማቂዎች ላደረሱት ጉዳት ተጠያቂው ከዋሻ ወጥተው የማያውቁ መነኮሳት ተደርገዋል።

አሁን እንግዲህ አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ነው። ጥያቄው የኢህአዴግ አባላትን ደጋፊዎችን እና ተደጋፊዎችን ይመከታል። ማሳሰቢያ መልሱን በትግሉ ወቅት የተሳተፉ አንዲመልሱ ይበረታታል። ከድህነት ጋር የምትታገሉትን አላልኩም።

እኔ የምለው ኢህአዴግ በትግል ላይ እያለች የደርግ አድናቂ ነበረች ማለት ነው…? ከመቼው ገብተን ከመቼው እንደ ደርግ በሆነን! ብላ አብዝታ ታስብ ነበር ማለት ነው? የታጠቀ ሃይል ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ባለበት ጥቃት የአካባቢው ሰው እና የሀይማኖት አባቶችን ማሰር አግባብ ነው!?  ወይስ መነኮሳቱ በዋሻ ውስጥ ሲገኙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ታጋዮች መስዋቸው ነው!?

በመጨረሻም

እመክራለሁ

ጎበዝ ይሄ ነገር ብሶትን ማቀጣጠል በመባል ይታወቃል። ደርግም ጉድ የሆነው እንዲሁ ለታጋዮች ጥቃት በአፀፋው ህዝቡን ሲያንገላታ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይሄንን እናንተው በትግል ላይ ያሳለፋችሁት እንጂ፤ እኔ ከኑሮ ጋር የምታገለው ግለሰብ ልነግራችሁ አይገባም ነበር። ግን ተናግሪአለሁ ባለስልጣኖቻችን ሆይ የብሶት ማርገብገቢያ አትሁኑ!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

2 responses »

  1. በለው! says:

    “በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ክፍለ ሀገሮች ቢሄዱ በእድሜ የሚበልጥዎም ሰው እንኳ “ጋሼ” ብሎ በአክብሮት ነው የሚጠራዎት”
    *ነበራ ድሮ.. ሁሉ ድሮ ቀረ ይህ ያለፈው ሥርዓት ትቶብን ያለፈው የመከባበር ጎታች ባሕል !!

    “አርበኞች የሸፈቱት በመንግስት ላይ አኩርፈው አይደል እንዴ!?” “ጋሼ አትሳሳት አርበኛማ ሽፍታ አይደለም። አርበኛ የአላማ ሰው ነው!”
    **ለነገሩ ሻቢያም ህወአትም ሸፍተው ነበር አርበኝነትን የማያጠቃልለው ድልድይ በማፍረስ፣የገበሬ ጎተራ በመድፋት፤የማሳ እሸት በመዝረፍ፣ት/ቤት ፤የሕክምና ጣቢያ፤የህዘብ መገልገያ ተቋማትን በማፍረስ የተካነ ፤ሀገር በባዕድ ሀገር በጦር ስትወረር ወግኖ በሀገሩ ሉዓላዊነት መደፈር ላይ የተባበረ ተመሳጥሮ ሕዘቡን ያስፈጀ ንብረት ያወደመ የሲያድ ባሬ አገልጋይ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው።ለዚህም ነው በዚያን ዘመን ያልደፈሯቸውን ወይም ዘርፎ በማዘርፍ ያልተባበሯቸውን ዛሬ በተናጠል ከግል ንበረታቸው, ትዳራቸው, ከመሬታቸው እያባረሩ ዘራቸውን ከመበረዝ እስከማጥፋት የሚበቀሏቸው።
    “አርበኞች ግንባር፤ “በአካባቢው የህዝቡን ተቃውሞ ችላ ብለው በቁፋሮ የተሰማሩ መሳሪያዎችን አውድሜያለሁ” የሚል መግለጫ አወጣ። የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር። ልክ እንደ ኢህአዴግ ብሶት የወለደው፤ በኢህአዴግ አመራር ተማሮ ጫካ የገባ የታጠቀ ሃይል ነው።
    *** “የመረረው የስኳር ብዛት አያጣፍጠው!!” ስንት ካልጠፋ መሬትና ውሃ የታሪክ እና የሃይማኖት ቦታን ማረስ መንግስት በሐይማኖት ጣልቃ አይገባም ሲል በሩቅ ሆኖ ያፈርሰዋል ማለት ይሆን ? “ልዩነታችን ውበታችን ሲሉ” አማራን የምዕራብ ወልቃይት ዋልድባ ! ትግሬን የምስራቅ ወልቃይት ዋልድባ ለይቶ ማቧድን ይሆን ? ? አቤት ውበት ቀለጠ በለው!

    “የታጠቀ ሃይል ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ባለበት ጥቃት የአካባቢው ሰው እና የሀይማኖት አባቶችን ማሰር አግባብ ነው!?”
    “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ሻቢያ ባድሜን ወሰደች የአርብቶ አደር ማማ በቦንብ አቃጥለው ጠላት ደመሰስን አሉ”
    “መነኮሳቱ በዋሻ ውስጥ ሲገኙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ታጋዮች መስዋቸው ነው!?”
    ****”እባብ ያየ በልጥ በረየ” ፯ ቁጥር የለበሰ ኳስ ተጫዋች ባለበት ሁሉ የግንቦት ፯ ደጋፊ ናችሁ ተብሎ መወንጀል ተጀምሯል። አሁን ቡለዶዝር ካቃጠሉ ለምን ተደግፈውት መፅሐፍ አላነበቡም ብለው ይሆናል። ቡልዶዘርና ታንክ ? ?
    “እኔ የምለው ኢህአዴግ በትግል ላይ እያለች የደርግ አድናቂ ነበረች ማለት ነው…? ከመቼው ገብተን ከመቼው እንደ ደርግ በሆነን! ብላ አብዝታ ታስብ ነበር ማለት ነው?”
    *****አዎን !! ኢህአዴግ በመዋቅሩ ሁሉ ከትግል እስከ አሁን አመራሩ በሁሉም ዘርፍ የደርግ አባላቶችን ተማምኖ እንደሚኖር ዛሬም የደህንነቱን ሥራ ሁሉ እንደሚስሩ በጥሞና(በጥንቃቄ,በእርጋታ) ታነቡ ዘንድ ተጋበዛችሗል።
    አይጋ ፎርም ደራሲ ተክላይ ገብረእየሱስ (ከጦር ሀይሎች) ፯/ ፫/ ፪፼፲፪ ለአቶ ግርማ ሰይፉ የፓርላማ ተወካይ የተላከ ማስፈራሪያ…የፀሐፊው ማስታወሻ ቀጭን ትዕዛዝ ለፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች ከግርጌው ። ስላነበብኩት ተመስገን ደስአለኝ!!! “ዮናስ ፯/፱/፪፼፲፪ “የመለስ አምልኮን በጨረፍታ” ከክስ መዝገብ የተጨረፈውንም ያንብቡ!! በቸር ይግጠመን በለው!

  2. Tikidem says:

    እንደምነህ አቤ ፣ አንድ ጊዜ ሆነ ያሉትን ልንገርህ፣ ግን እንደ ወያኔ ውሸት አይደለም፣
    የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ በዓል ዕለት አንዱ ታዞ ይሆን ወይም ስራው ይሆን አልታወቀም በተለያዩ ባንዲራ የባዕሉን አካባቢ ያደምቃል፡፡ ሌላኛው በመንግሥት ሥራ ታዞ የሄደ ይጠይቀዋል፣
    ጥያቄ፣ ይሄ የምትሠቅለው ባንዲራ የምን የምን ሃገር ነው
    መልስ፣ እኔ ምን አባቴ አውቄ፣ ከየት አባቱ እንዳመጣው አላውቅም ፣ ሁለቱም መንግሥትን ሊያገለግሉ ነው አካሄዳቸው በሆዳቸው ግን የተግባቡ ይመስለኛል፡፡

Leave a comment