ረስቼው፤ የአድራሻ ለውጥ ሳልነግርዎ!

ባለፉት ግዜያት “በወርድ ፕሬስ” ነፃ የብሎግ አድራሻ በመጠቀም እንገናኝ እንደነበረ ይታወቃል። አሁኑ ግን በአንድ ፃድቅ ቸሮታ “ዶሜን” ስለተገዛልን  http://www.abetokichaw.com  በሚለው ድረ ገፅ ላይ የተለመዱ ጨዋታዎቻችንን እና መረጃዎችን የምንቀባበልበት አድራሻ አበጅተናል።

ታድያ ለወትሮው በዚህች “በወርድ ፕሬስ ብሎግ” ተመዝግባችሁ በየኢሜላችሁ ስትከታተሉኝ የነበረ ወዳጆች “የት ጠፋህ?” ብላችሁ መልዕክት ሰዳችሁልኝ ባይ ግዜ አዲሱ አድራሻችንን በብሎጋችን ላይ አለመናገሬ ትዝ አለኝ! (ሞት ይርሳኝ… “ጠላትህ” እንዳይሉ ችግር የለም እኔኑ ይርሳኝ! ባይሆን “አብሮይርሳን” ማለት ነው)

አዲሳባ ያላችሁ ወዳጆች  https://www.abetokichaw.com/ በሚል ብትገቡ የሚቻላችሁ ይመስለኛል።

አብሮነታችንን ያጠንክርልን!

እግዜር ኢህአዴግ ቢሆን ኖሮ የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ የሚሰጠው መግለጫ! (አቤ ቶኪቻው)

ዛሬ አዲሳባ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የምትወጣ ስለ አቶ መለስ መጥፋት አበክራ የምትጠይቅ እና የምትጨነቅ አንድ ጨዋታ አለችኝ። ለዝች ብሎግ አንባቢዎች ነገ ትለጠፋለች። እስከዛ ይቺን መቆያ እንኩማ፤

ያው ሁላችንም እንደሰማነው አቶ መለስ ተይዘዋል። ስንቱን ሲይዙ የነበሩት ሰውዬ አሁን ግን ራሳቸው በእግዜሩ በሽታ ተይዘዋል። በህመማቸው ሳቢያም ፓርላማው እንኳ ይኸው የ2005 ዓ.ም በጀቱን እስካሁን አላፀደቀም።

እኔ የምለው ግን በቃ አቶ መለስ ከሌሉ ሁሉም ነገር አለቀለት ማለት ነው? የምር ይሄ ነገር በጣም ያሳስባል።

ልክ እንደ አቶ መለስ ሆኖ የሚጫወት “ካስት” እንዴት አይኖርም!? እሳቸው ስለታመሙ እከሌ ወይም እከሊት እንደ አቶ መለስ ሆነው ይጫወቱልናል! መባል የለበትም እንዴ!? የቡድን ስራ ምናምን የሚባል ነገር የለም ማለት ነው…? አይበልባቸውና የሆነ ነገር ቢሆኑ ታድያ ምን ሊውጠን ነው!

ለማንኛውም ይቺን ያኽል ከተንደረደርን ወደ ፉገራችን እንግባ፤

እንግዲህ ይህ ዘገባ የሚተላለፍላችሁ በእግዜር ቁጥጥር ስር በሚገኘው ቴሌቪዥን ነው አሉ። በእግዜር ቁጥጥር ስር የሚገኝ ቴሌቪዥን የቱ ነው? ካሉኝ ህልም መሆኑን እገልፃለሁ። የምር ግን እግዜር ህልምን ያህል ቴሌቪዥን በእያንዳንዳችን ላይ ገጥሞ ሳለ ለገዛ ፕሮፖጋንዳው መጠቀም ሲችል በነፃነት የፈለገንን እንድናይ ማድርጉ ምን ያህል ዲሞክራት ቢሆን ነው ብለው አይደነቁም! በእውነቱ እንደ እግዜር አይነት ነፃነት የሚሰጠንን መንግስት ያምጣልን! እንደርሱ እንኳ የትም አይገኝም ግን ቢያንስ የሚቀራረብ…

ለማንኛውም እግዜር ኢህአዴግ አይደለም እንጂ ቢሆን ኖሮ የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ በቴሌቪዥኑ እንዲህ ይል ነበር፤ ብለን ብንገምት ምን ይለናል!? በነገራችን ላይ ይህ ዜና ቃል በቃል ከዚህ በፊት እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዳለም አራጌ፣ እነ ውብሸት እና ርዮት የተያዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያነበበልን ነው። ልዩነቱ እነ አስክንድርን የያዛቸው ፖሊስ ነው አቶ መለስን ደግሞ በሽታ ነው፤

አባቴ በህመም አይቀለድም ይለኝ ነበር። ነገር ግን በላዬ ላይ ያደረው በል ብሎኛልና እንደሚከተለው እጀምራለሁ፤ አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ። እርስዎም ሲጀምሩ እግዜሩ ይቅር ይበልህ ብለው ከጀምሩልኝ ችግር የለውም!

ገመትን፤
አቶ መለስ ዜናዊ ራሱን ኢህአዴግ ብሎ ከሚጠራ አሸባሪ ድርጅት ጋር የህዝብን መሰረተ አንድነት እና የሀይማኖት አውታሮችን ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ግብረ አይል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግለሰቡ በውጪ ሀገር የሚንቀሳቀሰው ቻይና ኮሚኒስት የተባለ አፋኝ ድርጅት የሀገር ውስጥ አደራጅ፣ ቀስቃሽ እና አንቀሳቃሽ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ስልጣንን ሽፋን በማድረግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አክራሪነት እንዲስፋፋ፣  አንድ ለአምስት የሚል ህዋስ በመፍጠር በመላው ሃገሪቱ መረብ ዘርግተው ሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሽብር ጥፋት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታውቋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በልማት ስም ሰላማዊ የሀይማኖት ሰዎችን ከፀሎት ስፍራቸው በማፈናቀል እንዲሁም ህገ መንግስቱን ሽፋን በማድረግ በርካታ ሙስሊሞችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር ፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ቡድን አረጋግጧል።

ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ህመሞቹ የመያዣ ፈቃድ እንዳሳዩዋቸው እና በአሁኑ ሰዓት በተኙበት ቦታ የተለያዩ በሽታዎች በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉለት መሆኑን ተጠርጣሪው ራሳቸው አረጋግጠዋል!

አቶ መለስ ዜናዊ በአሁኑ ሰዓት የተያዙ ሰዎች መብት እንዲያገኙ መደረጉን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጎብኚዎች እንዲመለከቷቸው ተፈቀዷል። ጎብኚዎቹም ተጠርጣሪው እንደፈለጉ ማቃሰት እና የሚያስፈልጋቸውን ነገርም ያለ አንዳች ገደብ ሲጠይቁ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የተጠርጣሪው ግለሰብ ፍርድ ነፃ እና ገለልተኛ በሆነው መንግስተ ሰማያት መታየት የተጀመረ ሲሆን ጥፋታቸውን አምነው እና ተፀፅተው ይቅርታ ከጠየቁ ምህረት ሊደረግላቸው እንደሚችል ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በድጋሚ ይቅር ይበለን ዜናው አበቃ!

የታሰሩት የዋልድባ መነኮሳት የት ገቡ!? (አቤ ቶኪቻው)

በ1998 ዓ.ም አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ፤ ለአንድ ስታስቲክሳዊ ስራ ወደ ወደ አርማጭሆ አካባቢ ሄጄ ነበር። በወሬ ደረጃ ስንሰማው የነበረ “አርበኞች ግንባር” በመባል የሚታወቅ የታጠቀ ቡድን እዚህ አካባቢ “በህይወት” መኖሩን ሰማሁ። ለስታስቲክሳዊ ስራው የገጠሩን መንደር መንገድ እንዲመሩን የተመደቡልን የመንግስት ታጣቂዎች ነበሩ። እኔ እና ሌሎች ከአዲሳባ ለስራ ወደ እዚህ የመጣን ልጆች ስለ አርበኞች ግንባር በደንብ ለማወቅ ጉጉት አድሮብናል። ነገር ግን የመንግስት ታጣቂን ስለ ተቃዋሚ ለዛውም ስለ ሸማቂ ሃይል መጠየቅ እየፈራን እየተባን በአካባቢው ስለሚኖሩ ሽፍቶች በመጠየቅ እናሟሙቅ ጀመር።

“እዚህ አካባቢ ሽፍታ አለ ይባላል እውነት ነው?”  አልነው አጃቢያችንን፤

“እንዴ ጋሼ ሽፍታማ ሃገሩ ነው!” አለን በኩራት። (በነገራችን ላይ አርማጭሆ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ክፍለ ሀገሮች ቢሄዱ በእድሜ የሚበልጥዎም ሰው እንኳ “ጋሼ” ብሎ በአክብሮት ነው የሚጠራዎት። እናውቃለን ባክህ… ካሉኝ “እኮ…” ብዬ ቀጥላለሁ!)
ጥያቄያችን ቀጥሏል።
“ሰዉ ምን ሆኖ ነው የሚሸፍተው…?” አልነው።
“ሰበቡማ ብዙ ነው ምሰሌ፤ በመንደር ግጭት የተጠቃ እንደሆነ፤ አኩርፎ ጥቃቱን ለመወጣት ይሸፍትና በዛው ሽፍታ ሆኖ የሚቀር አለ…” ልክ ይህንን ምላሽ እንደሰማሁ፤ መቼም ያን ጊዜ ቀልጣፋ ነበርኩ፤ ለማወቅ ወደፈለግነው ዋና ነጥብ ቀልጠፍ ብዬ ገባሁ፤

“በመንግስት ላይ አኩርፎ የሚሸፍትስ የለም?” ብዬ ጠየቅሁ…!

ይሄኔ መንገድ መሪያችን የመንግስት ታጣቂ ያነገታትን አሮጌ ክላሽ ከፍ ከፍ እያደረገ፤
“እሱማ ምን ይጠፋል!?” ብሎ በጥርጣሬ እያየን ዋናው ጨዋታችንን በአጭሩ ሊቀጨው ፈለገ። ስለ አርበኞች የማወቅ ጉጉት የሁላችንም ነበርና አንዱ ወዳጃችን፤

“አርበኞች የሸፈቱት በመንግስት ላይ አኩርፈው አይደል እንዴ!?” ብሎ ሌላ ጠቋሚ ጥያቄ አመጣ። በሆዳችን ጎ…በዝ ብለን ወዳጃቸንን አደነቅን!
ይሄን ጊዜ የገጠሩን መንገድ ሲመራን የነበረው የመንግስት ታጣቂ  ቆም አለና፤ ትክ ብሎ አየን፣ ከዛም በሆዱ “የመጣው ይምጣ!” ያለ በሚመስል መልኩ፤
“ጋሼ አትሳሳት አርበኛማ ሽፍታ አይደለም። አርበኛ የአላማ ሰው ነው!” ብሎ መንግድ መምራቱን ቀጠለ።

በእውነት በጣም ነበር የተደነኩት። በወቅቱ የሄድነው ለመንግስት ስራ ነበር። መንገድ የሚመራን የመንግስት ታጣቂ ነው። ይህ የመንግስት ታጣቂ ስለ ሸማቂው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር በአድናቆት ሲናገር መስማት በእውነቱ ያስገርማል። ግንባሩ እውነትም በህዝብ ልብ ውስጥ የገባ ስለመሆኑ ማስረጃ ነው።

ከዛ በኋላ በይፋ ድጋሚ ስለ አርበኞች ግንባር የሰማሁት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነበር። “ሀገር ጫታ ሆነ!” በሚል ርዕስ በ2001 ዓ.ም አካባቢ (ነው መሰለኝ) መንግስታችን ከዛ በፊት አንድም እንኳ፤ በዛ አካባቢ ስለነበረው እንቅስቃሴ ያልነገረን ለግንባሩ እውቅና ላለመስጠት ነበር ለካ!

“ሀገር ጫታ ሆነ” በሚለው እና ስለ አርበኞች ግንባር የሚዳስሰው የኢቲቪ ፕሮግራም  ስለ አርበኞች ግንባር ተጨማሪ ማወቅ ቻልን…! “ለካስ እነዚህ ሰዎች በዚህ ደረጃ መንግስታችንን አስጨንቀውታል!?” እኛኮ መንግስታችን ዝም ሲል ግንባሩን ከቁብም አልቆጠረውም ብለን ነበር። ለካስ የሆዱን በሆዱ ችሎ ነው ፀጥ ያለው…? ምስኪን መንግስታችን! ብለን አዘንን።

ከዛ በኋላ ለረጅም ጊዜ ስለዚህ ግንባር በቅጡ ሰምቼ አላውቅም ነበር። አሁን በቅርቡ ደግሞ ሌላ ወሬ ሰማሁ።

በዋልድባ ገደም ህልውና ላይ እየተገነባ ያለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ባለፉት ሰሞናት ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። ኢቲቪም ትንሽ “ፎገር ፎገር” አድርጎ ነገሩን አንደተረሳ አድርጎታል። የአካባቢው ህዝብ መነኮሳቱ እና ምዕመኑ ግን ዝም አላሉም ለፈጣሪም ለህዝቡም አቤት እያሉ ነበር። ቢሆንም ግን መንግስት አካባቢውን በጦር ከቦ ቁፋሮውን ተያይዞታል። እሰይ የኔ አንበሳ! ብለን አድንቀን ሳንጨርስ ታድያ ሌላ ነገር ሰማን፤ ምን…? አዲስ መስመር ላይ አለልዎት

አርበኞች ግንባር፤ “በአካባቢው የህዝቡን ተቃውሞ ችላ ብለው በቁፋሮ የተሰማሩ መሳሪያዎችን አወደሜያለሁ” የሚል መግለጫ አወጣ።
ከላይ እንዳልነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር። ልክ እንደ ኢህአዴግ ብሶት የወለደው፤   በኢህአዴግ አመራር ተማሮ ጫካ የገባ የታጠቀ ሃይል ነው።
ባለፈው ጊዜ ደጀ ሰላም የተሰኘ ድረ ገፅ በዋልድባ ገዳም መነኮሳት መታሰራቸውን እና ለተቃጠለው ዶዘር እና ለተሰነዘረው ጥቃት ሃላፊነቱን ትወስዳላችሁ። መባላቸውን ዘግቦልን ነበር። እስከ አሁንም መነኮሳቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አልሰማንም። ልብ አድርጉ ሸማቂዎች ላደረሱት ጉዳት ተጠያቂው ከዋሻ ወጥተው የማያውቁ መነኮሳት ተደርገዋል።

አሁን እንግዲህ አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ነው። ጥያቄው የኢህአዴግ አባላትን ደጋፊዎችን እና ተደጋፊዎችን ይመከታል። ማሳሰቢያ መልሱን በትግሉ ወቅት የተሳተፉ አንዲመልሱ ይበረታታል። ከድህነት ጋር የምትታገሉትን አላልኩም።

እኔ የምለው ኢህአዴግ በትግል ላይ እያለች የደርግ አድናቂ ነበረች ማለት ነው…? ከመቼው ገብተን ከመቼው እንደ ደርግ በሆነን! ብላ አብዝታ ታስብ ነበር ማለት ነው? የታጠቀ ሃይል ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ባለበት ጥቃት የአካባቢው ሰው እና የሀይማኖት አባቶችን ማሰር አግባብ ነው!?  ወይስ መነኮሳቱ በዋሻ ውስጥ ሲገኙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ታጋዮች መስዋቸው ነው!?

በመጨረሻም

እመክራለሁ

ጎበዝ ይሄ ነገር ብሶትን ማቀጣጠል በመባል ይታወቃል። ደርግም ጉድ የሆነው እንዲሁ ለታጋዮች ጥቃት በአፀፋው ህዝቡን ሲያንገላታ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይሄንን እናንተው በትግል ላይ ያሳለፋችሁት እንጂ፤ እኔ ከኑሮ ጋር የምታገለው ግለሰብ ልነግራችሁ አይገባም ነበር። ግን ተናግሪአለሁ ባለስልጣኖቻችን ሆይ የብሶት ማርገብገቢያ አትሁኑ!