ቅዳሜን አባቴ “ሰንበተ ጢኖ” ሲል ይጠራው ነበር። ነገም ዋናው የእረፍት ቀን ነው በነዚህ የእረፍት ቀናት ደግሞ “ክቡር…” ምናምን እያልኩ ከማካብድብዎ ዝም ብዬ መለስ ብልዎትስ ስል አሰብኩልዎ…!

አዎና በነዚህ የእረፍት ቀናት እርስዎም ቢሆኑ ዘወትር የማይለይዎትን የክብር ከረባትዎንም ሆነ ያቺ “ማን እንደሰፋት የማያወቁት” ሱፍዎን ወለቅ አድርገው የሆነበት አስቀምጠው እና ቱታዎን ለብሰው ለሃያ አመታት በምቾት እና በድልዎት የተቀመጡባት “ወደፊትም ለአርባ አመታት የሚኖሩባት” ቤተመንግስትዎ ውስጥ ፈርሸው ቤቱን ሞቅ ሞቅ እያደረጉት እንደሆነ አስባለሁ።

አረ ሳልነግርዎ የሀገሬ ሰው በዛን ሰሞን ምን እያለ ሲቦጭቅዎ እንደነበር ከዛሬ ነገ እነግርዎታለሁ ብዬ እርስት አደርግሁት እኮ!

እኚያ የየመኑ ፕሬዘዳንት የሀገራቸውን አብዮተኞች ሸሽተው እርስዎ ዘንድ የተሸሸጉ ግዜ ሰዉ ምን ብሎ ሲቧልትብዎ እንደነበር ሰምተዋል? ከሰሙም ደግመው ይሰሙት ካልሰሙም ልንገርዎ እና ይግረምዎ…!

መቼም የኛ ሰው ነገረኛ ነው። ያው እንደሚታወቀው የመኖች ይቺ የጫት ነገር አትሆንላቸውም ይባል አይደል? እናልዎ እርሳቸውም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለዚህ የሚሆን ሁነኛ ወዳጅ ፍለጋ ነው እያለ ሰዉ ሲያወጋ ነበር። እኔማ እንዲህ አይነት የርሳቸውን ክብር የሚነካ አሉባልታ አግባብ አይደለም ብዬ ከስንቱ ተጣለሁልዎ መሰልዎ…

ለማንኛውም ዝም ብዬ ሳስብ ዛሬ ከትላንት እና ከትላት በስተያ ጭቅጭቅ የተረፈች መንፈስዎን “ፍርሽ” ብለው የሚያድሱበት ቀን ይመስለኛል። አሁንም ሳስበው ሳስበው ከፊት ለፊትዎ የፕሮፌሰር መስፍንን “አደጋ የበዛበት የአፍሪካ ቀንድ” መፅሐፍ በአድናቆት እየቃኙ  የተመስገን ደሳለኝን “የመለስ አምልኮ” የተባለውን መፅሀፍ በብስጭት እያዩ፤ እንዲሁም የወሰን ሰገድን “የቃሊቲ ምስጢሮች” በአግራሞት የሚያገላብጡ ይመስለኛል። የመንጌ እና የሲሳይ አጌና መፅሀፎች ቀድመው አንብበዋቸዋል ብዬ እገምታለሁ። ወይስ ዛሬም ከ ”ዘኢኮኖሚስት” ውጪ አያነቡም?

የሆነ ሆኖ እንዴት ሰነበቱ መለስ?

ዋናው እንኳ ይቺን ጦማር የምሰድልዎ በትላንቱ የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ አንድ የምስራቅ አፍሪካ ሰው በጥያቄ ሲዳፈርዎ አይቼ መበሳጨቴን ልገልፅልዎ ነው።

በሀገርዎ ፓርላማ ውስጥ ሲጠየቁ እንዳሻዎ በተረት፣ በቀለድ፣ በጨዋታ፣ በሀይለቃል፣ አረ ባሻዎ መልኩ ቢመልሱ አንድ እንኳ የሚናገርዎ ማን አለ? ማንም። እርግጥ ነው ከዚህ በፊት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ተመስገን ዘውዴ “ምነው አሁንስ በዛ ንግግርዎ ለከት ይኑረው…!” አይነት ነገር ሲናገሩ አንዳንዴም ደግሞ ከርስዎ ማንጓጠጥ እኩል ሲያሽሟጥጡዎት ተመልክቼ አውቃለሁ።

ከዛ ውጪ ግን ማንም ያልደፈርዎትን ሰውዬ ትላንት በአለም ኢኮኖሚ ፎረም መድረክ ላይ፤ “ዲሞክራሲን ከሚያፍኑ እንደ ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር በይበልጥ የመተባበራችሁ  ምስጢር ምንድነው?” ብሎ ሲያበቃ “አቶ መለስ ዙሪያ ጥምጥም ሳይሄዱ በቀጥታ ይመልሱልኝ” ማለቱን ስሰማ እንዴት ቢደፍራቸው ነው? ብዬ የደነገጥኩትን መደንገጥ የተበሳጨሁት መበሳጨት አይጠይቁኝ።

ለነገሩ ግን እርስዎም እኮ ራስዎን አለቅጥ ለተቺ አጋለጡ። ትዝ ይልዎት እንደሆነ፤ በፎረሙ ላይ አወያይ የነበረችው ሴት አንድ ጥያቄ ጠይቃዎ ያልተጠየቁትን ሲያወሩ፣ ሲያወሩ፣ ሲያወሩ ቆይተው ሰዓቱን ከፈጁት በኋላ፤ “ጥያቄሽን ረሳሁት ምን ነበር ያልሽኝ?” ብለው ድጋሚ ሲጠይቁ ተሰባሳቢው በሙሉ እንዴት እንደሳቀብዎ እኔም እንዴት እንደተሸማቀኩልዎ ቢያዩኝ ለአንዱ ቀበሌ ሊቀመንበር ያደርጉን ነበር።

በነገራችን ላይ ባለስልጣኖቻችንን ኮርቼባቸዋለሁ። እንዴ አሪፍ አስተኳሽ ሆነው የለም እንዴ…! ገና እርሰዎ ተናግረው ሰይጨርሱ በጭብጨባ አዳራሹን ማድመቅ ይጀምሩ ነበርኮ። አዩ ስብሰባው ኢትዮጵያ ውስጥ መደረጉ ካለው ጠቀሜታዎች አንዱ ይሄ ነው። በርከት ያሉ ባለስልጣናትን አስገብቶ በየንግግሩ እንዲያጨበጭቡ ማድረግ። እንዴት እንዴት ያሉ ጥሩ አጨብጫቢ በለስልጣኖች አሉን! በእውነቱ ኮራሁባቸው።

ለማንኛውም መለስ ሆይ እንደው እንዴት ሰነበቱ ልበልዎ ብዬ ነው። እስቲ እንደ”ሙዳችን” መልካም ፈቃድ በየሰንበቱ እንዴት ሰነበቱ? እያልኩ እጠይቅዎታለሁ።

ቸር ይግጠመን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

4 responses »

  1. selam says:

    bareta belanale ,batam naw yatamachegn

  2. tigist says:

    አቤይ ያንተ መርፌ አወጋግ ለስላሳ ቢሆንም መዳኒቱ ገን አንጀት ያርሳል ! እንባይ እስኪንቀንጠባበት ነው የሳኩት የልብ አውቃ አይደለህ በርታ…..

  3. በለው! says:

    አባቴ ቅዳሜ”የሰንበቴ ጢሞ” እያለ ይጠራዎት ነበር ? ቆይ ግድ የለም ሰውዬው ሰሞኑን ተወጣጥረው የማንበቢያ ጊዜ የላቸውም ብለህ ጉድ አደረካቸው? ? “ማን እነደሰፋት የማያቋት ደስ ስላለቻቸው ገዝተው የለበሷት ሱፍ ምነው እንደዚህ ባለጌ የተፋበት የመሰለችው ለምንድነው ? ለብሰዋት ሲቅሙ ነበር ወይስ ለብሰዋት ተኝተው ነበር? ወይስ ተንተርሰዋት ነበር? ከ”ኢኮኖሚስት” መፅሔት በቀር አያነቡም የተባለላቸው ” ዘ ይኮንን በሚሰት ”

    እያንዳንዳችሁ “የምትሰሩትን እናያለን… የምታደረጉትን እንከታተላለን… የምትጽፉትን እናነባለን”

    ድንቅ ስብሰባ ነበር “የግል ባንክ ያልፈቀድነው መቆጣጠር ስለማንችል ነው” ፈረነጆቹ ቋንቋቸውም ሆኖ ስላልገባቸው ዝም አሉ አጃቢዎችዎ ሐሳብዎን ሳይጨርሱ አጨባጨቡ፤ ኢቲቪ የአጨብጫቢውን ድምቀት ያለበትን አቀረበ እኛም ታዘብን!! ቁምነገሩ ያለው የግል ባንኮች ቢከፈቱ የወያኔ ባለሥልጣናት፣ ካድሬ፤ ቤተዘመዶች እና( መጤው)ሕዝቦች ያሏቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌላውም ብሔር ብሔረሰው በገበያ የመፎካከር፤ የመሥራት፤ የማደግ ዕድል፤ ይከፈትለታል ከአንድ ብሔር ሞኖፖል ነጻ የሚሆንበት አጋጣሚዎች ይፈጠሩ ነበር። የሀገሪቱም የገበሬው ምርት ውጤቶች ጥሩ ዝውውርን ያደርጉ ነበር። ምንም እንኳ “ከዝነጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል” ቢሆንም በአንዳንድ ቀጥተኛ አገላለጽ የታንዛኒያው የተሻለ ነበር ለአሁኑ አልተሳካም ለሚቀጥለው ቅላፄዎን ሳይሸራርፉ፤ ቶኑ ምንም አይልም፤የተመልካች የዓይን ግንኙነቱ አይከፋም ፤ደጋፊን አብዝቶ አዳራሹን ማሸበር በግል ፓርላማዎ ሊሰራ ይችላል ። ሌላው ታዛቢም የሚከተለውን መልዕክት አለው።

    “አዩ ስብሰባው ኢትዮጵያ ውስጥ መደረጉ ካለው ጠቀሜታዎች አንዱ ይሄ ነው። በርከት ያሉ ባለስልጣናትን አስገብቶ በየንግግሩ እንዲያጨበጭቡ ማድረግ። እንዴት እንዴት ያሉ ጥሩ አጨብጫቢ በለስልጣኖች አሉን! በእውነቱ ኮራሁባቸው። ብትጠሉትም የሚወዳችሁ እና ታማኝነቱ ከእናንተ የማይለይ ወዳጃችሁ…
    ለማንኛውም መለስ ሆይ እንደው እንዴት ሰነበቱ ልበልዎ ብዬ ነው። እስቲ እንደ”ሙዳችን” መልካም ፈቃድ በየሰንበቱ እንዴት ሰነበቱ? እያልኩ እጠይቅዎታለሁ።

    ቸር ይግጠመን!

  4. Kulich says:

    Here is what I read on twitter last week. I like it and I am sharing it here

    “እነሆ ጠቅላያችን ከተወለዱ 57 አመታት፤ ከጠቀለሉን ደግሞ 21 ዓመት ሆናቸው:: እንዴት ነው ጥቅለላ? የሚል ጥያቄ ብቻ ለ 4 ኪሎ ይድርስ haha”

Leave a comment