ጋሽ ግዛው በድፍን ሽሮሜዳ ታዋቂ የነበሩ ሞቅታን እንደገንዘብ እየቆጠቡ የሚጠቀሙ ሰው ነበሩ። እርሳቸውን ሳይሰክሩ ያያቸው ሰው ካለ እርሱ አብሯቸው ያደረ መሆን አለበት፤ በቀረ ግን ሁሌም ሞቅታ ውስጥ ናቸው።

ጋሽ ግዝሽ ሁልግዜም ወደቤታቸው የሚገቡት እምቢኝ እያሉም ቢሆን፤ በሰዎች ተደጋግፈው ነው። አንዳንዴም በወሳንሳ! አለበለዛ ሲወድቁ ሲነሱ የሚያዩት አበሳ አይወሳ…! ጋሽ ግዛው በሞቅታቸው ተዓምር ካመጡት ልዩ ልዩ ጠባይ ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። ከመንግስታችን ተዓምራዊ በሀሪያት ጋር እየተነፃፀረ ይቀርባል።

አንድ፡

ያለ አጠጋቢ ምክንያት መሳደብ እና መዝለፍ። ለነገሩ ምክንያቱ ለርሳቸው አጥጋቢ ነው በሞቅታ ውስጥ ለመግባት ላልታደለ ሰው ግን፤ “እንዲህ አይነት ክፉ ቃል ከእርሳቸው አንደበት ይጠበቃል?” በሚያስብል መልኩ አላፊ አግዳሚውን እና በአግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጠውን ጠጅ ጠጪ ሁላ ሙልጭ አድርገው ነው የሚሳደቡት። መንግስታችን በተለይም ዋናው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በፓርላማ ዘመናቸው የሰነዘሩብንን ሃይለ ቃል… (ስድብ ማለት አላስችል አለኝ እኮ!) ያ ታማኝ በየነ ለታሪክ ይሆናል ብሎ ሰብስቦ አስቀምጦልዎታል  ከጥቂቶቹ መካከል “ቆሻሻ… በክት… የበሰበሰ…እብድ ውሻ…” የሚሉት ይበልጥ እውቅና ያገ  ስድቦቻቸው ናቸው። በእውነቱ እንዲህ አይነቱን ስድብ ጋሽ ግዛውም አይሞክሩትም።

በተለይ አሁን አሁን የሀይማኖት ሰዎች ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ናዳዎች ስናይ በእውኑ መንግስታችን ሞቅ ብሎታል ያሰኛል። መቼም አንድ መነኩሴን “የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ያለው!” ብሎ መጠርጠር ከስድብ በላይ ነው። ስሙ ራሱ “ሰላም” የሆነውን ሙስሊም አሸባሪ ብሎ መኮነንም ደረጃውን የጠበቀ ስድብ ነው።

ሁለት

ጋሽ ግዛው ሰክረው ሲወጡ ህፃናትን ማባረር እና ሲይዟቸውም መምታት። መለያ የስካር ባህሪያቸው ነው። በርግጥ ህፃናቱም እርሳቸውን ከመተቸት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም። “ሰካራም ቤት አይሰራም ቢሰራም ቶሎ አይገባም ቢገባም ቶሎ አይተኛም … ቢተኛም….” እያሉ መስከር ያለውን ጦስ በቀልድም በዋዛም ይነግሯቸዋል። እራሳቸው ግን ማንም ምንም እንዲናገራቸው አይወዱም። ስለዚህ ህፃናትን ያሳድዳሉ ሲያገኙም ይደበድባሉ። መንግስታችን እና ጋሽ ግዛው አንድ ናቸው። ቀላል ማስረጃ ይህው እነ እስክንድር የታሰሩት እነ ዳዊት ከበደ እና መስፍን ነጋሽ የተሰደዱት “ሰካራም ቤት አይሰራም ቢሰራም ቶሎ አይገባም” ብለው ትችት ስላቀረቡ አይደለምን!?

ሶስት

ዋና የጋሽ ግዝሽ መገለጫ መጣችላችሁ፤ “እኔ ግዛው ቀብራራ እኮ ነኝ አሁን ይሄንን ገብቼ ዘለዝልና  ከዚህ እዛ ድረስ ክሪስመርስ ነው ያማስመስለው” ብለው በጋዜጣ የተጠቀለለች ቅንጥብጣቢ ስጋ ለመንገደኛው በሙሉ ያሳያሉ። እውነቴን ነው የምልዎ ቅንጥብጣቢዋ እቤት ሳትገባ መንገድ ላይ ተበትና የምትቀርበት ግዜ ይበዛል። አንዳንዴ በሰላም እቤት ከገባች ደግሞ ለነገም መፎከሪያ ስለምትሆን ተጠቅልላ ትቀመጣለች እንጂ አትበላም። ብለው የሚያሟቸው ብዙ ናቸው። ታድያ እዝችጋ መንግስታችን ትዝ አላላችሁም…? ይሄ እኮ “መልካም ገፅታ ግንባታ” ነው። (ነውንዴ በዚህማ መንግስታችን ከጋሽ ግዛውም ይበልጣል! ሳይሉ አይቀሩም ብዬ ልጠርጥር?)

አራት

ጎረቤት ወይም ሌላ አሳቢ ሰው “ለምን ይሰክራሉ?” ብሎ የጠየቃቸው እንደሆነ፤ አሁን ትልቅ ፀብ ተነሳ! ከመንግስት ቋንቋ እንዋስላቸው “ይሄ የውስጥ ጉዳያችን ነው ከጣማችሁ ተቀበሉ ካልጣማችሁ በሊማሊሞ በኩል አቋርጡ!” ይላሉ። ታድያስ መንግስታችንስ ማንን ሲሰማ አይተው ያወቃሉ? (ቻይናን… ብለው እንዳያላግጡ ብቻ!)

በጥቅሉ

መንግስታችንም ሆነ ጋሽ ግዛው ሞቅታ ውስጥ መሆናቸው ጥርጥር የለውም። እናም ደገፍ ደግገፍ ካላደረግናቸው በቀር ክፉኛ አወዳደቅ እንዳይወድቁ ያሰጋል። ትልቁ ችግር ግን ጋሽ ግዛውም ሆኑ መንግስታችን እንደግፋችሁ ብለው የቀረቧቸውን ሁሉ እንደሌባ ነው የሚቆጥሩት…? እናም ማንንም አያስጠጉም ታድያ ብዙ ግዜ ክፉኛ አወዳደቅ ይወድቃሉ።

ቀጥሎ መንግስቴን እመክራለሁ። (ይህ ምክር እንደ አቋም መግለጫም ይታይልኝ!)

ማንም የተቃወመ ቢመስል ቅሉ ለሀገር እና ለመንግስቱ ልስራ ላገልግል ያለ ነው። መንግስቴ ሆይ እሺ በል “ተቃዋሚ” “አሸባሪ” “ነውጠኛ” ያልካቸው በሙሉ እንደግፍህ እያሉ እንደሆነ ምን ታውቃለህ…? በእውኑ ብቻህን እየተንገዳገድክ አይወድቁ አወዳደቅ ከምትወድቅ ደግፉኝ አግዙኝ ማለት የአባት ነውና ዛሬውኑ እንደግፍ ስላሉ የታሰሩት ይፈቱ! “ሞቅታ ይብቃ” ብለው የሚመክሩትም ይሰሙ!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

2 responses »

  1. አቤ:- ያለ:ፍልላጐትህ:በመሰደድህ:አዝነናል::እንደ:ልብብህ:ለመጻፍ:ምቹ:ቦታ:እንደ:እሚሆንልህ:ስንናሥብ:
    ግን:ሕዝባችን:ለሚፈልገው:ዜና:አድራሽነህን:በመገንዘብ:እንኮራብሃልለን::

  2. በለው! says:

    አዎን፣ ሲደግፉህ እወቅበት፤ የተደገፉህን ግን አትመናቸው፤ አግዳሚ መቀመጫ ላይ የተቀመጡም በፓረላማ መቀመጫ ያላቸውም ባይጠጡም ሽታው አስክሮአቸዋል እና! ያቶ መለስ ቃል በደጋፊዎች፤ የሻገተ አመለካከት፤ነፍጠኛ፤ሰው በላ፤ ኪራይ ሰብሳቢ፤ሞፈር ዘመት፤ መልዕክተኞች (የቀጠናው አተራማሾች) በዚያው ላይ ሳቅ ጭብጫቦ..ካ ካ ኪ ኪ ሆ ሆ….

    አዎን የታስሩ የተደበደቡ የተሰደዱ በዓይነ ቁራኛ የሚጠበቁም አሉ ። ምን አደረጉ፣ዘፈኑ፣ደገፉ ለመሆኑ ሃጢያቱ ምንድነው?
    “ወያኔ አይሰራም … ቢሰራም አያሳምርም… ባያምርም ግድ የለውም … ግድ ያለውንም አይወድም… የሚሰራም አይወድም… ይገፋፋል እንዲሰደድም… ባይሰደድም ያስረዋል አይለቀውም… ይገርፈዋልም አይተወውም…. ብለው አስቀድመው ጮኸው ነበር በርዶአቸው ግን ማን ይሰማ ወያኔ ግን አሁንም ሞቅታ ውሰጥ ነው፤

    ድምጻቸውም ሥራቸውም ህልውናቸውም ይመለስላቸው ነጻነትን እኩልነትን ሰላምን ፍቅር መተሳሰበን ተጠምተዋል ተበርደዋል ስለዚህ ሞቅ ያላቸሁ በረድ፤ ሰከን፤ቀዝቀዝ በሉ፤ ሞቅታ “የመልካም ገፅታ ግንባታ” አደለም !
    የአፍ ወለምታም በቅቤ አይታሽም ! አላግባብ አፍን መክፈትም አብዮታዊ ‘ዶማነት’ ኢንጂ አቢዮታዊ ዴሞከራሲ አደለም።አራት ነጥብ።

Leave a comment