ዛሬ በጠዋት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የሙያዬ ስልክ ነው። ሙያዬ ደሞ ማናት…? ብዙ ወንድማገኝ ትባላለች። በኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ (ኢካድኤፍ) ፓልቶክ ሩም ውስጥ ካሉ በታላቅ ትጋት “ሀገሬ ኢትዮጵያ  አብቢ ለምልሚ”  እያሉ ከሚወተውቱ ትጉሀን መካከል አንዷ ናት!

ሙያዬ ወይም ብዙ ወንድማገኝ ኢህአዴግ ገብቶ ምንም ሳታደርገው ከስራዋ  አሰናበታ እንጂ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው ጋዜጠኞች ምድብ  ነበረች። በተለይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስታቀርባቸው በነበሩት ሀገርን የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞቿ ታላቅ አድናቆትን ያተረፈች ነበረች። በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ስለ ሙያዬ ሲነግሩን “ወያኔ ብዙ ወንድማገኝ ምን አድርጋው ከስራ እንዳሰናበታት ይደንቀኛል እርሷ እኮ ትልቅ ሽልማት የሚገባው ሀገር የማስተዋወቅ ስራ ስትሰራ የኖረች ትጉህ ጋዜጠኛ ናት!” ብለውን ነበር።

ሙያዬ በዚህ ፓልቶክ ሩም ስታቀርበኝ የመጀመሪያዋ አይደለም በርካታ ግዜ ዕድሉን ሰጥታኛለች። አረ እንደውም በህይወቴ በሚዲያ ደረጃ ለመጀመሪያ ግዜ “ብንጠይቀው ይመልሳል” ብላ፣ ሰው አድርጋኝ ቃለ  ምልልስ ያደረገችልኝ ሙያዬ ነበረች። ከዛም በኋላ በተደጋጋሚ እየደወለችልኝ ከ”ከፓልቶክ ሩሙ” ታዳሚዎች እና ከራሷ የሚቀርቡልኝን ጥያቄዎች ለመመለስ ሙከራ አደርግ ነበር።

አሁን ግን ጠፍታ ከርማ፤ በስንት ግዜዋ ዛሬ ደወለችልኝ…
ከጠየቀችኝ ጥያቄዎች ውስጥ አበበ ገላውን እና ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዙሪያ የሚያጠነጥን ይገኝበታል…! አረ እርሷ ጉደኛ ነች፤ “አንተ የአበበ ገላውን እድል ብታገኝ እንደዛ ለመናገር ወኔው አለህ ወይ?” ብለኝ ቁጭ…

እውነቱን ለመናገር እኔ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን አበበ እንዳገኛቸው አይነት ባገኛቸው እንደርሱ ላስደነግጣቸው አቅም ያለኝ አይመስለኝም! ይልቅስ ተንደርድሬ ሄጄ እግራቸው ስር ድፍት ብዬ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ፤ “ንጉስ ሆይ ሺ አመት ነገሱ አይበቃዎትም…? አረ በቃዎ፣ አረ ተዉ እኛንም አያስጨንቁን፣ አረ ይተዉ ግፍ አያከማቹ፣ እርስዎም ስልጣኑ ይደክምዎታል፤ እኛም የጫኑብን ቀንበር አደከመን፣ ስለ አቡንአረጋዊ ብለው ገለል ይበሉልን! ባይሆን ውለታዎን እንከፍላለን እባክዎን በቃዎ…!” ብዬ እለምናቸዋለሁ እንጂ ጨክኜ እንደ አበበ ገላው የምጮኽባቸው አይመስለኝም!

ለማንኛውም አበበ ገላው የለኮሰው ችቦ አሁንም ድረስ እያበራ ነው። መነጋገሪያነቱም አላበቃም። ለምሳሌ “ኢካድኤፎች” ባለፈው ግዜ አቤ በውይይታቸው ላይ ተጋብዞ አደራ ባለቸው መሰረት ኢሳትን ለመደገፍ የሚያስችል የገዘብ ማሰባሰቢያ እያደረጉ ይገኛሉ። ሙያዬ እንደነገረችኝ ከሆነ (መሆኑም አይቀርም…) “ዘመቻ አበበ ገላው” በሚል በተሰየመው ገቢ ማሰባሰቢያ እስከ አሁን ወደ ሃያ ሺህ ዶላር አካበቢ ለኢሳት ማጠናከሪያ አሰባስበዋል።

ዛሬ ታድያ እኔ በተጋበዝኩበት እለት ከ”ሩሙ” ታዳሚዎች እጅግ ወዳጆቼ የሆኑቱ በስሜ ለኢሳት ገንዘብ ሊሰጡልኝ ቃል ገብተዋል። በእውነቱ እነዚህን ወዳጆቼን በይፋ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። እውነቱን ለመናገር ኢሳት ለህዝቡ መረጃ በማድረስ በኩል እየተጫወተ ያለውን ሚና አደንቃለሁ። እናም አቅም ያለው ሁሉ ኢሳትን መርዳት እንዳለበት እመክራለሁ።

ቀጥሎ ለኢሳቶች ይህንን እላለሁ።

እንግዲህ ኢሳትን ለመደገፍ እኔም ቦንድ ተገዝቶልኝ የለ…? ቦንድ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው…? ከአባይ እርዳታ ጋር አነፃፅሬ ለማሸሞር ነውን…? በፍፁም። አሁን የቁም ነገር ግዜ ነው።

ኢሳቶች የተዋጣውን ገንዘብ መመለስ አለባችሁ ብዬ አስባለሁ። “እኛ ንግድ አንነግድ ምን አትርፈን እንመልሳለን…?” ብላችሁ ለመጠየቅ አትቸኩሉ! “እንግዲያስ…?” በሉኝ፤ ጎሽ እንደሱ ነው የሚባለው…! ብዬ እቀጥላለሁ፤ መረጃ የተራበውን ህዝብ በየቤቱ ደረጃውን የጠበቀ መረጃ ብታደርሱት ከዚህ የበለጠ ክፍያ ከወደየት ይገኛል!? በእውኑ ከኢቲቪ የሚገኙ በሽታ አምጪ መረጃዎችን የምናከሽፍበት አማራጭ የዜና አውታር ካገኘን ያደረግነው እገዛ ከነወለዱ እንደተመለሰ አይቆጠርምን…!? መጠርጠሩስ…!

ማጠቃለያ፤
ኢሳትን የረዳችሁ በሙሉ ሁላችንንም እንደረዳችሁ ይቆጠራልና እግዜር ይስጣችሁ ወደፊትም ቀጥሉበት። ኢሳቶችም ደረጃውን የጠበቀ ስልጡን መረጃ ታቀርቡልን ዘንድ አደራ በዲሽ፣ አደራ በኢንተርኔት፣ አደራ በራዲዮን እንላችኋለን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

2 responses »

  1. ሄሌሌ ሃንባቤ says:

    “አፋፍ አፋፍ ስሄድ አገኘሁ ሚዳቋ፣
    ጅራቷን ብይዛት አይኗ ፍጥጥ አለ” እየተባለ የሚታወቀዉ ሰንጎ መገን ግጥም ወደ አእምሮዬ ብቅ ብሎ አስታዉሶኝ ነበር አበበ ገላዉ “መለስ ዜናዊ አምባ ገነን ነዉ” ብሎ ሲጮህበት መለስ ዜናዊ አይኑ ፍጥጥ ብሎ ቪዲዮ ላይ ሳየዉ። ይህን የሰንጎ መገን ግጥም የተማርኩት አራተኛ ክፍል ሳለሁ ነበር። አራተኛ ክፍል ሳለሁ የአማርኛ አስተማሪያችን ካስተማረን የሰንጎ መገን ግጥሞች በከፊል እነሆ፤
    “ስጋ ያማረዉና መረቅ የሸተተዉ፣
    እበጎቹ መሃል ገብቶ ለጥ።
    “አንተ ባለታክሲ የምትገሰግሰዉ፣
    እስቲ አቁምልኝ እኔ ግን አልሄድም። ከእነዚህ መሳይ ሰንጎ መገን ግጥሞች መካከል አስቂኝና ለማስታወስ ቀላል ሆኖ የሚታየዉ ጅራቷ ፍጥጥ የሚለዉ የሚዳቋዋ ግጥም ነዉ። ስእላዊ ድርሰት ሆኖ ነበር የታየኝ መለስ ዜናዊ አይኑን አፍጥጦ በድንጋጤ ተዉጦ ሳየዉ።
    አቤ! አንተ እንደ አበበ ገላዉ ድፍረት ባይኖርህም የፕላስቲክ ፊኛ እንደዛ ባለ ስብሰባ መካከል ብታፈነዳ መለስ ዜናዊ በድንጋጤ የልብ ትርታዉ ሊቆም ይችል እኮ ነበር። ወይም አቶ ገብረ መድህን አርአያ “ታጋዮች የሽሬን ባንክ ለመዝረፍ ተኩስ ሲከፍቱ መለስ ዜናዊ ዎኪ ቶኪዉን ይዞ ፈረጠጠ” እንዳሉት ምናልባት በፍርሀትም ሆነ በመደንበር ከስብባዉ ፈርጥጦ ሊወጣ ይችል ነበር እኮ። ያ ቢሆን ኖሮ ሌላ ጉድ ይወራ ነበር። ሙያዬ ምስክርም ምንኛ ደስ ይላት ነበር። ሙያዬ እኔ ከማደንቃቸዉ ሴት ታጋዮች አንዷ ናት። በፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ በጋዘጤኝነት ሙያ የምታበረክተዉ የትግል አስተዋጽኦ እጅግ ሊደነቅ የሚገባ ነዉ። እግዜር ብርታቱን ላንተ እና ለእርሷ ይስጣችሁ!!

  2. fitih says:

    Don’t you think ESAT is the exat opposite of ETV??? they are both extremest in opposit direction. Huletim maganenun tekinewutal …. we need a tru media that can tell us the truth 😦 ……. I hate ETV!!! i hate ESAT !!!!

Leave a comment