ሰፈሬ ሽሮሜዳ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አቅራቢያ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ግዜ በአጋንንት የተለከፉ ፀበልተኛ ወገኖች “ትለቃለህ አትለቅም” በሚለው አስገምጋሚ የአስጠማቂው ቁጣ ሁልግዜም መልሳቸው ከተረበሸ ድምፅ የሚፈልቅ “እለቃለሁ!” የሚል ሲቃ እንደነበር አይቻለሁ። ችግሩ ግን ብዙ ግዜ “እለቃለሁ” ካሉ በኋላም በነጋታው “አብሬያት አድጌ፣ አብሬው ከርሜ” ለማን ትቼው እለቃለሁ” ብለው ድጋሚ ያገረሻሉ። አሁንም አስጠማቂው “አንተ ክፉ መናጢ ትለቃለህ አትለቅም…!?” ሙግታቸውን ይጀምራሉ። መስቀል እና ፀበል ለአጋንቱ ፀር ናቸውና “እለቃለሁ እለቃለሁ…” እያለ ይለፈልፋል። ምሱን ተናግሮ ቀምሶ ጨርሶ እስኪለቅ ድረስ ግን “እለቃለሁ” ስላለ ብቻ አይታመንም!
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዘንድሮም “እለቃለሁ!” እያሉ ነው። በእርሳቸው ፍቅር የተለከፍን እኛ፤ “ያለ እርስዎ በሳል አመራር ችግር እና ጉስቁልና ያበስለናልና እባክዎ ይሄንን አሳብ ወደ አዕምሮዎ አያምጡት!” ብለን ብንመክርም፤ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አያስጎምጁን!” እያሏቸው ይገኛሉ።
በተደጋጋሚ እንዳየነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አስለፍላፊያቸው ብዙ ነው። ከዚህ በፊት በፓርላማ ውስጥ፤ ከዛም በተለያዩ የውጪ ሃገር ጋዜጠኞች “ትለቃለህ አትለቅም!” የሚሉ አስለፍላፊዎች አጋጥመዋቸዋል። ያው የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትራችንም ደንብ ነውና፣ ስርአቱ ነውና “እለቃለሁ!” እያሉ በተደጋጋሚ ለፍልፈዋል። ነገር ግን አለቀቁም።
እኔ የምለው ግን ክቡርነታቸው በርካታ ግዜ “ለቃለሁ” እያሉ ሲተዉት፣ “ለቃለሁ” ሲሉ ሲተዉት ሰዉ ንግግራቸውን አጓጉል ከእርኩስ መንፈስ ጋር እያዛመደባቸው እኮ ነው…!
በነገራችን ላይ ከላይ ያለውን የኪዳነምህረት ፀበል ትዝታዬን ያመጣሁት እንደው ነገር ለማሳመር ብቻ ብዬ አይደለም። በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ የውጪ ሀገር ጋዜጠኛ “ትለቃለህ አትለቅም?” ብሎ ሲጠይቃቸው “እለቃለሁ!” ብለው በመናገራቸው (“እለቃለሁ” ብለው ሲለፈልፉ…” ልላቸው ነበር! ይቅርታ ከላይም “ለፈለፉ” የሚል ቃል ካለ ከፀበልተኞቹ ጋር ተምታተውብኝ ነውና በጅምላው ይቅርታ ጠይቄ እቀጥላለሁ)
እና ታድያ ጋዜጠኛው በጠየቃቸው ጊዜ “እለቃለሁ!” ብለው ሲመልሱ አንዱ ወዳጄ “አፈር ስሆን ‘ምስህ’ ምንድነው? በለህ ጠይቃቸው እና ያሉትን አቅርበን ቀምሰው በደንብ ይልቀቁን ሁሌ “ለቀኩ እያሉ አያስጎምጁን!” ብሎ የተናገረውን አስታውሼ ነው።
እኔ የምለው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን መልቀቅ ከአጋንንት መልቀቅ ጋር ማመሳሰል ፍትሃዊ ንፅፅር ነው ትላላችሁ…!?
በጣም ፍትህዊ ነው አቢ ምሱ የሚሰጠው ግን እንደሚመስለኝ ከ ለቀቀ በሁአላ እንዳይመለስ ነው እንደ ፑቲን እና እሱ ይልቀቅ እንጂ ለምሱ እናዋጣለን በሁአላ….
አቤ ቶሎ ካለቀቀማ ምሱ የሚሆነው የጋዳፊ እጣ ነወ :: እኔ ግን እግዚአብሄር ልብ ሰጥቶት በክብር ስልጣን በህዝብ ለሚመረጥ መንግስት እንዲያስረክብ ነው:: ምኞቴ
በእኔም ሠፈር ያለው የየካው ሚካኤል ዋዛ እንዳይመስላችሁ !
” አስለቃቂና ለቃቂ ሙግታቸውን ይጀምራሉ። መስቀል እና ፀበል ለአጋንቱ ፀር ናቸውና “እለቃለሁ እለቃለሁ…” ይላል ገና ሳይጀመር እንዲሁ የሚያቃዣቸው ጠ/ሚኒስትር ” የጥምቀት ዕለት አንድ ሕዘብ አንድ ሃይማኖት ሲሉ ሰማሁ ብለው በፓርላማ (በውሸት ማማ) ሲቃ እየተናነቃቸው ሲያጓሩ(ሲለፍፉ) ነበር። “ሲያጓሩ” የሚለውን ‘ሲለፈለፉ’ የሚለውን የቀደሞ ሥርዓት ርዝራዦች፣አሸባሪዎች፤ሟርተኞች የይለቃል ሙሾ እንደወረደ ላለመጠቀም ሳንሱር ተደርጎ ነው። ይቅርታ…..
ለግምገማ ያህል………….
እስቲ አማካሪዎቻቸው “የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መሪያችን ቆራጥ አመራር እና ውሳኔ በፍቃደኝነት ለቀው ሊሄዱ ስለሆነ በአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝታችሁ አለቃቀቃቸውን አዳምቁልን” ተብሎ ቅስቀሳ ቢደረግ ያላቸውን ደጋፊና አይልቀቅ ብለው ሰይጣን እንዲሰፍርባቸው የሚመኙላቸውን ደጋፊ በታዘብነው ጥሩ ነበር። ደጋፊዎቻቸው መቼም መደገፊያ የሌላቸው አሳዛኝ ናቸው እባካችሁ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ !!
የእሳቸው ሥንብት በዚህ ፎቶው ላይ በሚታየው መልክ ከሆነ እልል በቅምጤ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን መልቀቅ ከአጋንንት መልቀቅ ጋር ማመሳሰል ፍትሃዊ ንፅፅር ነው ትላላችሁ…!?
( ፩) እንዴታ….! ከዚህ በላይ ሰይጣን ከየት ይምጣ ብላችሁ ?
( ፪) እሳቸውም እያነፃፀሩ አደለም እንዴ ሕዝብ የሚፈጁት(….)?
ሀ) ሕዝብ ተራበ ? የሕዝብ ቁጥር ከደርግ ዘመን በጥፍ ስለጨመረ ነው ። የዕድገታችን መገለጫ ነው።
ለ) ኑሮ ተወደደብን ? አሜሪካም ኑሮ ተወዷል። ሴፍቲ ኔት አላዘጋጀንም… በሰፊ ኔት ልንጨምራችሁ አስበናል።
ሐ) ህዘቡ መብራት የለውም ? ኬንያ፣ ጅቡቲ፤ ሱዳን፤ የልማታችን ተጠቃሚ ሆነዋል። መ)የትምህርቱ ጥራት ያሰጋል ?ትምህርት ቤቶችን ለሁሉም ክልል ለማዳረስ ቆርጠናል። ምን ?(ደሞዝ) ጀምረናል፣ ሠ) በሀገሪቱ የጤና ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው መድሀኒት የለም?ብዙ ኢነቨስተሮች ይመጣሉ አውሮፓም ዕጥረት አለ። ረ)በከተማ ውሃ የለም፤ ጥራቱም አስተማማኝ አደለም፤ ? ሕብረተሰቡ ቁጠባን ‘ከግመል’ መልመድ አለበት። ሰ)ሕዘቡ የነጻ ሚዲያ ያስፈልገዋል ? አዲስ ዘመን መግዛት አቅም የሌላቸው ተከራይተው ማንበብ ይችላሉ። ሸ) የፖለቲካው ምሕዳር ጠቧል ? በትግራይ መስተዳደር ክልል እና በአማራ ክልል ዘመናዊ እስታዲየም ሊገነባ ነው። ቀ) ወጣቱ የአጓጉል ባህል ተጠቃሚ ሆነ ? እኔም እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አላሰበኩም፤ተተኪው ትውልድ ቻይና ሰልጥኗል። በ) በሀገሪቱ ምርጫ በደንቡ አይደረግም ? ምርጫ ይደረጋል እንጂ ኢህአዴግ ከሥልጣን ይለቃል አይልም ። ተ) የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ? ዓለም በቃኝን ያፈረስነው የቁም እስርን በመገንባታችን ነው ስሙን ቀይሮ ይገነባል። ቸ) በፖለቲካ አለመመቸት ሕዝቡ ተሰደደ? ኢንቨስተር ለመሆን አስበው ይሆናል ፩ ለ ፭ ይደራጁ ገንዘብ እንሰጣለን። ነ) ኢኮኖሚው አልተረጋጋም ? የአካባቢ ሀገሮች ሰላም ለእኛም ሰላም ዋስትና አለው ብቻችንን መብላት አንችልም። ኘ)ሀገሪቱ የራሷን ወደብ ባትለቅ ኖሮ ቢያነስ ፴፫ %በወጪዋ ላይ ይቀነስ(ይደጉም)ነበር?ወደብ ለመግዛት እናፈላልጋለን። አ) አባይን መድፈር ይቻላል? ዶሮን ሲደልሏት እነጂ… እንኳን እኔን ግንድ ካገላበጠ ሞኞች ይሞከሩና ይጥሩኝ። ከ)ዲያስፖራው በፖለቲካ ይሳተፋል ? ጠርተናቸው አናውቅም ስማችንን ሲጠሩት ሰምተናል በጩኸት ይረዱናል። ኸ)የመንግስትን በሐይማኖት ጣልቃ መግባትን ህገመንግስቱ ይከለክላል? ከዳር ቆማችሁ አታበጣብጡ የሚል አልተፃፈም ። ወ)ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የምንሰለፈው መቼ ነው?ጂ-8 ጂ-20 ስብሰባ ሄደን ብፌ ማንሳታችንን በቲቪ ሲለፈፍ። ዐ) ሀገሪቱ ፲፩% አደገች የሚባለው እንዴት ነው?የፓርቲ አባላቶቻችን ነግደው ያተረፉበት ገንዘብ ይቆጠር እና ይመለሳል።
ዘ)ኪራይ ሰብሳቢ ማለት? እራሱን በሕቡ ያደራጀ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ውጭ በልዩ ሕግ እና ደንብ የሚመራ። ዠ)ሙስና በደርግ የመጠሪያ ስሙ(ጉቦ) ልዩነት አለው?ሙስና ከአንድ ሚሊየን ብር በታች የሆነ ገንዘብን አያጠቃልልም።
ፐ)ደብል ድጅት የት ነው የሚጨምረው?ዘጠኝ ዓመት ደብል ድጅት ከጨመረ … አሁን ማነጻፀር ሳይሆን……..ነው። እኔም እዚህ ደከም አለኝ ለማነፃፀር ይረዳኝ ዘንድ የሰንበት ቡናዬን በደብል ቀጅቼ የሕዘቡን ውሎ አዳር ልገምግም።
ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ የተበተኑ ልጆቿን ትሰበስባለች !!!!!
በቸር ይግጠመን ከሀገረ ካናዳ>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>
Abe,you makes me nerves how come you say that?do you understand what is gona happen with out Melese in our country another Agannte (evil mind)will appear and diss troy Ethiopia how can we exist O my God.behave please.Thank you.
በአጋንንት የተለከፉትን ሰዎች ከያዛቸዉ አጋንንት ለማስለቀቅ ጸበል በመርጨት የታወቁት አባ ወልደ ትንሳኤ የሚባሉ ቄስ በወሊሶ ጸበል ይሰሩ እንደነበር አዉቃለሁ። አሁን ግን በህይወት ይኑሩ አይኑሩ አላዉቅም። የሳቸዉን ያህን የሚያክል ቄስ አለ የሚል ሰምቼ አላዉቅም አጋንንትን በማስለቀቅ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይረዱት ነዉ እንጂ አጋንንት የያዛቸዉ ብቻ ሳይሆን ሰይጣንም እንደ ፈረስ አድርጓችዉ ማታ ማታ ሳይጋልብባቸዉ አይቀርም ብዬ እገምታለሁ። እንደዛ ላሉ ሰዎች ነዉ አባ ወልደ ትንሳኤ ፍቱን መድሀኒት በመሆን የታወቁት። በእዉነቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛር ወይም አዶ ከብሬ ይኑርባቸዉ አይኑርባቸዉ የማዉቀዉ ነገር የለም። ምናልባት አዶ ከብሬዉ ወይንም ዛሩ ይሆን “እለቃለሁ” እያለ አእምሮአቸዉን የሚያስጨንቀዉ? ታምራት ገለታ እንደሆነ እስር ቤት ገብቷል የሆነ ፍንጭ እንኳ እንዳይሰጠን። የቱን ጠንቋይ መጠየቅ እንደሚሻል እንኳን አላዉቅም። የመላ ምት ፍልስፍና ማድረጉ ይበጅ ይሆን እንዴ ጉዳዩን በሳይንሳዊ ምርመራና መረጃ አስረግጦ ይሄ ነዉ ብሎ ለመናገር?