ዛሬ ሰንበት ነው። እንዴት አደራችሁ!  ነገ ጠዋት በሰፊው እስክንገናኝ  ለሰንበት ታኽል ግን የሆነች ነገር መሰንዘር ግድ ይላል ብዬ አሰብኩ። አስቤስ …? ትላንት የበሀይሉ ገ/ኢግዚአብሔር አዲስ መፅሐፍ “ኑሮ እና ፖለቲካ” እጄ ገባ። እንዴት እንዴት አይነት ጨዋታዎችን ይዟል መሰለችሁ!? በእውነቱ  ዛሬ በማውጊያችን አንድ ለሰንበት ጣል ባደርግ ደስ እንደሚላችሁ ርግጠኛ ሆንኩ… ሆኜም እነሆ አልኩ፤

የቢል ነገር

እንደ ትናንት ምሳ የተመገብንበት ቤት እንደ ዛሬ ሁደን ምሳ አዘዝን ይህቺ ምግብ ቤት ከሌሎች ምግብ ቤቶች አንፃር ዋጋዋ ደህና ናት ተብሎ በኛ ዘንድ ሞገስ ያገኘች ቤት ነበረች።

ከአቅም አንፃር ደግሞ በጣም ደህና እንዲሆንልን አምስት ስድስት ሆነን በማኅበር አዝዘን እንመገብ ነበር። ምግቡ መጣ፤ ከጥሩ የምሳ ጨዋታ ጋር ተበላ፤ በጥርስ እንጨት ጥርሳችንን እየጎረጎርን ሂሳብ እንዲቀበለን አስተናጋጃችንን ጠራን። እስኪመጣም ዐይናችንን ወደ ተከፈተው ቴሌቪዥን ሰደድን።

“የቢን ላደን ሞት አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው!” ይላል ዘገባው። ለበላነው ምግብ ማወራረጃ ይሆን ዘንድ የኛም የውይይት ርዕስ ቢን ላደን ሆነ።፡

“ለመሆኑ ቢን ላደን የሚባል ሰው በህይወት ነበረ?”

“እንዴ ምን ነካህ አለ እንጂ!”

“እውነት ግን ለምን ሬሳውን አያሳዩንም?”

“ያልነበረ ሰው መቼም ሞተ ተብሎ አይነገርም!”

“ቢን ላደን ለኦባማ ስልጣን ማራዘሚያ ጠቀመው!”

አስተናጋጁ ከቆይታ በኋላ እንደ መፅሐፍ ተገላጭ የሂሳብ መቀበያ ውስጥ ቢል ሸጉጦ ሰጠን፤ ቢሉ ቢነበብ ትላንት በበላነው በእያንዳንዱ ምግብ ላይ በትንሹ ስድስት ብር ተጨምሯል።፡

“ምንድነው ይሄ?” ቢሉን እያየ ያለ ወዳጃችን ፊቱን አኮሳትሮ ጠየቀ። በእንዲህ አይነት ጥያቄ የተሰላቸው አስተናጋጅ ፊቱን አዙሮ የዋጋ ዝርዝር የተፃፈበትን ነጭ ሰሌዳ አሳየን። የዋጋ ጭማሪው እውነት ነው። 34 ብር የነበረው የበግ ጥብስ 40 ብር ብሎ ይጀምራል ዝርዝሩ።

“ለምንድነው በአንድ ቀን ይሄ ሁሉ ጭማሪ!?”

“ቢል መቁረጥ ዛሬ ስለጀመርን!” በታከተ ድምፅ አስተናጋጁ መለሰ።

“ቢል ከምትሉ ቢላ ብትሉ አይሻልም!?” በምሬት ሌላው ወዳጃችን።

ሻዩ፣ ማኪያቶው፣ ሽሮው፣ ቀይ ወጡ… /ሆድ ስለባሰኝ በዚሁ ልቀጥልበት፤- ትራንስፖርቱ፣ ስኳሩ፣ ወይ ዘይት፤ ዘይት የቅቤ ረዳት ተዋናይ ተደርጎ መጠራት ከጀመረ ጀምሮ ዋጋው የማይቀመስ ብቻ ሳይሆን በፈለጉት ዋጋ ታስሶ የማይገኝ ሆኗል። “ሸኖ ቅቤ፤ ሸኖ ለጋ፤ ሻዲ ለጋ…” ያኔ ሲሉት መጠርጠር ነበረብን። … ነዳጁ፣ ሰዉ፣ ስጋው፣ ግብረ ስጋው… አዬዬ ምን ይሻላል?/ ሁሉ ነገር በየቀኑ ይጨምራል። “የዚህ የኑሮ ውድነት ጦስ መጨረሻው ምን ይሆን?” ስጋት ባጀበው ዝግ ባለ ድምፅ ራሴን ጠየቅኩ።

“ወይ ጉድ” አለ አንዱ ወዳጃችን በመሃል አንዳች የታወሰው ነገር ያለ በሚመስል።

“ምን ሆንክ?”

“ቢል ላደን መቼ ሞተ?”

“እንዴት?”

“በህይወት አለ እኮ፤ ያውም እዚችው እኛው ምድር!”

“ምን ማለት ነው?”

“ቢል ላደን መጥቶ ይኸው እኛን እየጨረሰን እኮ ነው።” አለ ንግግሩን ይበልጥ እያሻሻለ። የጓደኛችን ንግግር ሁላችንም የገባን ዘግይቶ ነው።፡ነገሩ ቅኔ መሆኑ ነው፤ ቢል ላደን። እውነትም ቢል ለአደን።

“እንገዛ ነበር እቃ በጥሩ ዋጋ፤

ቢል ላደን መጣና ኑሯችን ተናጋ።” ብንለውስ?

በሀይሌን እናመሰግናለን ብዕርህ ትባረክ ብለንም እንመርቃለን። መልካም ሰንበት ይሁንልዎ ወዳጄ!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

One response »

  1. በለው! says:

    አዎን በሀይሉን እናመሰግናለን! በመተማመን በፍቅር ግብይይቱ ይጧጧፍ ነበር ድሮ የዛሬን አያድርገውና ፣ዛሬማ ሁሉ ጠፋ ተወደደ “ይገዛ የነበር ዕቃ በጥሩ ዋጋ፤ ቢል(bill) ለአደን(for hunt) መጣና ኑሮአችን ተናጋ፤ ለበላነው ብቻ ሳይሆን ለምንስበው አየር ሂሳብ ከመጠየቅ ያድነን ክፉን ያስተንፍስልን እኛም ከሥጋት እንዳን! ገበያ ለመሄድ የተነሳቸሁ የሸኖ ቅቤ የለመደ ቅልጥማችሁ ምነው ሸኑ ከላያችሁ?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s