አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረው እያልን ማውራት ከጀመርን ሰማንያ ቀን በቅርቡ እንደሚሞላው አንድ ወዳጃችን በለጠፈው ማስታወሻ አስታውሶናል። እንደውም ዛሬ ሳይሆን አይቀርም… የሆነ ሆኖ ከዚህ ቀጥሎ ጋሽ ስብሀት ፅፎት በሳቅ ፍርስ ካደረገኝ ጨዋታ መካከል የሚከተለውን እንድናወጋ ወደድኩ… እንደሚከተለው አስታውሳለሁ!
በቀድሞ ግዜ ከነበሩ “ዋና ሰዎች” መካከል አሉ የሚባሉ አንድ ባለስልጠን ቀኛዝማች ይሁኑ ግራ አዝማች ወይም ፊታውራሪ ረስቼዋለሁ… ዘመቻ ሄደው ሲመጡ ታሪኩ ይጀምራል።
ዘመቻው ሁለት አመት የፈጀ ነበር። እናም ባለታሪካችን ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ ነው የሚመለሱት። መጀመሪያ የተቀበላቸው ታድያ ማነው…? ገብሬ። ገብሬ ማነው…? ገብሬማ የባለታሪካችን ዋና አገልጋይ ነው። ገብሬ እቃቸውን ተሸክሞ ከፊት ከፊት እየሄደ፤ መንገድ ላይ ጨዋታ ተጀመረ…
“እሺ ገብሬ ሀገሩ ሰላም ነው…?”
“ሰላም ነው ጌታዬ… ሁሉ ሰላም ነው… ብቻ…” አለ ገብሬ የጌታውን እቃ ተሸክሞ ከፊት ከፊት ኩስ ኩስ እያለ።
“ብቻ ምን…? አንተ የተፈጠረ ችግር አለ እንዴ?”
“የለም ጋሼ ብዙ አይደንግጡ… ብቻ መቻል መሞቱን ልነግርዎ ነው” አላቸው። መቻል ማነው…? ያላችሁ እንደሁ መቻልማ ባለታሪካችን አብዝተው የሚወዱት ውሻ ነበር።
“ውይ አፈር ስሆን… መቻል ሞተ…!?”
“አዎ ጌታዬ…! ሞተ…! ምፅ…” ኩስኩስታውን ገብሬ ቀጥሏል።
“ምን ሆኖ ሞተ በል…?” አሉ ባለታሪካችን፤ እንኳንም ሌላ መርዶ አልነገርከኝ በሚል ዜማ!
“አዬ… ጌታዬ ጉራች ታረደና የርሱን አጥንት ሲበላ ከጉሮሮው ላይ ስንቅር ብሎ አይሞቱ አሟሟት ሞተ…” ገብሬ በሱ ቤት ማሰተዛዘኑ ነው ለካስ ጉራች ደግሞ በጣም የሚወዱት በሬ ነበርና ጭራሽ ክው ብለው፤
“አንተ… ጉራች ለምን ታረደ በል…?” ብለው በቊጣ ጠየቁት።
“እሱማ… ለእሜቴ ተስካር ነው ጌታዬ…!” አለ ገብሬ። እሜቴ እኮ ባለቤታቸው ናቸው!
ከቀደመው የእጥፍ እጥፍ ከዛም በላይ ሌላ እጥፍ ክውታ፤ ክው አሉ ባለታሪካችን! ጠላትዎ ክው ይበልና! ይሄኔ ገብሬም ኩስ ኩስ ማለቱን ትንሽ ገታ አደረገ።
“አንተ ምንድነው የምታወራው…? እሜቴ ሞተች ነው የምትለኝ…?”
“ምፅ… አዎ ጌታዬ እሜቴ ሞቱ እኮ!”
“የጉድ ሀገር…! ምን ሆና ሞተች መሆኑን?”
“አይ ጌታዬ… በወሊድ ነው!” (ልብ አድርጉልን ባለታሪካችን ከሁለት አመት በኋላ ወደ ቀያቸው መምጣታቸው ነው…)
“እንዴ… አንተ ሰውዬ ዛሬ ታመሃል እንዴ…? ከማን አረገዘችው…? እስቲ ንገረኝ…?” አሉ በቁጣ ተገስለው።
ይሄኔ ገብሬ ጣጣ አለው እንዴ…! ቀልጠፍ ብሎ መለሰ።
“እንጃ ጌታዬ ሰዉ ከገብሬ ነው ይላል እኔ ደግሞ ከኔ አይደለም እላለሁ!” ብሏቸው እርፍ።
በአግባቡ ተርኬው ይሆን? ብቻ ጋሽ ስብሀት ለመዘከር ያህል ነውና ልክ አንብው ሲጨርሱ “ጋሽ ስብሀት ነፍስህን ይማረው!” በማለት ተባበሩኝ! አመሰግናለሁ።
ማስታወሻ… ሽመልስ ሲሳይ የተባለ ወዳጃችን በነገረን ማብራሪያ መሰረት ጥቂት ማስተካከያ ተደርጓል ምስጋና ይገባዋል!
abe kkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk