ዛሬ ለቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን አንድ መልዕክት ለመስደድ አስቤያለሁ። እስከ ዛሬ ድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን የተለያዩ መልዕክቶችን ስንልክላቸው ነበር። እርሳቸው ግን አይተው እንዳላየ፣ ሰምተው እንዳልሰማ ዝም ብለውናል። በርግጥ መልዕክቶቻችንን እንደሚያነቡ ባለፈው ግዜ ጠቁመውናል። “እያንዳንዳችሁ በየጋዜጣው የምትፅፉትን እናያለን የጋዜጠኝነት ሀሁ ያልገባችሁ ጋጥ ወጦች ናችሁ” ብለው እስከ ዶቃ ማሰሪያችን በተናገሩበት “ዲስኩር” ቢያንስ መልዕክቶቻችንን እያዩ እንደሆነ ተረድተናል። እኛም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያነቡን ባወቅን ግዜ ደስ አለን” ብለን ጮቤ ረግጠናል።

ቢሆንም ግን አንድም ቀን እንኳ “እንዲህ ይባላል፤ “እንዲህ አድርገን እናሻሽላለን። እንዲህም ተብለናል፤ እንግዲህ ካልፈለጋችሁ ምን እናደርጋለን … እንለቃለና…” ብለው ምላሽ ለመስጠት አልሞከሩም። (እኛ እንደሳቸው “አህያ ትልቅ ጆሮ አላት ግን በቅጡ አትሰማም ትላልቅ አይንም አላት ግን ያለመነፅር ማየት ይቸግራታል…” ብለን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ከእንስሳ ጋር አናዛምድም። እናስ… እናማ… በቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገር እየጠየቅናቸው “ጆሮ ዳባ” አሉን። ብለን እናልፈዋለን…

ታድያ ምን ይጠበስ…? ያሉኝ እንደሆነ፤ ምን ይጠበስ መሰልዎ… ጉዳያችንን ይዘን ሄደን ለባለቤታቸው እንነግራለን። እናም ውጤቱን እንከታተላለን። ይሄ እስከ አሁን ያልተሞከረ ጥሩ መላ አይመስልዎትም?

ከዛ በፊት ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ ጨዋታ አለኝ እንደሚከተለው ይቀርባል…

ባል እና ሚስት ከተጋቡ በኋላ የባል እናት ቤት አብረው ይኖሩ ነበር አሉ። ሲኖሩ ሲኖሩ ከዕለታት አንድ ቀን ሚስት እና የባል እናት ይጣላሉ። ጭቅጭቃቸውም በበረታ ግዜ እናት ሆዬ “እኔ ከአንቺ ጋር ምን አነዛነዘኝ… አንቺንም እኔንም የሚያስተዳድረን ልጄ ነው። እርሱ ሲመጣ ሁሉንም ዘክዝኬ እነግረዋለሁ…!” በማለት “ሀርድ ይሰጣሉ። ታድያ ሚስት  ምን አለች መሰልዎ… “ንገሪው… አንቺ አጠገብሽ ቁጭ አድርገሽ ከምትነግሪው እና እኔ አንገቱ ስር ገብቼ ከምነግረው የማንን እንደሚሰማ እናያለን?” አለች አሉ።

እንግዲህ ይህ ህዝብ እናት የሆነ ህዝብ ነው። ግና አጠገብ ቁጭ አድርጎ ቢመክርም የሚሰማው አላገኘም። ስለዚህ በተሻለ ሁኔታ የሚመክር ካገኘን እንሞክር…

እባክዎ ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎን ይምከሯቸው… እንበል።

ወዳጄ… እንዴት ሰንብተውልኛል? ሰላምም ሳልልዎ ቀጥታ ወሬዬን ጀመርኩ አይደል? ይቅርታ ይደረግልኝ ለመሆኑ ጤና እንዴት ይዝዎታል…? አይዞት በርታ ይበሉ። “ዋናው ነገር ጤና” እንዳለው ዘፋኝ ጤና እና እድሜ ካለ ሌላው ትርፍ ነውና ጤናውን ከእድሜ ጋር እንዲያጎናፅፍዎ ምኞቴን እገልፃለሁ።

እኔ የምለው “የአዲሳባ ኑሮ አሁንም አልተቻለም!” የሚል ወሬ ሰማሁ። ለምሳሌ “ባለ ብሩ ዳቦ” ሙዚየም ውስጥ ካልሆነ የመገኘት እድሉ የመነመነ ሆኗል (አሉ) አሁን አሁን አዲሳባ ላይ “ባለ አንድ ብሩን ዳቦ ስጠኝ” ብለው ቢጠይቁ ዳቦ ቤቱ ውስጥ ያለው ነጋዴ ብቻ ሳይሆን አንድ ብርዎት ላይ የተሳለው ልጅ ራሱ “አልሰሜን ግባ በሎ” ብሎ ከወትሮው በተለየ መልኩ ይስቅብዎታል እየተባለ ነው። ታድያ አሉ ነው። ምን ይደረግ ከሀገር ርቄ የአሉ ወሬ ሰለባ ሆኜ የለ? (“እሱ እንኳን ተው ድሮም አሉ ትወዳለህ…” ብሎ ማሽሟጠጥ የተከለከለ ነው።)

ይልቅስ ከላይ ሙዚየም ስል ያቺ ሉሲ ትዝ አለችኝ። እሷ ሴትዬ በቃ እንደወጣች ቀረች እንዴ…? የከተማው ሰው “ዲቪ ደርሷት ነው” እያለ ሲቧልት ሰምተን ነበር። በርግጥ የመንግስት ሰዎች  “ለጉብኝት ነው ትመለሳለች” ብለው ለማስተባበል ሞክረዋል። ይህው እርሷ ግን በዛው ጥገኝነት ጠይቃ ይሁን፣ ድሮውን አካሄዷ ለዘለቄታው ይሁን? ባልተለየ ሁኔታ እስከ ዛሬ ከአሜሪካ አልተመለሰችም። አረ ጎበዝ “ሼም” ነው።

ነገ ይህንን ልብ ያለ አንድ ጋዜጠኛ “ሀገሪቱ ህያው ብቻ ሳይሆን ሙታንም የሚሰደዱባት ሀገር ሆነች!” የሚል ዘገባ ቢሰራብን እንደተለመደው “መልካም ገፅታችንን ለማጥፋት ላይ ታች የሚሉ አካላት…” ብለን ለመልስ ምት መከራችንን ከምናይ ከአሁኑ መላ ቢበጅላት መልካም አይደለም? የምሬን ነው፤ የሉሲ ነገርማ በጣም አሳሳቢ ነው። ወይ ደግሞ ሰዎቹ “እሟ ቀሊጦ” ብለውን ከሆነም የአክሱምን ሀውልትን ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ አይነት ለእርሷም ይቋቋም። እንጂ በውነቱ ይሄ ነገር ለሰሚም መልካም አይደለም።

ውይ ይቅርታ ቀዳማዊ እመቤት አቆምኩዎ አይደል…? አሁን ወደ እርስዎ ተመልሻለሁ። እባክዎ ባለቤትዎን ይምከሯቸው ብዬ ጀምሬም አልነበር…? እንቀጥል

ችግሩ ምን መሰልዎ… “ያው እንደሚያውቁት…” ብዬ ልልዎት ነበር ለካስ እርስዎ ምን ችግር እንዳለብን ምን አበሳ በላያችን ላይ እንደተጫነ አያውቁምና…

ይህውልዎ ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎ ዜጎቻቸውን እያማረሩ ይገኛሉ። እንዲገጥም እያባረሩ የሚልም እንጨምርበት። እውነቴን ነው የምልዎ… እኔ የእርስዎም፤ የባለቤትዎም፣ የእናት ድርጅትዎም ወዳጅ ነኝ… ማንም ያላወቀልኝ ወዳጅ። ነገር ግን ሀገሬው የሚያወራውን እሰማለሁ ሰምቼም እናገራለሁ። ስለዚህ ንግግሬን ከክፋት አይዩብኝ ለራሳችን ብዬ ነው…

ባለቤትዎ በትዳርዎ ላይ ያላቸው አስተዳደር የተሳካ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ። በሀገር ማሰተዳደር ላይ ግን “ከማስተዳደር ይልቅ ማደናገር ነው የያዙት” እያለ የማያማቸው ኢትዮጵያዊ የለም። በሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ በየ ቡና ረከቦቱ እና በየመጠጥ ባንኮኒው፤ በውጪ ያለው ደግሞ በየ አደባባዩ እና በየ ኢንተርኔት መስኮቱ… ባጠቃላይ ባለቤትዎን ሁሉም ያብጠለጥላቸዋል። እኔማ ይሄንን ሳይ ውይ… ወደዛ “በቃኝ” ባሉ እና በተገላገሉ እያልኩ ሁሌ ነው የምመኘው።

አንድ ግዜ እርስዎ በአንድ ቴሌቪዥን ጣብያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እኔ ገንዘብ ብፈልግ መለስን ከዛ ስራ ነው የማስለቅቀው…” ሲሉ ተናግረዋል። ታድያልዎ ይንን ንግግርዎን በቅርቡ ድጋሚ አዳምጬው ነበር። እና በሀሳቤ ቀዳማዊት እመቤታችን ገንዘብ በፈለጉ… ስል አጥብቄ ተመኝቻለሁ። ለምን እንደሆነ መቼም ይገባዎታል…

እኔ የምልዎት ግን በዛ ቴሌቪዥን ላይ “በአለም የመጨረሻዎቹ ደሀ መሪዎች እኛ ነን” ሲሉ የሰማሁት ነገር ጆሮዬ ነው… ወይስ እውነት እንደዛ ብለው ተናግረዋል? ምን ነካዎ… ቢያንስ ቢያንስ ለመልካም ገፅታችን ሲሉ እንኳ እነ ኢፈርትን፣ እነ ጉናን፣ እነ መስፍን ኢንጂነሪንግን፣ እነ መሰቦን፣ እነ ወጋገንን፣ እነ ወዘተን ጠቅሰው “መካከለኛ ገቢ ካላቸው መሪዎች መካከል ነን” ቢሉ ምን ነበረበት? ለምን ህዝቡስ ሰጥቶ እንዳልሰጠ ይቆጠራል? እኛ በዚህ በኩል መልካም ገፅታን ለመገንባት መከራችንን ስናይ እርስዎ ደግሞ በዚህ በኩል ሲያፈርሱ ጥሩ ነው…? (ለነገሩ ይሄ እርስዎን ሳስመክርዎ ለመካሪዎ የምነግረው ይሆናል)

ለአሁኑ ግን እባክዎን ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎን ይምከሩዋቸው…

ዋና የጨነቀኝ ነገር ምን መሰልዎ… ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየደረሰባቸው ያለው ተቃውሞ በየግዜው እየበረታ፤ እየበረታ የመምጣቱ ነገር ነው። እንደኔ ግምት ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳንስ ህዝቡ እና የገበታ እንጀራቸው ራሱ በፈቃደኝነት የሚጠቀለልላቸው አይመስለኝም።

ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ከብዙዎቹ መካከል የኑሮ ውድነቱ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ እየጨመረ ቁርስ እና ምሳ ለመብላት እንኳ ድርጅቶች ስፖንሰር ካላደረጉ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ ነው። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ “የዕድገት መገለጫ ነው” የሚል ነው። ይታይዎት ርሃብ የዕድገት መገለጫ ሲሆን… ህዝቡ በዚህ ጉዳይ በየጓዳው እያጉረመረመ ለመሆኑ መረጃ አለኝ። በርግጥ ማስረጃ የለኝም… (በቅንፍ የመረጃ እና የማስረጃን ልዩነትና አንድነት ለመረዳት ባለቤትዎን ይጠይቁ)

እንግዲህ እርስዎም ያስቡት ይህ ማጉረምረም እየጠነከረ ሲሄድ ሊፈጠር የሚችለውን ይገምቱ…

ቀዳማዊት ሆይ፤ እውነቱን ልንገርዎ… እኔ እያቃዠኝ ነው…! ህዝቡ ብሶት በማቆር ላይ ነው። ብሶት ምን እንደሚያደርግ ለርስዎም ለርሳቸውም ለመንገር አይቃጣኝም። ስለዚህ እባክዎን ይምከሯቸው።

“ህዝቡ ይወደኛል” ብሎ መዘናጋት ለጋዳፊም አልበጀም። ለማንኛውም ተዘገጃጅቶ መጠባበቅ ይሻላል። ውይ ምን ነካኝ የምን መጠባበቅ አመጣሁኝ? መጠባበቅ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ለመጣበቅ ይዳርጋል እንጂ ዋጋ የለውም። ግድየልዎትም ዝም ብለው “በቃኝ” እንዲሉ ቢያደርጉ ነው የሚሻለው። ምን አስጨነቅዎ “የመለስ ጭንቅላት ለልጆቼ ትምህርት፣ ለቤት መግዣ፣ ከዛም በላይ በሚሆን ገቢ ያመጣል ብለው የለ…? ይህንኑ ለርሳቸውም ይንገሩዋቸው። መንገር ከፈሩም “YouTube” ላይ ያገኙታል ይክፈቱላቸው።

ለነገሩ እንደሰማነው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በምድር ላይ የሚፈሩት ብቸኛ ሰው እርስዎ ነዎት። አንድ ግዜ አንድ ወዳጃችን በፃፈልን መጣጥፍ፤ ያኔ በበረሃ ዋሻ እያላችሁ እንኳ እንዴት እንዴት ያሽቆጥቁጡዋቸው እንደነበር ነግሮን አድንቀንዎታል። እንዲህ ነው እንጂ! እኔም ዛሬ ይሄንን ብቃትዎን ተማምኜ ነው ይምከሯቸው ማለቴ።

እኒያ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪውን ይበላል!” ብለው ተናግረዋል። እኔም ያስጨነቀኝ ይህው ነው። ጠቅላይ ሚንስትርዬን እወዳቸዋለሁ እርስዎንም እወድታለሁ እናት ድርጅታችንም ደስ ትለኛለች። ታድያ የሚበላውን ያጣ ህዝብ “ሆ” ብሎ እንዲበላችሁ አልመኝም። ስለዚህ ልክ ይሄ መልዕክት እንደደረስዎ ከባለቤትዎ ጋር ይማከሩ እና “በቃን” ይበሉ። እውነቴን ነው በቃችሁ! ምንም ባይፈጠር እንኳ ይሄን ሁሉ አመት እናተ ብቻችሁን እዳ አለባችሁ እንዴ? ስለዚህ “ይብቃችሁ”

ውድ ቀዳማዊ እመቤታችን፤ እንግዲህ ባለቤትዎ እኛ አጠገባቸው ሆነን ብንናገር ሊሰሙን አልቻሉም። እስቲ እርስዎ ደግሞ በሚስት ዘዴ ይምከሯቸው። አልመክርም ካሉ ለርስዎ ደግሞ ሌላ ዘዴ እናፈላልጋለን! እስከዛው ሰላም ይሁኑ!

በመጨረሻም

ማርች 8

ትላንት የሴቶች ቀን ሴቶች በሚገኙበት ሁሉ ተከብሮ ውሏል። እኔም ቀዳማዊት እመቤትን ጨምሮ ሴቶቻችንን በሙሉ እናኳን አደረሳችሁ እላለሁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ክብረ በዓል በዋናነት እንዲያሰናዳ ሃላፊነት የተሰጠው አንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አለ። ማን መሰላችሁ…? “የሴቶች የህፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር” መስሪያ ቤት ነበር። ይሄ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ሁሌ እንዳስገረመኝ ነው። እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነውና እንዴት…? ይበሉኝ

መስሪያ ቤቱ ሴቶችን ይዟል፣ ህፃናትን ይዟል እንዲሁም ወጣቶችን ይዟል። እዚህ ውስጥ የቀሩት ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። ታድያ እነርሱንም አካቶ ለምን “የሰዎች ጉዳይ ሚንስቴር” አይባልም? እያልኩ ሁሌ እገረማለሁ።

የሳምንት ሰው ይበለን!

አማን ያሰንብተን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

18 responses »

 1. Meron says:

  አቤ አመሰግንሃልሁ::

 2. Andinet says:

  as sweet as usual. I like it. keep it up. For those who are living outside Ethiopia your blog is making your work accessibility easier.

 3. rediet says:

  abe abe abe nefs neger neh……hahahaha i like this letter….nice one dear….

 4. rediet says:

  nice abe…….i like this letter……nice one berta

 5. ጆሮ ያለው ይስማ የሰማም ላልሰማው ያሰማ ነው ነገሩ, በዘመንኛው አነጋገር LIKE US OR FOLLOW US lol አቤ, ተስፋ አደርጋለሁ ክብርነቶ ሰምተው መልሕክቱን ያስተላልፋሉ

 6. selam says:

  ወይ አቤ!!!!!!! በስንት ጊዜየ ፈገግ አሰኘህኝ መሰለህ፡፡ ኧረ ዕድሜህን ያርዝምልን፡፡ ክፋ አይንካህ ወንድማችን፡፡ የጠላትህን ጉልበት ቄጤማ ያድርገው፣ አይኑን ይጋርድልህ …….. አሜን አትልም? በል በቃ ሌላውን ሌላ ጊዜ እመርቅሀለሁ፡፡ ባለህበት ሰላም ሁን፡፡

 7. tizita says:

  thank you so much abe for sharing your outstanding piece and i have no words to appreciate your skills and talents. Ethiopia requires you very much and may the almighty god bless you.

 8. Adyamseged says:

  አቤ ምን እልሀለሁ-እግዜር ይስጥልን! ጠላቶችህን አይናቸውን ጨለማ: ጉልበታቸውን ቄጠማ: አፋቸውን ለምለም ያድርግልህ!!!

 9. Jacob Seyoum says:

  thank you Abe, berta Berta.

 10. BEZU says:

  Ethiopia have many people like u.we need true thing not ” ALUBALTA “

 11. zewdu F. says:

  well done my men!!!

 12. rasdesta says:

  Abbe ! I am really sorry that you are not in Ethiopia. I am feeling it how much Ethiopians are missing u ….God bless u man

 13. Bam says:

  “ሀገሪቱ ህያው ብቻ ሳይሆን ሙታንም የሚሰደዱባት ሀገር ሆነች!” ……Like this!!!

 14. King says:

  Abeye bedenb negeren……ke mehaymenet awtan plzzz..plzzz

 15. delna says:

  እንደኔ ግምት ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳንስ ህዝቡ እና የገበታ እንጀራቸው ራሱ በፈቃደኝነት የሚጠቀለልላቸው አይመስለኝም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s