እትዬ ፍዳዬንአየሁ ይባላሉ። በሽሮሜዳ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ዋና ስማቸው እንኳ ወርቅያንጥፉ ነበር። ነገር ግን ወርቅ አልተነጠፈላቸውም። ከባለቤታቸው አቶ ሃይለኛው ጋር ሲኖሩ አንድ ልጅ አፍርተዋል። የልጃቸው ስም እንደማንም የደሀ ቤተሰብ ልጅ ተስፋዬ ነው።

ያው እንደሚታወቀው፤ በምስኪን ቤተሰብ ውስጥ የመጀመሪያ ልጅ ሲወለድ የሚወጣለት ስም ተስፋዬ ነው። ምክንያቱም ቤተሰቦቹ ተስፋ የሚያደርጉት ከእግዜር ቀጥሎ ልጃቸውን በመሆኑ ነው።

እትዬ ፍዳዬን አየሁ እና ልጃቸው ተስፋዬ ባለቤታቸው አቶ ሃይለኛው በህይወት እያሉ እንደምንም ለእለት ጉርስ ለአመት ልብስ የማይቸገሩትን፤ እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ግን የእነ ተስፋዬ ተስፋ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።

በዚህም የተነሳ ጎረቤት፤ “አሁንማ ጎርምሷል ሊስትሮ ሰርቶም ቢሆን ያግዝሽ እንጂ!” የሚል ሃሳብ ማቅረብ ቢጀምርም እትዬ ፍዳዬን አየሁ ግን “እምቢኝ እኔ በህይወት እያለሁ ልጄ ለስራ ሳይደርስ አደባባይ አይወጣም ተምሮ ጥሩ ደረጃ እንዲደርስልኝ ነው ምኞቴ” ብለው ወይ ፍንክች አሉ። እናም ያለ አባት የቀረው፣ ተስፋ ይሆነኛል ብለው ተስፋዬ ያሉት ልጃቸውን ምንም እንዳይጎድልበት ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

እውነትም ተስፋዬም አላሳፈራቸውም ጥይት የሆነ ተማሪ ወጣው! ሚኒስትሪን ነቀነቀው ማትሪክንም በጠሰው እና ዩንቨርስቲ ገባ።

ተስፋዬ የተመደበው “ሾሎቅ” የተባለ የሀገሪቱ ክፍል የተሰራ አዲስ ዩንቨርስቲ ነው። አንዳንድ የሾሎቅ ነዋሪዎች፤ “በአካባቢያቸው መብራት ሳይኖር፣ መንገድ ሳይገባ፣ ውሃ ሳይስፋፋ፣ እንኳን ሌላ ቀርቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳይኖር ቀድሞ ዩንቨርስቲ በመገንባቱ መንግስት አካባቢውን በተማረ ሃይል ለማጎልበት ቆርጦ መነሳቱን ያሳያል!” ብለው አስተያየታቸውን ሲሰጡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታይቷል።

እትዬ ፍዳዬን አየሁ… (ውይ ስማቸው ለምን እንደወጣላቸው ሳልነግራችሁ…) ከላይ እንደነገርኳችሁ የመጀመሪያ ስማቸው ወርቅ ያንጥፉ ነበር። ይህ ስም ለምን ተሰጣቸው…? ሀገር ጉድ ያስባሉ ቆንጆ ስለነበሩ! እርሷን የሚያገባ መጀመሪያ ወርቅ አንጥፎ ነው። በሚል ምኞት   ነበር።

ነገር ግን የመጀመሪያ ባላቸው ሲያገባቸው እንኳንስ ወርቅ ነጠላም አላነጠፈም። ጠልፎ ወሰዳቸው እንጂ፤ ሳይወዱ በግድ ወይዘሮ የተደረጉት ወርቅያንጥፉ በስንተኛው ጊዜ ከጠላፊያቸው አምልጠው አዲሳባ ገቡ። አዲሳባ ሰው ቤት ሰራተኛ ሆነው ሲኖሩ ከቀጣሪያቸው ጋር ፍቅር ጀመሩ። እዛም ትንሽ እንደቆዩ ወንደላጤው ቀጣሪያቸው ሌላ ሚስት ሊያገባ እንደሆነ ነገራቸው። አለቀሱ ሆዳቸው ባባ፤ አለቀሱ የፍቅር እና የቁጭት እንባ… ከዛም ጥለውት ወጡና ከእንጦጦ እንጨት እየለቀሙ በመሸጥ ኑሯቸውን ሊገፉ ሽሮ ሜዳ መኖር ጀመሩ።

በዚህ ጊዜ አቶ ሃይለኛውን አገኙ። ከእርሳቸው ጋር ተጋብተው መኖር ሲጀምሩ ተስፋዬን ፀነሱ። ይሄኔ አቶ ሃይለኛው እግዜር ይስጣቸውና “እንጨት ለቀማውን ትተሽ አርፈሽ ቤትሽ ቁጭ በይ!” ብለው አሳረፏቸው።

ልጁም ከተወለደ በኋላ በዛው ለመደባቸውና እንጨት ለቀማውን ርግፍ አድርገው ተዉት። የቤቱ ውስጥ ችግር ግን እቤት የሚያስቀምጥ አልነበረም።

ያው ሽሮሜዳ ገንዘብ ከፍሎ የሚያሰራ ባይኖርም፤ የተስፋዬ እናት በየቤቱ በክፍያ ሳይሆን በ “ላግዛችሁ” ሰበብ ስራ እየረዱ ለርሳቸውም ለልጃቸው ተስፋዬም የሚበላ እያገኙ፤ ከአቶ ሃይለኛው ጋር ራት፣ መብራት እና መኝታ ብቻ ነበር የሚጋሩት።

ይሄኔ ከየጎረቤቱ ሲጫወቱ ታድያ “ቤተሰቦቼ ወርቅ ይነጠፍላታል ብለው ወርቅ ያንጥፉ አሉኝ። እኔ ግን እንኳንስ ወርቅ ሊነጠፍልኝ ፍዳዬን አየሁ!” እያሉ መብከንከን የዘወትር ተግባራቸው ነበር። በዚሁ ፍዳዬን አየሁ ተብለው ቀሩ።

ባለቤታቸው አቶ ሃይለኛው ከሞቱ በኋላ ተስፋዬን  የማስተማር ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ እትዬ ፍዳዬን አየሁ ላይ ወደቀ። የባሰውን ፍዳቸውን  ያዩ ጀመር። አንዴ ቀን ስራ አንዴ ያንኑ እንጨት ለቀማ እየሰሩ ገቢ ለማግኘት መከራቸውን አዩ።

ተስፋዬ ዩንቨርስቲ በጠሰ በድፍን ሽሮሜዳ ደስታ ሆነ። ሾሎቅ ዩንቨርስቲ የተመደበው ተስፋዬ ከእናቱ ላለመራቅ ቀረብ ያለ ቦታ የሚቀይረው ሰው ፍለጋ በየ ዩንቨርስቲዎች ደጃፍ እና በተለያዩ የአውቶብስ ፌርማታዎች፤ የቀይሩኝ ማስታወቂያ ለጠፈ። ነገር ግን አልተሳካለትም።

ጉዞ ወደ ሾሎቅ

የሾሎቅ አካባቢ ሰዎች ኢህአዴግ አዲሳባ ሲገባ በርካታ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው። ነገር ግን አካባቢያቸው መንገድ እንኳ በቅጡ አልተሰራላቸውም። “ምነው እኛ ለናንተ እንደዚህ ነበርን?”  ብለው መንግስትን ቢጠይቁም፤ የመንግሰት ተወካዮች፤ “ሀገራችሁ ለትግል እንጂ ለልማት አይመችም” ብለው መልሰውላቸው ነበር። ይኸው ዛሬ ወግ ደረሳቸውና ዩንቨርስቲ ተገነባላቸው። ይህ ዩንቨርስቲ ለሀገሪቱ ሶስት ሺህ አራተኛው ሲሆን ለክልሉ ደግሞ ሶስት መቶ ሃያ ሁለተኛው ነበር።

ተስፋዬ ዩንቨርስቲው ለመድረስ አሰቃቂ የመኪና መንገድ እና አድካሚ የእግር ጉዞ አሳልፏል። “ዩንቨርስቲ ለመግባት ከተማርኩት ይልቅ ወደ ዩንቨርስቲው ለመድረስ የተጓዝኩት ይበልጥ ያድክማል።” ብሎ ለእናቱ ደብዳቤ ቢፅፍ እናቱ እትዬ ፍዳዬን አየሁ፤ “አይዞህ ልጄ እስኪያልፍ ያለፋል” ብለው አፅናንተውታል።

በዩንቨርስቲው የተሟላ መፅሐፍ፣ የተሟላ ቤተ ሙከራ፣ የተሟላ የትምህርት መሳሪያ ማግኘት ፈተና ሆነበት። የዩንቨርስቲው መማሪያ ክፎሎችም ሆኑ ማደሪያ ቤቶች ገና ተሰርተው አላለቁም ነበር። አንዳንድ ጊዜ እነ ተስፋዬ ክፍል ውስጥ እየተማሩ የሚማሩበት ክፍል ግንባታ እዛው ይደረጋል።  እነ ተስፋዬ ከፊት ለፊት ባለው ወንበር ላይ ሰብሰብ ብለው ሲማሩ ከኋላ ያለው ግድግዳ ሊሾ ይገረፍ ነበር። እንደውም ግንበኛው አስራ ሁለተኛ ክፍል ሳልጨርስ ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጋር አብሬ ተማርኩ! እያለ ማታ መሸታ ቤት ተማሪዎቹ ስለሚማሩት ነገር እያወራ የጠጪውን አፍ እንደሚያስከፍት ይነገራል።

በጥቅሉ ተስፋዬ እንደ እናቱ እትዬ ፍዳዬን አየሁ ፍዳውን አይቶ ተመረቀ።

ወደ ቤት ወደ ማድቤት

ተስፋዬ ዲግሪውን ጭኖ ወደ ትውልድ መንደሩ ሽሮሜዳ መጣ። እትዬ ፍዳዬን አየሁ ይቺን ቀን በጉጉት ሲጠብቋት ይኸው ደረሰች። ልጃቸው ተስፋዬ ዳቦ ሊሆናቸው ደረሰላቸው።

ወደ ሰፈሩ ከአራት አመት በኋላ ሲመጣ በሃሳቡ፤ “ወደቤት ወደ ማድቤት አንድ እንጀራ ለጎረቤት” እያለ ነበር። እንጀራው ግን ከየት ይመጣ ይሆን? በርግጥ ተምሯል። ግን ምን ይሰራ ይሆን? በእውኑ በሾሎቅ ዩንቨርስቲ ያገኘው እውቀት ተወዳዳሪ ያደርገው ይሆን…? ተስፋዬ ከእርሱ በፊት ከዩንቨርስቲ የተመረቁ ልጆች ውስጥ ስራ ያገኘ ሰው ማሰብ ጀመረ። ማንም በሀሳቡ አልመጣም።

የሽሮሜዳን አስፋልት ጨርሶ የሰፈሩን ኮረኮንች መንገድ ሲጀመር ተቆፋፍሮ ድንጋይ ተቆልሎ ተመለከተ። በሃሳቡም “ይሄ የማያልፍለት ሰፈር ዛሬም ይፈርሳል…!?” እያለ በሆዱ አማረረ።

የተቆለለው ድንጋይ ኮብል ስቶን ይባላል። ለአራት አመት በኖረበት “ሾሎቅ” የኮብልስቶን ግንባታ አላየም። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ግን ብዙ ጊዜ ስለ ኮብል ስቶን ሰምቷል። እንደውም አንድ ጊዜ በኢቲቪ የጥያቄና መልስ ውድድር “የከበረ ድንጋይ ከሚባሉት ውስጥ አንዱን ጥቀስ…” ተብሎ የተጠየቀ ተወዳዳሪ “ኮብል ስቶን” ብሎ መመለሱን አስታውሶ ሳቀ።

የተቆለሉት ኮብል ስቶኖች  የሞቀ ወግ ይዘው ነበር። ግማሹ “ተመስገን ጌታዬ የወንዝ ድንጋይ አድርገህ አላስቀረኸኝ!” እያለ ሲያመሰግን ሌላው ደግሞ፤ “እዚህ ቆልለው አቧራ ከሚያጠጡን እዛው ወንዛችን ውስጥ በውሃ መንቦራጨቅ በስንት ጣዕሙ!” እያለ ያማርራል።

ድንገት ተስፋዬን ሲመለከቱ ኮብል ስቶኖቹ ማውራታቸውን ትተው ፀጥ ፀጥ አሉ። እርሱ ካለፈ በኋላ ለኮብል ስቶንነት ያልታደለ በድሮ ጊዜ “የኬር ንጣፍ” በመባል የሚታወቅ ድንጋይ ስለ ተስፋዬ ተናገረ፤ “እዚህ ሰፈር ረጋ ብሎ የሚረግጠን እርሱ ነበር የት ጠፍቶ መጣ!?” አለ። ሌላውም “አንተ እዚሁ ተኝተህ፤ እርሱ ዩንቨርስቲ በጥሶ ይኸው አራት አመት ተምሮ ጨርሶ መጣ!” አለ ምንው ድንጋይ ባልሆንኩ በሚል ቁጭት። ይሄን ግዜ አንዷ ኮብል ስቶን ቀበል አደረገችና “እሰይ ጠራቢያችን እርሱ ነዋ!” ስትል በደስታ ተናገረች። በዚሁ ጨዋታው ደራ፤

ኮብል ስቶኖቹ ከዚህ በፊት በማህበር በተደራጁ ያልተማሩ ሰዎች ሲጠርቡ እና ሲቀጠቀጡ በጣም ከበድ ከበድ ያለ ዱላ ያርፍባቸው ነበር። አሁን ግን ተመስገን ጊዜው ተሻሽሎ ባለ ዲግሪዎች ይጠርቧቸው ጀምረዋል። ባለ ዲግሪዎቹ ልጆች እጃቸው እስክርቢቶ የለመደ ስስ በመሆኑ የተነሳ ብዙም አይመቷቸውም። በዚህም አንድ ሰው ተመርቆ ሲመጣ ደስታቸው ወደር የለውም። አንዳንዶቹም “ምንም ቢሆን የተማረ የጠበኝ ነኝ!” እያሉ ባለተማረ ሰው የተጠረቡት ላይ ይንቀባረሩባቸዋል። አንደውም ከኮብል ስቶኖቹ አንዱ አንድ አባባል ፈልስፏል። “የተማረ ይጥረበኝ!” የሚል።

እትዬ ፍዳዬን አየሁ ፍዳቸውን አይተው ያሳደጉት፤ ፍዳቸውን አይተው ዩንቨርስቲ ድረስ ያስተማሩት፣ ተስፋ ይሆነኛል ያሉት ልጃቸው በርቀት ሲመጣ ተመለከቱት በተለይ ይቺ አራት አመት እንዴት እንዳለቀችላቸው የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ናቸው። ከዚህ በኋላ አረፍ ሊሉ ነው። ተስፋቸው ይኸው መጣ!  እልልታውን አቀለጡት።

በየቦታው አለፍ አለፍ ብለው የተቆለሉ የሰፈራቸው ኮብል ስቶኖችም ከእትዬ ፍዳዬን አየሁ ጋር አብረው እልልታቸውን አቀለጡት። ምንም ቢሆን “የተማረ ይጥረበኝ” ነውና!

ከኮብል ስቶኖቹ አንዱ ግን እንዲህ ሲል ጠየቀ፤ “እኔ የምለው ቅድም ወንድሜ የኬር ንጣፍ ሲናገር እንደሰማሁት ይሄ ረጋ ያለ ልጅ ለአራት አመት ትምህርት ላይ ነበር። ይኸው ሌሎቹ ምንም ሳይማሩ ይቀጠቅጡን የለ እንዴ!? እርሱ ታድያ እንደነርሱ ሳይማር ሊጠርበን ሲችል፤ ይሄን ያህል ጊዜ በትምህርት ምን አለፋው!? አለ።

ይሄንን ጥያቄ፤ ተስፋዬም፣ እትዬ ፍዳዬን አየሁም፣ ሌላ ኮብል ስቶንም፣ የኬር ንጣፍም፣ መንግስትም፣ ፀሐፊውም መመለስ አይችሉም። ምናልባት ጊዜ ይመልሰው ይሆናል።

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

11 responses »

  1. Abecho fikir says:

    ተምረንም የ”ኮብልስቶን”(የኮረት ንጣፍ) ባለሙያ አደረጉን! ቆይተው ደግሞ በደረጃ ባንክ ዘራፊ ተመራቂ ተብለው ራሳቸው ስልጠና ይወስዳሉ። ከባንክ ዘራፊና ስኳር ላሽ ኮረት አንጣፊ መፈጠሩ ለነሱ ትልቅ ግብም ባይሆን ግብግብ ይሆንላቸዋል-ይፈልጉታላ።

    • dubale says:

      fiker tew bakeh…be kurat new mseraw coblestone bagere mdr…ante aleh aydel ende masters cherseh be sew ager parking yemtsera. tewu engi eyetewawekn…ere tewu ensrabet…agerachin enalmabet

  2. Tikur sew says:

    ምን አልባት ተሳስቸ ይሆናል ፤ የዚህን ያክል ዉድቀት ግን ይኖራል ብየ አላስብም ። የተማረ ፣ማሰብ የሚችል፣ ነገን የሚረዳ ፣ እዉነተኛ ለሀገር የሚቆረቆር መሪ መመደብ ይገባቸዋል ፡ አቶ መለስ !!!! ይህ ካልሆነ ግን ሀገር ከዚህ በላይ በብርሀን ፍጥነት ወደታች ማደጓን የበለጠ ታፋጥን ይሆናል እንጂ የተማረ ህብረተሰብ ጎዳና እያደረ ያለተማረ እቅድ እየነደፈ እድገቱ በዚህን ያክል እንደሚባለዉ በፍጥነት እያደገ ይቀጥላል ማለት ግራ የሚያጋባ ነገር ነዉ !!! አምላክ ዉድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ !!!! አሜን።

  3. Agazi Meles Kendebbo says:

    Tnx….Abe !

  4. Buta madingo says:

    Well,if educated ppl.are working on cobble stone what is my chance will be, i am not educated i am not HODAM i am not ASHQABACH what am i suppose to do OMG.

  5. Tulu forza (Austria) says:

    የሰላ ማህበራዊ ሂስ ይሏል ይሄ ነው-የጨለማውን ስርዓት እርቃን በቃላት ብርሃን ማጋለጥ። ወያኔ ለምን ከሽሮ ሜዳ እንዳባረረህ አሁን ገና ገባኝ አቤ!

  6. Demelash says:

    Abe thanks, It is TRUE woyane never want to see a developed Ethiopia and Ethiopians. Only God knows the future of this country and people. it is so sad to hear that graduate citizens live in the street of addis! (You can read this week REPORTER Amharic).How come REPORTER freely express such social crisis under the noses of woyane? I know a teacher who beg during his free time at 4 killo St. Gebrel and Silase church.
    By the way Abe your writing style looks like Bewketu Seyoum’s writing style.

  7. Demelash says:

    Abe Breaking news Mr Zenawi’s health condition was deteriorating, he can not report present the next year fiscal budget of the country and send members for recesses. Probably some Ethiopian prayer or curs get in heaven.

  8. ሄሌሌ ሃንባቤ says:

    “ድሀ አይግዛ፣ ከገዛም አያብዛ” ፣ “ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” ፣ “ሁሉ አማረሽን ገበያ አታዉጡዋት” እየተባሉ የሚተረቱት ተረቶች ህሊና የማይገዛቸዉ፣ አስተዉለዉ ለማይናገሩ፣ ችሎታ ሳይኖራቸዉ በጉልበት ህዝብን ለመግዛትም ሆነ ለመጉዳት በሚነሱ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ተረታዊ አባባሎች ናቸዉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ደግሞ በብዙ አገሮች በተለይም በአፍሪካ አገሮች ዉስጥ ብዙ ጉዳት በህዝብ ያደረሱ እንዳሉ ከታሪክ መረዳት አያዳግትም። የእዉቀት፣ የስነ ልቡና እና የህሊና ጉድለት ያለባቸዉ ግለሰቦች የዝቅተኝነት መንፈሳቸዉን የሚወጡት ጉልበት በማሳየት ነዉ። ይህ ጉልበት ማሳየት ደግሞ የባሰ ፖለቲካዊና ማህበረ ሰብአዊ ዉድቀት ዉስጥ ሲከታቸዉ ከዉድቀቱ ለመዉጣት ሳይሆን የሚፍጨረጨሩት ገመናቸዉን ለመሸፈን ነዉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ምን ጊዜም ቢሆን ከስህተታቸዉ አይማሩም። ጋዳፊ፣ ቤን አሊ፣ ሙባረክ፣ አሊ አብዱላ ሳሌህ የት እንደደረሱ አየነዉ እኮ። “ባልነጀሬ አይበልሽ ከፋ፣ አይበልሽ ከፋ፣ ሁሉም ያገባል በየወረፋ” የሚባለዉ ዘፈን ወደ ፖለቲካ ሲመነዘር “ማነህ ባለሳምንት…….እኔ ነኝ የምትል የጋዳፊ ወዳጅ” የሚስብል አባባል ያስከትላል። የነፍስ ግቢ ዉጪ መፍጨርጨር አይቀርምና የሚከፈለዉ ተከፍሎ መገላገሉ ተገቢ ይሆናል። ይመችህ አቤ!

  9. በለው! says:

    “አሞሌ ጨው ከት ብላ ሳቋን ለቀቀችው “ውይ ! ይቺ ኮብላይ እስቶን የቀበና (የቅንብቢት) ሠፈር ናት! ድሮ አላፊ አግዳሚውን የቆመውን የተቀመጠውን በካልቾ የሚጠርቡት ሰፈር ኖራ የተማረ ይጥረበኝ አለች…ኡ ኡ ቴ አልቀረባትም አንደእኔ አጣፍጥም ነበር ለወጥ መስሪያ ሆና ያልተማረው እንዲንከባከባት !!

    ተመስገን ደስአለኝ አቤ…ለእግሩ ጫማ የሌለው ሕዘብ የተማረ ወጣት በጠረበው ድነጋይ ይንፈላሰሳል በሉኝ !?!
    ያ..የፈረደበት የዋህ ድሃ ሕዝብ ‘የተማረ ይግደለኝ’ ሲል ይኼው እንደተመኘው ሆነለት! ቢበላውም፣ ቢያስበላውም፣ ቢያባላውም፣ ይግደለኝ አለው ገደለው ! ገደለው! በቀጥታ ወደ ገደለው እንሂድ….

    ሕዝቡም ድንጋይም እኩል ያማርራሉ…
    “ይሄ ረጋ ያለ ልጅ ለአራት አመት ትምህርት ላይ ነበር። ይኸው ሌሎቹ ምንም ሳይማሩ ይቀጠቅጡን የለ እንዴ!? እርሱ ታድያ እንደነርሱ ሳይማር ሊጠርበን ሲችል፤ ይሄን ያህል ጊዜ በትምህርት ምን አለፋው!? አለ።” እኛም የታዘብነው ይህ
    ጊዜ ይመልሰው ይሆናል ብለን አንተወውም ። ጊዜው ይሮጣል ከተጠራቢው ጠራቢው በበዛ ቁጥር ተጠራቢው እየቀነሰ ወይም እየተሸራረፈ በሄደ ቁጥር መዶሻ እራሱ ይሳለቅብናል። ሙያን ለባለሙያተኛው ሀገር የጋራ ነው በለው!!!!!!

  10. ነህምያ says:

    “የተማረ ይጥረበኝ”

    የተማረ ይግደለኝ ሲባል እንዳልነበር
    የተማረ ይጥረበኝ ያውም ባለማስተር
    የሚል ዘይቤ መጥቶ በኢትዮጵያ ከናኘ
    ልብ ይበል ያን ጊዜ ሕዝብ አንደተሞኘ
    የልማቱ ነገር እንደነበር ጥፋት
    የዕድገቱም እመርታ ቁልቁል ወደ አዘቅት

    የዩኒቨርሲቲ ጋጋታ
    ለመፍትሔ ካልሆነ ለመከታ
    ዶክተርና ማስተር
    ከሆኑ ለዝና ከሆኑ ለክብር
    ትምህርት እንደ ዝናብ ወይም እንደ ካፊያ
    ቢዶፍ ቢርከፈከፍ በኢትዮጵያ

    ብልሃት ዘይዶ ችግር አላራቀ
    ችጋርን አጥፍቶ በሀብት አልጠመቀ
    ታዲያ ይህን ያህል ወጣ ተመርቆ
    መባሉ ምንድነው? …
    በምን ይታወቃል አውቆ ይሁን ሰርቆ

Leave a comment