አንድ የተለመደችን ተረት ትንሽ ለማሻሻል ጥረት አድርጌ ልንገራችሁማ….
ሰውየው ዕድሜ ጠገብ መሆናቸውን ለማወቅ ፀጉራቸውን ተመልክቶ ብቻ መረዳት ይቻላል። አንድም እንኳ ጥቁር ፀጉር አይታይባቸውም። ሙሉ ነጭ ጥጥ የመሰለ ባለ ግርማ ሞገስ ፀጉር ባለቤት ናቸው!
ልጅየው ዕውቀት ጠገብ እንዳልሆነ ለማወቅ አነጋገሩን ብቻ ሰምቶ መረዳት ይቻላል። አንድም እንኳ ብስለት ያለው ነገር አይታይበትም። ሙሉ ነጭ የሆነ ከለር አልባ አነጋገር የዘለፋ እና የዘረፋ ባለቤት ነው።
ከወደ አፋፉ እያዘገሙ ሲመጡ ተመለከታቸው። ቢያገኝ ሊዘርፍ ቢያጣ ሊዘልፍ ታጥቆ የተነሳ ነውና፣ ወደ ሽብታማው ፀጉራቸው እያመለከተ፤ “ሼባው የጥጥ ፋብሪካው የት ነው ያለው ባክህ…!” ብሎ አንጓጠጣቸው። እሳቸውም ረጋ ባለ አስተማሪ ድምፅ፤ “አዬ… የኔ ልጅ ነገሩ እንኳ እዚሁ ቅርብ ነበር ግን በዚህ አካሄድህ የምትደርስበት አልመሰለኝም!” ብለው መለሱለት።
ወዳጄ እንዴት አሉልኝ እኔ የምለው ኢህአዴግ ነብሴ ከዚህ ቀጥሎ አርባ አመት ለመንገስ እቅድ አለው። ወይ ጉድ ይሄ ቁጥር መቼም ሲጠሩት የትግሉን ያህል አይከብድም። አስራ አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ እድገት ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ የምርጫ ውጤት አርባ አመት የስልጣን ዘመን፤ በእውነቱ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ሆኑ መላው የኢህአዴግ ቁልፍ ሰዎች አባይን ሳይሆን፤ ቁጥርን የደፈሩ ተብሎ ትልቅ ቢል ቦርድ ቢሰራላቸው መልካም ይመስለኛል።
እዝችውጋ ሳይረሳ ትላንት የአባይ ግድብን አስመልክቶ ታላቁ ሩጫ ተከናውኖ ነበር።የመሮጫ ቲሸርቱ አንድ መቶ ብር ነበር የሚሸጠው። ወይ መቶ…. መቶ ምን ተሰርቶ? እንደሚገኝ አልገባቸውም ሰዎቻችን። በነገራችን ላይ “ቲሸርቱን ግዙ እንጂ!” የሚለው ማስታወቂያ ለእሁድ ሩጫ እስከ ቅዳሜ ድረስ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲነገር ነበር፤ ያው ከዚህ እንደምንረዳው ህብረተሰቡ ዘንድ የሩጫ ቲሸርቱን ለመግዛት የሚሆን የገንዘብም ሆነ የሞራል እጥረት መኖሩን ነው።
ምንጮቼ እንደነገሩኝ አብዛኛውን ቲሸርት ለየ መስሪያ ቤቱ እና ለየ ቀበሌ፤ ወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም ለአነስተኛና ጥቃቅኖች ነው የተሸጠው አሉ… (እንግዲህ አሉ ነው እኛማ የት አየነው…!?) ከፓርላማ አባ ዱላ ከኢቲቪ ደግሞ አባ መሰለን ግን ቃለ ምልልስ ሲደረግላቸው አይቻቸዋለሁ። በተለይ አባዱላ ባለፈው ጊዜም ለአባይ ልደት በኳስ ጨዋታ መከራቸውን ሲያዩ ነበር። እኔ የምለው እንዲህ በስፖርት የሚቀጧቸው ምን አድርገው ነው። ቪላ መገንባት በርሳቸው አልተጀመረ…! ደሞ ቪላውንም ለኦህዴድ ሰጥቻለሁ ብለው ነበርኮ… ወይስ ከግምገማው በኋላ እምቢ አልጫወትም ብለው ቀምተውታል መሰል!?
እኔ የምልዎ ወዳጄ…
አንድ
የሰሞኑን ነገር ልብ ብለው እየመዘገቡልኝ ነው!? እነ እስክንድር ነጋ “ሽብርተኛ” ተብለው የተፈረደባቸው ሳያንስ ምን ባደረጉ እንደሁ እንጃ ለሁለት ቀናት ምግብ ሳይገባላቸው፤ ጨለማ ቤት እንዲያድሩ ተፈርዶባቸው ነበር አሉ። ከዛም በስንት ጩኸት ተመልሰው ቀድሞ ቦታቸው ገብተዋል። ልብ አድርጉልኝ አነዚህ ሰዎች ተፈርዶባቸው እንኳ እንዲህ የሚንገላቱ ከሆነ በምርመራ ወቅትማ እንዴት ተደርገው ነበር…?
ሁለት
የሙስሊም ወንድሞቻችንም ያ ሁሉ ተቃውሞ ከአሁን አሁን መፍትሄ ያገኛል ሲባል “ኢማማችሁን ቀበሌ ውስጥ ምረጡ” በሚል መፍትሄ ሊያጠናቀቅ የፈለገ ይመስላል። የቀበሌን ምርጫ ከዚህ በፊት ያየ ያውቀዋልና፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ “ቀበሌ የሚመረጠው የፖለቲካ ምርጫ እንጂ የሀይማኖት አይደለም” በሚል አጥብቀው እየተቃወሙት ይገኛል። መንግስታችን ግን ይህ አክራሪነት ነው አሸባሪነት ነው እያለ ከመውቀስ አልተቆጠበም!
ሶስት
የዋልድባ ነገር አሁንም መፍትሄ አላገኘም። ሰሞኑን ዋልድባ በፌደራል ፖሊስ ተከባ እንደነበር ሰምተናል። በርግጥ በኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያኑ እንደሙስሊሙ በየ ቤተስኪያኑ ተቃውሞውን ሲያሰማ አልታየም። ነገር ግን በፀሎቱ እየተጋ ነው። ከዚህ እዚያ የሚባረሩ እና የሚታሰሩ የዋልድባ መነኮሳትም ዝም አይሉም።
አራት
በሲዳማ አካባቢ ደግሞ ሌላ ግጭት ተቀስቅሷል ዝም ብዬ ግጭት ብቻ እላለሁ እንዴ? ወጣቶቹ ተሰባስበው “ሲወን” የሚባል አንድ በህቡዕ የሚሰራ ድርጅት ሁላ አቋቁመዋል እንጂ…! ይሄ ንቅናቄ መመህራንን፣ የፖሊስ አባላትን እና የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞችን ያቀፈ እንደሆነ ተሰምቷል። ንቅናቄው ኢህአዴግን ካላነቃነኩት ሞቼ እገኛለሁ! ብሏል አሉ!
አምስት
በዚህ ላይ የሁሉም ጠቅላይ አዛዥ የኑሮ ውድነት እና ውጥንቅጥ ሰዉን ቅጥ እያሳጣው ይገኛል። ባለስልጣኖቻችን ለዚህ ሲመልሱ የእድገት መገለጫ ነው። አታዩም እንዴ ፎቁን? አታዩም እንዴ መንገዱን? ይሉናል። አንድ ወዳጃችን በቅርቡ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ፤ “ተመስገን መንገድ እየተሰራልን ነው ፈጥነን ወደቤታችን መግባት እንችላለን፤ ግን እኮ ቤት ገብተን የምንበላው የለንም!” ብሎ አማሮ ነበር። እናም የኑሮው ነገር ሁሉንም በየጓዳውና በየፌስ ቡኩ እያማረረው ነው!
ለኢንተርኔት ቆጣሪዎ አስቤ እንጂ ችግሮቹ ተቆጥረው አያልቁም…!
የምር ግን ባለስልጣኖቻችን ህዝቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች እና ለሚያነሳቸው ችግሮች መልሱ ሲባሉ፤ “ሲያላገጡ እንጂ መልስ ሲሰጡ አልታዩም!” እያለ የሚያማርር ሰው በየ ቦታው እየተበራከተ ነው።
ታድያ በዚህ አካሄድ ነው አርባ አመት የሚኬደው…!? እንደውም አንድ ግጥም ትዝ አለችኝ፤ “በነጠላ ጫማ በአንቺ አረማመድ፤ እንዴት ያልቅልሻል ያ ሁሉ መንገድ!?”
“የጥጥ ፋብሪካውስ ቅርብ ነበር ግን በዚህ አካሄድህ የምትደርስ አይመስለኝም!” አሉ ሽማግሌው…! እናጃ…!!
አቤ፣ነገሩ እኮ ፈረኦናዊ አገዛዝ ነው። ቁጥሯም ከዚያው የተቃረመች ናት። የሰው ልጅ አንድ ጊዜ አቅሉን ከሳተ፤ነገሮችን በውሉ መለዬት አይችልም። እኒህም እንዲሁ ሆነዋል። ነገሩ ሁሉ “ቆቅ ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” አይነት ነው። በቻ በአይምሯቸው ጓዳ ያንባረቀባቸውን ሳያገናዝቡ፤ሳያሰናስሉ እንዲሁም ሳይመካከሩ ዝርግፍ ያደርጉታል። አወዳደቃቸውም እንዲሁ ፈረኦናዊ ነው የሚሆነው። ተበላሽተው፤ አበለሻሽተው ብን ትን ብለው ይሄዳሉ። የዘነጉት ግን የኢትዬጵያ አምላክ የዘገዬ ቢመስልም የቃል ኪዳን አገሩ ስትጠፋ ዝም አይልም! ሁሉም እንደ ስራው ያገኛታል!!!!
አቤ ጠፍተህብን ቆየህ እኮ፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ክረምት ሰውን በስብሰባ አታሎ ለማለፍ እየሞከረ ይመስላል፡፡ መምህራን ባለፈው በጠየቁት የደሞዝ ጭማሪ የተነሳ አሁን ሰፊ ግምገማ በማለት የማይፈልጉትን መምህር ለማባረር እየሰሩ ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች አበል ተጨመረ በማለት በኢቲቪ በመናገር በነጋታው በማንኛውም እቃ ላይ ዋጋ እንዲጨመርብን ምክንያት ሆናል፡፡ እንዴት ከስተታቸው አይማሩም፡፡ ለማንኛውም ቸር ያሰንብተን፡፡
what a great piece …thanks abe tokichaw
“በነጠላ ጫማ በአንቺ አረማመድ፤ እንዴት ያልቅልሻል ያ ሁሉ መንገድ!?”
በታኮ በታኮ ወይ መወላገድ
ኢህአዴግን አየሁ በምላስ ሲሄድ
አንዳዴም ሲቀናው ሲቀለማምድ
አልፎ አልፎ ሲዘንብ ተደፍቶ ሲዋርድ
ትርፉ መውደቅ ነው ሳይውቁ መራመድ!
http://www.ethiotube.net/video/14255/PM-Meles-Zenawi-full-speech-at-the-closing-
http://www.ethiotube.net/video/14681/Mebratu-Abera–Tiz-Alegn-Arada
http://www.diretube.com/desta-bekele/kin-kin-video_5c77cada0.html
ቂን…ቂን… ቂን.. ታድያ በዚህ አካሄድ ነው አርባ አመት የሚኬደው…!?