ዛሬ ሰንበትም አይደል!? ሲነጋ ከኔጋ በተለያዩ ጨዋታዎች የምንገናኝ ይመስለኛል። ለዛሬ ግን በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር አዲስ ጉዳይ መፅሔት ላይ ያወጣውን ይቺን ጨዋታ ትቋደሱልኝ ዘንድ አነሆ… እላለሁ! በሀይሉንም አዲስ ጉዳይንም “ገለታ” እንላለን!
ተመልካቾቻችን በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጥ አስራ አንድና የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚያደርጉትን ጨዋታ ከዚህ ከስቱዱዮአችን በቀጥታ የምናስተላለፍላችሁ እኔ፣ ኢንስትራክተርና ጋዜጠኛ ድማሙ እንዲሁም ቴክኒሻናችን ነይማ ነን፡፡ ወደ አጓጊው ጨዋታ ከመሄዳችን በፊት የስፖንሰራችንን ማስታወቂያ ሰምተን እንመለስ፡፡
ሻሼ አረቄ!
የሴትነት ልኩ ይታይ ከተባለ፣
ከአረቄ ማውጣት ውጪ፣ ሙያ ወዴት አለ?
ለደማቅ ጨዋታ፣ ለፌሽታ፣ ለደስታ፣
የሻሼ አረቄ፣ ጠርሙሱ ይከፈታ!
የምን ብላክ ሌብል፣ የምን ኋይት ሆርስ፣
የሻሼ አረቄ፣ ይምጣ በፈረስ!
ሻሼ አረቄ…!
ተመልካቾቻችን ከስፖሰራችን ማስታወቂያ ተመልሰናል፡፡ በዳፍ በኩል የመንግሥት ባለስልጣናቱ ሲገኙ፣ በሚስማር ተራ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጥ አስራ አንዶቹ ይገኛሉ፡፡
አሁን ጨዋታው ተጀምሯል፡፡ ኳሷ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እግር ስር ናት፡፡ ሰባት ቁጥሩ አቶ ዘንጉ ኳሷን ይዘዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲያቸውን ወክለው ፓርላማ ገብተው የነበሩት አቶ ዘንጉ ኳስ ይዘዋል፡፡ አቶ ዘንጉ በእርግጥም ያኔ ፓርላማ ውስጥ ስለመኖራቸው የሚያውቁት እርሳቸውና ከእርሳቸው ጋር የተቀመጡት ብቻ ናቸው ተብለው ሲተቹ ነበር፡፡
ጨዋታው ቀጥሏል፤ የመንግሥት ባለስልጣኑ የተከበሩ አቶ ጠነነ ኳስ ቀሙ፡፡ ኳስ ለመቀማት አደገኛ አገባብ ነበር የገቡት፡፡ ሆኖም ዳኛው በቸልታ አልፈዋቸዋል፡፡ የተከበሩ አቶ ጠነነ ለተከበሩ አቶ ቢተው አቀበሉ፡፡ አቶ ቢተው ኳሱን ይዘዋል፡፡ አቶ ቢተው ኳሱን እየገፉ ነው፡፡ ተመልካቾቻችን የባለስልጣኑ ቡድን አባላት የሚያደርጉት የመሬት ቅብብል ማራኪ ነው፡፡
የተከበሩ አቶ ቢተው ኳስ ይዘዋል፡፡ በከተማችን ውስጥ የታወቁ አምስት ህንፃዎች ባለቤት የሆኑት አቶ ቢተው እያታለሉ ነው፡፡ አቶ ቢተው እያታለሉ ኳሱን ይዘው ወደ ፊት እየሄዱ ነው፡፡ የተከበሩ አቶ ቢተው በረዥሙ መቱ፤ ሆኖም ኳሱ ወደ ውጪ ወጣ፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ቡድን ግብ ጠባቂ የሆኑት አቶ ሰንደሉ የመልስ ምት ለመምታት እየተዘጋጁ ነው፡፡ ተመልካቾቻችን፣ አቶ ሰንደሉ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መሥርተው ማፍረሳቸው ይታወቃል፡፡ በመጪው የፖለቲካ ምርጫ በአሥረኛው ፓርቲያቸው እንደሚወዳደሩ አቶ ሰንደሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰንደሉ በረዥሙ መቱ፡፡ እሳቸው የመቱትን ኳስ ለማግኘት በተደረገው ዝላይ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተጫዋች በመንግሥት ባለሥልጣናት ተጫዋች የተመቱ ይመስላል፡፡
ኦ! አደገኛ ጥፋት ተፈፅሟል፡፡ አዎ! የመንግሥት ባለስልጣናት ቡድን ተከላካይ የሆኑት አቶ መክት በተቃዋሚ ፓርቲው አባል በአቶ ጻድቁ ላይ አደገኛ ጥፋት ፈፅመዋል፡፡ ዳኛውም ፊሽካ ነፍተዋል፡፡ ሁኔታው ያስፈራል፡፡ ዳኛው ቀይ የሚሰጡ ይመስላል፡፡
ኢንስትራክተር የተከበሩ አቶ መክት ቀይ የሚያዩ ይመስሎታል? ኢንስትራክተር ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ አዎ! ተመልካቾቻችን ቀይ ካርድ ሊያሰጥም ላያሰጥም ይችላል በማለት ኢንስትራክተር ራሳቸውን ነቅንቀዋል፡፡ አደገኛ ጥፋት የተሠራባቸው አቶ ጻድቁ ሜዳ ላይ እንደተኙ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተመልካቾቻችን የመንግስት ባለስልጣናት ቡድን ተከላካይ የሆኑት አቶ መክት በአደገኛ አጨዋወታቸው የታወቁ ናቸው፡፡
‹‹መክት፣
የተቃዋሚ ፓርቲን፣ አደረገው እንክት!›› የተባለላቸው ናቸው፡፡
የተከበሩ አቶ መክት በፓርቲያቸው ግምገማ ላይ ከስልሳ ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ያላግባብ ወስደዋል በሚል ሲከሰሱ፣ ‹‹ክፍለ ከተማ› የምታክል መሬት ወስጄ በ‹ክልል› ተጠረጠርኩ›› ብለው ማሾፋቸውን ሰምተናል፡፡
አሁን ጨዋታው ሊቀጥል ነው፡፡ የተጎዱት የተቃዋሚ ፓርቲ ተጫዋች አቶ ጻድቁ ሜዳ ውስጥ ተኝተዋል፡፡ የዳኛው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡ ዳኛው ለመንግሥት ባለሥልጣኑ ለተከበሩ ለአቶ መክት ቀይ ይሰጧቸው ይሆን የሚለው ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም፡፡ ኢንስትራክተርንም ስጠይቃቸው ራሳቸውን ነቅንቀዋል፡፡ ዳኛው ጥፋት የተሠራበት ቦታ ላይ ቆመዋል፡፡ አዎ! ተመልካቾቻችን ዳኛው ጥፋት የሠሩትን ባለሥልጣን አቶ መክትን በፊሽካ ጠሯቸው፡፡ በሠሩት ጥፋት ምንም ያልተፀፀቱት አቶ መክትም ወደ ዳኛው ቀረቡ፡፡ ቀይ የሚያዩ ይመስላል፡፡ ዳኛው ቀይ የሚሰጧቸው ይመስላል፡፡
ኦ! ኦ! በምክር ብቻ አለፏቸው፡፡ ዳኛው አቶ መክትን እንደ ነፍስ አባት መክረዋቸው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ካርድ ጨዋታው እንዲቀጥል አዘዙ፡፡ በጣም ይገርማል፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በውሳኔው ደስተኛ አለመሆናቸውን እየገለፁ ነው፡፡ ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይላቸው ዳኛውን ከብበው እየወተወቱ ነው፡፡ ‹‹የዳኛውን ውሳኔ በፀጋ ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም!›› እያሉ ነው ኢንስትራክተር፡፡
ተመልካቾቻችን ከጨዋታው በፊት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ዳኛው ፍትሐዊ እንዲሆኑ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህም በላይ ጨዋታውን የሚታዘብ ዳኛ ፊፋ እንዲልክላቸው፣ ሜዳውም ጠባብ እንደሆነና ጨዋታው በገለልተኛ ሀገር ሜዳ ላይ እንዲደረግ መንግሥትን ጠይቀው፣ ጥያቄያቸው ውድቅ እንደተደረገባቸው ሰምተን ነበር፡፡
አሁን ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዜሮ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ምርጥ አስራ አንዶቹ ዜሮ፡፡ ኳስ የመቆጣጠር ብልጫውን የወሰዱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲው ተጫዋች አቶ ጻድቁ ተጎድተው ከሜዳ ወጥተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ተመልካቾቻችን አቶ ጻድቁ በዛሬው ጨዋታ ላይ የቡድኑ አንበል ማን መሆን አለበት በሚለው ከቡድን አጋሮቻቸው ጋር ሰፊ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በመጨረሻ ራሳቸው አንበል ሆነው ተመርጠው ቡድናቸውን ወደ ሜዳ ይዘው ቢገቡም በተሰራባቸው አደገኛ ጥፋት ተጎድተው ከሜዳ ወጥተዋል፡፡ ተመልካቾቻችን እንደምታውቁት በተቃዋሚ ፓርቲ ምርጥ አስራ አንድ ቡድን ውስጥ ሁልጊዜ የአንበል ማን ይሁን ጥያቄ እንዳወዛገበ ነው፡፡
አሁን አቶ ጻድቁን ተክተው 14 ቁጥሩ አቶ ዘርፉ ገብተዋል፡፡ ጨዋታውም ቀጥሏል፡፡ አቶ ዘርፉ ለብዙ ዓመታት በገዢው ፓርቲ አባላት ውስጥ ትልቅ የሥራ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በነፃ ዝውውር ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ የተቀላቀሉት በቅርቡ ነው፡፡ አቶ ዘርፉ ስለቀድሞ ጓደኞቻቸው ያጨዋወት ስልት ለአሁኑ የቡድን አጋሮቻቸው በቂ መረጃ እንደሰጡ ይነገራል፡፡ ሆኖም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መረጃውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት አይስተዋልም፡፡
ኳስ አሁን ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ የእጅ ውርወራ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሰጥቷል፡፡ አቶ ዘንጉ ሊወረውሩ ነው፡፡ አቶ ዘንጉ ሊወረውሩ የቡድን ጓደኞቻቸውን በዐይናቸው እየፈለጉ ነው፡፡ በጣም ይገርማል፤ አቶ ዘንጉ በእጃቸው የያዙት ኳስ ቦንብ ይመስል ራሱን ነፃ አድርጎ ለመቀበል የተዘጋጀ የቡድን አጋር አላገኙም፡፡ ተመልካቾቻችን የተቃዋሚዎች ፓርቲ አባላት ተግባብተው መጫወት አልቻሉም፡፡
አቶ ዘንጉ ወረወሩ፡፡ ኳስ በቀላሉ የመንግስት ባለሥልጣናት እግር ሥር ገብታለች፡፡ ባለሥልጣኑ መሬት ለመሬት እየተቀባበሉ ነው፡፡ የታወቁበትን የመሬት ቅብብል ዛሬም እያሳዩን ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ግን ኳስን ባየር ላይ መጫወታቸውን ገፍተውበታል፡፡ ለግል ሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት የሚታወቁት አሰልጣኛቸው ከጨዋታው በፊት ሲናገሩ፣ ‹‹የምንጫወተው ያየር ላይ ኳስን መሠረት አድርገን ነው፤ ለምን? ባለሥልጣኑ በመሬት ቅብብሉ የተካኑ ስለሆኑና መሬቱም የእነርሱ ስለሆነ!›› ብለው ነበር፡፡ አሁንም እያየን ያለነው ይሄንኑ አጨዋወት ነው፡፡
እንግዲህ ተመልካቾቻችን እንደምታዩት የተቃዋሚ ፓርቲ የመሃል ክፍሉ ከአጥቂው ጋር እንዳይገናኝ በመንግስት ባለሥልጣናት ለሁለት ተቆርጧል፡፡ በዚህም የተቃዋሚ ፓርቲ ተጫዋቾች የመንግሥት ባለስልጣናትን የግብ ክልል ጥሰው መግባት አልቻሉም፡፡ ጨዋታውም በዜሮ ለዜሮ ውጤት ቀጥሏል፡፡
ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ ቅጽ 117 ሰኔ 9 ቀን 2004 (እ.ኢት.አ)
የሻሸ አረቄ ! የት ነዉ አቤ ? በጣም ደስ ይላል ጨዋታዉ ፤ ሻሸ ግን ተቃዋሚ ናት ወይስ ደጋፊ አቤ. . . ?
የወንድ ጠጪ ካላችሁ
ሰከሮ የልብ ማለት ካሰኛቸሁ
አደፋፋሪ የሻሺ አረቄ አለላችሁ
የባዕዱ የሗይት ሆርስ ይቅርባችሁ
ጥቁር ቢሆን እሰየው ነጭ ጠላ አይስማማችሁ
ሻሺ አረቄ (ቁንዲፍቲ) ይሁን ምርጫችሁ!!
ጨዋታው ቀጥሎ ውጤት ለማየት እንጓጓለን የምሕዳሩ መጥበብ ጉዳይ ገና መፍትሔ አላገኘም፤አራጋቢው ያዳላል፤የመሐል ዳኛው በሙስና ነው ቅጣት ምት ያልሰጠው፤አንዳንድ ተጫዋቾች ተገዝተው የገቡ አሉ፤በዳፍ በኩል የነበረው ደጋፊ በአነስተኛና ጥቃቀን (የቀን አበል እና ካኒቴራ) ተሰጥቶት ዕለቱን ድምቀት(ሙቀት) ሲፈጥሩ ውለዋል የሚሉ ተቃውሞዎች ተነስተዋል።
*አውራው ፓርቲ ግን በሙሉ ፍቃደኛነት እና በከፍተኛ ደረጃ ፺፮.፮ ድጋፍ አለኝ ይላል። ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ፸ ከመቶ ተቃዋሚው ጨዋታውን ተቆጣጥሮታል ብለዋል።
**ምርጥ ፲፩ በተደጋጋሚ ያሳየው የማጥቃት ሁኔታ ፪ ድጅት ከፍ ብሏል በሎ ቢመፃደቅም ደጋፊ(ቲቮዞ) ለማበዛት ያወጣው ፲፩ ከመቶ ወጪ ፓረቲው የመቆጠብ አቅሙን እንደ ውጭ ምንዛሪው ፲፯ ከመቶ ወደ ታች ያሽቆለቁላል ተብሎ ስለሚያስፈራ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ከወዲሁ መከፈት አለባቸው።ወጪን መገደብ ካልተቻለ ቢያንስ በአፍ መቆጠብ ጥሩ የመከላከያ ዘዴ ነው ሲሉ ለረጅም ጊዜ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ግለሰብ አስተያየታቸው ነው በለው!
***************************************
ለበለጠ ውጤት ከአራዳ ልጆች ማሽከርከርን ተማሩ
ጠጥታችሁ አትጫወቱ ! አታሽከርክሩ(አትሽከርከሩ)
አጋጣሚውን ከተገኘ የልባችሁን (ብሶታችሁን) ተናገሩ!!!!!!