(ይቺ ጨዋታ በትላንቱ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ወጥታ ነበር! ታድያ የብሎጋችን ታዳሚያንስ ለምን  አያነቡልኝም… እባክዎ ተቸገሩልኝ ወዳጄ…!)

ውድ የፍትህ ጋዜጣ ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ? ከዛሬ ነገ ብቅ እላለሁ እያልኩ ሳይሳካልኝ እየቀረ ተጠፋፍተን ከረምን እኮ! ፌስ ቡክ ሰፈር ግን በብዛት አለሁ። በየ ዕለቱ የሆነ ነገር ሳልል የዋልኩበት ጊዜ የለም። እንደውም ባለፈው ጊዜ “ኑ ፌስ ቡክ ሰፈር እንሰባሰብ” የሚል አንድ ጨዋታ ለእርስዎ ብዬ አዘጋጅቼ፤ ለአርብ ሳይደርስልኝ ቀረና ብሎጌ ላይ ለጥፌው ነበር። የፍትህ አዘጋጆች ከፈቀዱልንና ጨዋታው አዲሳባ ሌላ የህትመት ሚዲያ ላይ ያልወጣ ከሆነ እሱን ጨዋታ በሚቀጥለው ጊዜ እንቃመሰው ይሆናል።

ወደ ዛሬው ጨዋታችን ስንመጣ ለመንግስቴ አንድ አቤቱታ ማቅረብ ፈልጊያለሁ… እስቲ አብረን አቤት እንበል፤

እኔ አመልካቹ ግለሰብ ሀገራቸን በየጊዜው የምታወጣቸው አዎጆችን በደስታ የምመለከታቸው ሲሆን ለእያንዳንዱ አዋጅ ደግስ ደግሼ ዘመድ ጎረቤት ጠርቼ በደስታ እና በሀሴት ሳሳልፍ የኖርኩ ትጉህ ነኝ።

በአሁኑ ግዜ ሀገራችን በርካታ አዋጆችን እያወጀች እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ታላቅ የአዋጅ እመርታ አሳይታለች። ይህም ለቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እና ለሰላማችን የሚኖረው አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። እንዲሁም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መፋጠን፣ ድህነትን ለማጥፋት እና ለመሳሰሉት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች፤ አዋጆች በየጊዜው መታወጃቸው በእውነቱ አስደሳች ነው።

አሁን በቅርቡ የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ማጭበርበር አዋጅ ታውጇል። አዋጁን እንዳየሁት፤ ላካስ እስከዛሬ ስንጭበረበር ኖረናል! መንግስታችን ባይደርስልን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር!? ብዬ በእጅጉ አመስግኛለሁ።

ይህ የቴሌኮም ማጭበርበር፤  “ከኢኮኖሚያዊ ኪሣራ ባሻገር የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሆኗል” መባሉን ስሰማማ እስከዛሬ በሰላም መቆየታችን በእውኑ ከመንግስታችን የተነሳ ነው ስል አጥብቄ አመስግኛለሁ።

በተለይም በአዋጁ ውስጥ፤ “በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር የተያያዘ ሽብር የሚያስከትል መልዕክት ለማሰራጨት፣ ወይም በወንጀል ህግ የሚያስቀጣ አስነዋሪ መልዕክቶችን ለማሰራጨት በማንኛውም የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያና ኔትወርክ መጠቀም እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ 80 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል፡፡” የሚለውን ስመለከትማ የመንግስቴ ጥንቃቄ እና ዕቅድ ወለል ብሎ ታየኝ እና በደስታ ጮቤ ረገጥኩ።

በእውነቱ ከሆነ ይህው ጉዳይ እኔ አመልካቹንም በጣም ሲያሳስበኝ የከረመ ጉዳይ ነው። በተለይም ከአረቡ ሀገራት አብዮት በኋላ ልጅ ከአዋቂ ሳይለይ በየ ኢንተርኔቱ እተንጠለጠለ፣ መንግስቴን እያብጠለጠለ እና ጥሪውን እያቀጣጠለ በየቦታው “ለነፃነት ለፍትህ ተነሱ” እያሉ የሚተኩሱ የፌስ ቡክ ሸማቂዎች ተበረክታው በተመለከትኩ ጊዜ  ይህንን ማዕበል በምን እንቀቋቋመው ይሆን? ስል አብዝቼ ሳስብ ከርሜያለሁ።

በእውነቱ እኛ በየቀበሌው ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን ስናደራጅ አነዚሁ ወጣቶች ከሌሎች ጋር በመቀናጀት፤ በኮምፒውተር እና በሞባይላቸው በኩል በትላልቅ እና ከፍተኛ ሁኔታ ራሳቸውን ለአመፅ እና እምቢ ባይነት እያደራጁ እንደሆነ ስጠረጥር ከርሜያለሁ። “ያልጠረጠረ ተመነጠረ!” ያሉት ቤን አሊ ናቸው ወይስ ሙባረክ…? ጋዳፊ ይሆኑ እንዴ… ብቻ! እንጃ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው ነገሩ።

ነገር ግን ጠርጣራው መንግስታችን ቀድሞ በወሰደው አዋጅ የማውጣት እርምጃ በርካቶች በፌስ ቡክ እና በመሳሰሉት የኢንተርኔት ሰፈሮች ሲያጧጡፉት የነበረውን በሽብርተንነት አዋጁ የሚያስቀጣ አመፅ ቀስቃሽ የመረጃ ልውውጦች፤ ባይገታውም ማንኛውም የፌስ ቡክ አርበኛ በከባድ ጥንቃቄ እና ስጋት ውስጥ እንዲገባ አደርጎታልና አዋጁ ምስጋና ይገባዋል።

ታድያ ይህ አዋጅ የተሟላ ይሆን ዘንድ ከላይ በርዕሱ የተገለፁትን የማጭበርበር አደጋዎች የሚገታ ሌላ አዋጅ ቢወጣበት መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።፡

አንድ፤ የፀሎት ማጭበርበር አዋጅ

በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ በየ ቤተ ክርስቲያኑ እና በየ ቤተ መስጊዱ በሚሄድበት ጊዜ በፀሎቱ ምን እያለ እንደሚፀልይ መገመት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እንደኔ እምነት ይሄም በሀገሪቱ ላይ ታላቅ የደህንነት ስጋት ነው ብዬ አምናለሁ።

ምዕመኑ በየ እምነት ቦታው “በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር የተያያዘ ሽብር የሚያስከትል ፀሎት እየፀለየ እንደሆነ በምን ይታወቃል!? በእውኑ በየእምነት ተቋማቱ መንግስታችን ላይ ጉዳት እንዲደርስ ወይም ከመንበሩ እንዲነቃነቅ ወይም እንዲፈናጠር አምላክን የሚለማመኑ ግለሰቦች መበራከታቸው እኔ አመልከቹ መረጃ አለኝ፤ ይህም ፀሎትን ላለተፈለገ አላማ ማዋል ነው። ስለሆነም ወንጀሉ “ትልቅ በፀሎት የማጭበርበር ወንጀል” መሆኑ እንዲታወቅ እጠይቃለሁ።

ይህንን ለመከላከልም በፀሎት ማጭበርበርን የሚገታ አዲስ አዋጅ እንዲወጣ አቤት እላለሁ። በአዋጁ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በፀሎታ የማጭበርበር ወንጀል ለመፈፀሙ ወይም ሊፈፅም ለመሆኑ ፖሊስ ካመነ በድብቅ በሚደረግ የብርበራ ማዘዣ ፈቃድ ከፍርድ ቤት አውጥቶ አዕምሮውን እንዲበረብር ስልጣን እንዲሰጥም አመለክታለሁ።

ሁለት፤ የቁዘማ ማጭበርበር አዋጅ

መንግስታችን ከእንግዲህ ወዲያ በከተማው ውስጥ ኮምፒውተርን ወይም ስልክን በመጠቀም በ”ስካይፒ” ወይም በሌሎች መሰል ቴክኖሎጂዎች እየተደዋወሉ ከልብ ወዳጅ ጋር የሚደረግን ግንኙነት በአዋጅ መከልከሉ ይበል የሚያሰኘው ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደተገለፀው በኢኮኖሚ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በተጠቀሱት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የሚደረግ ግንኙነት ሰዎቹ ምን እየተባባሉ እንደሆነ ለማወቅ የማይቻል በመሆኑ፤ የሀገር ደህንነት ስጋትም እንደሚሆን በመታመኑ ነው።

ታድያ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቦቹ ከልብ ወዳጃቸው ጋር የሚያደርጉት ድብቅ ውይይት እንደመከልከሉ ከራሳቸው ልብ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ወይም ቁዘማ ለመጥፎ አላማ ሊያውሉት ይችላሉ ብሎ አመልካቹ ያምናል። ይህም ቁዘማን ላልታሰበለት አላማ በማዋል የቁዘማ ማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ያስችላል። ይህ  በቸልታ ከታየ የሀገሪቱ ደህንነት ስጋት መሆኑ አያጠራጥርም።

ለመሆኑ በዚች የጥጋብ እና የተድላ ሀገር ላይ አንድ ግለሰብ በመንግስት ላይ እያሴረ ካልሆነ በስተቀረ የሚቆዝምበት ምክንያት  ምን ሊሆን ይችላል? በመንግስት ላይ ማሴር ደግሞ በሽብርተኝነት አዋጁ የተከለከለ ነው።

ስለዚህም አንድ ግለሰብ በመንገድ ላይ፣ ወይም በቤቱ፣ ወይም በመስሪያ ቤቱ፣ ወይም በሁሉም ቦታ ከራሱ ጋር ሲወያይ ወይም ቁዘማ ሲያደርግ የተገኘ እንደሆነ ልክ በስካይፕ ወይም በሌላ ቴክኖሎጂ ከልብ ወዳጅ ጋር በድብቅ ሲወያይ እንደሚቀጣው ከሶስት እስከ ስምንት አመት ፅኑ እስራት እና እስከ ብር ሰማኒያ ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት እንዲጣልበት የመቆዘሚያ መሳሪያዎቹም በመንግስት እንዲወረሱበት የሚደነግግ አዋጅ እንዲወጣ እጠይቃለሁ።

ሶስት፤ የህልም ማጭበርበር አዋጅ

በአዲሱ የቴሌ ኮም ማጭበርበር አዋጅ ውስጥ “አለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን የአገር ውስጥ በማስመሰል (ኮልባክ) ወንጀል በየዓመቱ በበርካታ ሚሊዮን የሚገመት የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ እንድታጣ እያደረጋት” እንደሆነ ተጠቁሞ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦች እስከ አስር አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲበይንባቸው ያዛል። ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ…!

እኔ አመልካቹ ግለሰብ ደግሞ የህልም ማጭበርበር ከዚህም የከፋ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን የሚያሳጣ እንደሆነ ደርሼበታለሁ። ይህ በህልም ማጭበርበር ወንጀል ሰዎች በቴሌኮም ማጭበርበር አዋጁ የተከለከሉትን በሙሉ “እንደ ቪዲዮ ኮል”  እና “አለም አቀፍ ህልሞችን የሀገር ውስጥ አስመስሎ እንደማየት” የመሳሰሉትን ግንኙነቶች በቴሌ በኩል ብቻ ማድረግ ሲገባቸው በህልማቸው እንደልብ መመልከታቸው የቴሌን ገቢ በብዙ መልኩ የሚቀንስ ነው።

አንዳንዴም በፀረ ሽብር አዋጁ የተከለከሉ አመፅ የሚያስከትሉ መልዕክቶችን ከመለዋወጥም አልፎ በህልማቸው አመፁን እያቀጣጠሉ የሚያድሩ እንዳሉም በርግጠኝነት እናገራለሁ። ይህም ትልቅ የሀገር ደህንነት ስጋት መሆኑን አምናለሁ።

ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን የሀገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች በህልማቸው እየተፈፀሙ መሆኑ የታወቀ ወይም የተገመተ ከሆነ ግለሰቦች በድብቅ ህልማቸውን ለመበርበር በሚያስችል ፈቃድ በመታገዝ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ እንዲቻል፤ ቅጣቱም ዳግም ህልም በዞረበት እንዳይዞሩ የእድሜ ልክ እንቅልፍ ማጣት ውሳኔ እንዲሆን እጠይቃለሁ።

በነገራችን ላይ ከኛም የባሱ ለመንግስታችን አሳቢ የሆኑ ግለሰቦች ፊልም ላይ ክልከላ ማድረጋቸውን በቅርቡ ሰምቻለሁ። ይህም በጣም የሚያስመሰግን ነው። በኤድናሞል ሲኒማ ሲታይ የነበረው “ዲክታተር” የተባለ የፈረንጆች ፊልም ክልከላ ለዚህ ማሳያ ነው። ነገሩ የሚበረታታ ቢሆንም፤ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም ህብረተሰቡ ፊልም ቢከለከል ከሽብር ጋር የተያያዘ ህልም እያየ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነውና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አያይዤ አቤት እላለሁ!

ከሰላምታ ጋር! (ልበል እንጂ…!)

እስቲ ወዳጄ ጥሩውን ጊዜ ያምጣልን!

አማን ያሰንብተን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

11 responses »

 1. majesty says:

  ሃሃሃሃሃሃ… ግሩም እይታ ነው አቤ፡፡ ይሄ መንግስት የሚሰራው የጠፋው የአበደ ውሻ ሆኗል፡፡ ያበደ ውሻ ሁሉንም ይለክፋል፡፡ ቀበሌዎች የሚከተለውን አዋጅ ቢያወጡስ ማንኛውም የቀበሌያችን ነዋሪዎች ማታ ማታ ያያችሁትን ህልምም ይሁን ቅዠት በቀበሌያችን በሚገኘው የህልም እና ቅዠት መቀበል፣ መተንተንና ማደራጀት የስራ ሂደት በግንባር በመቅረብ ሪፖርት እንድታደርጉ ስንል እናሳስባለን፡፡

 2. Updater says:

  Abe, Skype is not prohibited. Where have u been? Adera don’t delete my comment. Do u think that being an opposition means opposing each and every aspect of government. Abe we should be careful to preserve our credibility. Betam weredkibign!

  • Dagmawi says:

   Have you read what is in the draft law or are you reading the latest government spin? It is clear they are trying to ban all VOIP communication. However, now that the entire world has noticed what an archaic and ass-backward government TPLF is they have started back-peddling. We will see what kind of law they will pass at the end. Maybe this will give the useless parliament an opportunity to look tough and reject some of the bullshit draft law they get from our Crime Minster/Prime Misery (executive branch)! Abe as always keep keepin’ on!

  • Ayichew says:

   ante degimo yetignaw wereda neh “werada” arfeh tirfirafihin eyeleqaqemik limatawi mengistihin bitamesegin yishalihal.

  • Nehemiah says:

   Ante yewetahew kaleh tibeqaleh.

   Bitch of Meles shut your board mouth up.

  • Buta madingo says:

   It is already band by the woyane government but they Dinnie in press conference last week but it is a law now under terrorist act to be jelled eight years in prison and or 80.000 Birr fine or maybe both so before you say some thing please make sure for every thing.Thank you.

 3. Negesse Mekonnen says:

  Abe nurilin!!!!!!!!!

 4. Dagmawi says:

  Updater – Have you read what is in the draft law or are you reading the latest government spin? It is clear they are trying to ban all VOIP communication. However, now that the entire world has noticed what an archaic and ass-backward government TPLF is they have started back-peddling. We will see what kind of law they will pass at the end. Maybe this will give the useless parliament an opportunity to look tough and reject some of the bullshit draft law they get from our Crime Minster/Prime Misery (executive branch)! Abe as always keep keepin’ on!

 5. Hundanol says:

  YET HEJE LIFENDA ALECH…. good job Abe!

 6. yelimatu tegoji says:

  ከድጡ ወደ ማጡ፡ ምን ነው አማካሪ ተብየወቹ ሚና የላቸዉም እንዴ?

 7. በለው! says:

  “አሁን በቅርቡ የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ማጭበርበር አዋጅ ታውጇል። አዋጁን እንዳየሁት፤ ላካስ እስከዛሬ ስንጭበረበር ኖረናል! መንግስታችን ባይደርስልን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር!? ብዬ በእጅጉ አመስግኛለሁ።
  ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መፋጠን፣ ድህነትን ለማጥፋት እና ለመሳሰሉት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች፤ አዋጆች በየጊዜው መታወጃቸው በእውነቱ አስደሳች ነው።”

  *እኔ የምለው ድሮ አባይ ግንድ ይዞ ይዞራል አልነበር እንዴ የሚባለው ? የዛሬው አባይ ገንዘብ ይዞ ይዞራል ያለው ማ ነው? አሳምኖም ይሁን አስፈራርቶ መንጠቁን ተያያዘው በጣም የሚገርመው ፍርድ ቤት የሄደ ሁሉ መክፈል (ቦንድ) መግዛት አለበትን? “መልዕክቶችን ለማሰራጨት በማንኛውም የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያና ኔትወርክ መጠቀም እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ 80 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል፡፡”??

  “በነገራችን ላይ ከኛም የባሱ ለመንግስታችን አሳቢ የሆኑ ግለሰቦች ፊልም ላይ ክልከላ ማድረጋቸውን በቅርቡ ሰምቻለሁ። ይህም በጣም የሚያስመሰግን ነው። በኤድናሞል ሲኒማ ሲታይ የነበረው “ዲክታተር” የተባለ የፈረንጆች ፊልም ክልከላ ለዚህ ማሳያ ነው። ”
  **ይህ እንኳን ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የታሰበ ሳይሆን ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመደጎም የተሸረበ (የተጎነጎነ)ሽሙጥ ነው። ምክንያቱም በሀገር ውስጥ የሚደረገውን ማሽሟጠጥ ለመግታት ቢቻልም አንዳንድ ፅንፈኛ ጋዜጠኖች “ዲክታተር” የሚል ማዕረግ ለመሪያችን ስለሰጡብን ወጣቱ ገንዘብ ከፍለን የፈረንጅ ፊልም ከምናይ ዋናውን በአደባባይ ቀርበን ማየቱ ተሻለ የኢኮኖሚ ቁጠባ እና ተጨባጭ ባህሪን መረዳት ለንቃተ ሕሊና መዳበር ሲጠቅም አልታይም ብሎ አንገት ማቀርቀር ወይም ለአንድ ወር መሰወር ይደብራል ሲሉ ደባሪዎችን ጠቅሰው ተደብረው ላዳበሩ ድብርተኖች መደበራቸውን ያስደበራቸውን ሰው ጠቅሰው እንዳይደብረው ይመችህ ሲሉ በአመቺው ቦታ ሁሉ በርካታ የሚመቹ ቃላቶችን ሳያሸበሩ ገልፀዋል። በቸር ይግጠመን በለው!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s