abetokichaw@gmail.com
ይቺን ጨዋታ ለፍትህ ጋዜጣ ልልካት አስቤ አላልቅ ብላኝ ስንት ጊዜ ሆናት መሰላችሁ፤ ቢያንስ ለዛሬ ይደርስልኛል ብዬ ነበር ሳይቻለኝ ቀረ። እንግዲህ የዛሬዋንም ፍትህ ለኔ አላላትም ማለት ነው! ብዬ ብሎጋችን ላይ ለጠፍኳት። ያነበበም ያስነበበም የተባረከ ነው!

ኑ… ፌስ ቡክ ሰፈር እንሰባሰብ!

እውነቴን ነው የምልዎ እንደኔ ጨዋታ ወዳድ እና ወሬ ለምን ያምልጠኝ ያሉ ከሆኑ፤ ወይም በዘመናዊ አጠራር መረጃ ምግቤ ነው የሚሉ ከሆነ፤ ያለ ምንም ጥርጥር ፌስ ቡክን የመሰለ ምርጫ የለም። ጨዋታ ቢልዎትስ ጨዋታ ብቻ ነው እንዴ…!?  መንፈሳዊ ቢሉ፣ አለማዊ ቢፈልጉ፣ ፖለቲካዊ ቢሻዎ… በያይነቱ ጨዋታ የት ነው የሚገኘው? ምንም ጥርጥር የለውም ፌስ ቡክ ላይ ነው። ከቤተ መንግስት ጀምሮ እስከ ቤተ ግለሰብ ድረስ ያለው ቡጨቃ ቀላል ነው እንዴ…? የምሬን ነው የተተነፈሰችዋ ሳትቀር አንዲትም ጨዋታ አታመልጥዎትም…!

ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ አዋሬ አካባቢ በ35 ሺህ ብር ወጪ ተሰርቶ የተሰቀለው ግዙፉ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢል ቦርድ መሰረቁን ከየት ሰማሁት? ምንም ጥያቄ የለውም፤ ከፌስ ቡክ ወዳጆቼ ነው። እዝች ላይ ግን አንድ አስተያየት አለኝ…

ከዚህ በፊት ጋሽ አርከበ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ ሲያደርጉ የተነሱት ፎቶግራፍ ፒያሳ ተሰቅሎ የነበረ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆዬ “እንዲህ አይነት የግለሰብን ገፅታ መገንበት ከድርጅታችን ህግ እና ስርአት ውጪ ነው።” ብለው ነገረውን አልነበር…? ታድያ አሁን ድርጅታችን ሰከረች ወይስ ተቃወሰች…? አዎና አንድ ሰው ወይ ሞቅ ካላለው ወይ ደግሞ ጨለፍ ካላደረገው በስተቀር የቀድሞ ውሉን እንደማይስት ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው። ወይ ደግሞ በግልፅ ቋንቋ “የኛ እንጂ የሌሎችን ምስል መስቀል ነውር ነው!” ብላለች ድርጅታችን ብንባል “ሙድ” አለው።

እውነቱን ለመናገር እኮ በአሁኑ ጊዜ ከኮሎኔር መንግስቱ ኃይለማሪያም በላይ የኮሎኔር መለስ ፎቶ እኮ በየቦታው እየተሰቀለ ነው። (ጠቅላይ ሚኒስትሬን ኮሎኔር ያልኳቸው ከመንግስቱ አላሳንሳቸውም ብዬ ነው። ምንም ቢሆን “አባይን የደፈሩ ጀግና” እኮ ናቸው።) እናልዎ በየቦታው የጠቅላይ ሚኒስተሩ ፎቶ ተሰቅሎ አንዴ፤ “አባይን የደፈሩ፣ አንዴ ኢትዮጵያን የደፈሩ” ተብሎ በመለጠፍ የሚወጣው ወጪ  ቀለላ አይደለም። ለነገሩ ግን ይሁን እድገታችን ለእርሳቸው ፎቶ የሚወጣውን ወጪ ካልሸፈነ ታድያ ለምን ሊሆን ነው!? እናም በጠቅላይ ሚኒስተሩ መሰቀል ተቃውሞ የለኝም! በደንብ ይሰቀሉ!

እናልዎ ወዳጄ በ35 ሺህ ብር ወጪ የተሰራው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢል ቦርድ መሰረቁን  የማስታወቂያው ሰራተኛው ወጣት ኢሳያስ በኢቲቪ “አርሂቡ” ፕሮግራም ላይ እንኳ ቀርቦ አልነገረንም። ለፌስ ቡክ ወዳጆቻችን እድሜ እና ኔትዎርክ ይስጥልኝና እነርሱ ናቸው ሹክ ያሉን።

ኔትዎርክ ብል ግዜ ትዝ አለኝ፤ መንግስታችን ውይ ረስቼው “ፀሐዩ መንግስታችን” ሳልለው እጅግ የሚያበራው፣ ከማብራትም አልፎ የሚሞቀው፣ ከመሞቅም አልፎ የሚያቃጥለው፣ ከማቃተልም አልፎ የሚፋጀው፣ ከመፋጀትም አልፎ የሚያፋጀው … (አሁን አሞግሳለሁ ብዬ ነገር ላመጣ ነው… አርፌ መንግስታችን ብዬ ልቀጥል) መንግስታችን ኔትዎችካችንን ከኤሊ የበለጠ ቀርፋፋ እያደረገው እንደሚያስቸግር መረጃ አለኝ ማስረጃ የለኝም እንጂ…

እኔ የምለው እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን የተለያየ የንግግር ፈሊጥ እየፈጠሩ አበላሹን አይደለ እንዴ…! ባለፈው ግዜ በፓርላማው ውስጥ ወደ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ እየተመለከቱ፤ “አሁንም ቢሆን በመደረክ ውስጥ አሸባሪዎች እንዳሉ መረጃ አለን ማስረጃ የለንም እንጂ!” ብለው ተናግረው ነበር። ይህው ከዛን ግዜ ጀምሮ እኔን ጨምሮ በርካታ ካድሬዎች ምን እኛ ብቻ በየድራማው ሁሉ፤ “መረጃ አለህ ማስረጃ ግን የለህም!” እያለን አጉል ፈሊጥ አብቅለን የለ እንዴ…!? እውነቱን ለመናገር አንደንድ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የቋንቋ ፈሊጥ አስተማሪ ሁሉ ይመስሉኛል። አረ እንደውም ተዳፈርካቸው አትበሉኝና ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ይልቅ ፈሊጠኛነታቸው ይበልጥብኛል!

ታድያ መንግስታችን ኔትዎርካችንን ያዝ ለለቅ እያደረገ በተገቢው ፍጥነት ወሬ እንዳንቀባበል አደረገን እያሉ የሚያማርሩ ወገኖች በዙ እንጂ ፌስ ቡክንማ የመሰለ የጨዋታ ቦታ፣ የወሬ መቀበበያ ስርፋ የትም የለም።

ያው ብዙዎች እንደምታውቁት ጥቂቶች ደግሞ እንደምትጠረጥሩት ከአረቡ ሀገራት አብዮት በኋላ በርካታ አምባገነን መንግስታት ህዝቦቻቸው ፌስ ቡክን ጨምሮ ሌሎችም ማህበራዊ ደረ ገፆችን እንዳይጠቀሙ፤ የቻሉ በቴክኒክ፣ የጨከኑ በጉልበት፣ ግፍ የፈሩ ደግሞ በፀሎት እየተከላከሉ  እንደሆነ ይታወቃል። የኛ መንግስት ከነዚህ የትኛውን ነው የሚጠቀመው? ብዬ አንድ ወዳጄን ብጠይቀው ምን እንደመለሰልኝ ያውቃሉ? (አንተው ካልነገርከኝ በምን አውቀዋለሁ ካሉ፤ ልንገርዎት…) “የኢህአዴግ መንግስት ሶስቱንም ዘዴዎች አጣምሮ ነው የሚጠቀመው ብሎኝ እርፍ!” ሰዉ እኮ ተናጋሪ ሆኗል ወዳጄ…!

ባለፈው ግዜ በአማራ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ፌስቡክን የሚመለከት አንድ ዝግጅት አሳይተውን ነበር። በዝግጅቱ ፌስ ቡክ ስራ የሚያባክን እንደሆነ እና እንደማያስፈልግ፤ በፌስ ቡክ የሚገኙ መረጃዎች አስተማማኝ እንዳልሆኑ፣ እንደውም መስሪያ ቤቶች ሰራተኞቻቸው ፌስቡክን እንዳይጠቀሙ ዘዴ መዘየድ እንዳለባቸው ሲመክሩን ነበር። ከዚህ ምን እንረዳለን…? ግልፅ ነው መንግስታችን ፌስቡክን ስንጠቀም ደስ አይለውም። ይቀፈዋል!

እኔ ግን እላችኋለሁ። ያለቻችሁን ትርፍ ግዜ በፌስ ቡክ መስኮታችሁ ብቅ እያላችሁ የሆናችሁትን ንገሩን የሆነውንም ስሙ። ማዶ ለማዶ ብንሆንም በፌስ ቡክ ላይ እንሰባሰብ።

በነገራችን ላይ አሁን አሁን ፌስ ቡክ የትግል ሜዳም እየሆነ ነው። በኢትዮጵያ ምድር የተከለከለው ተቃውሞ በተለያዩ አውደ ግንባሮች ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል። (እንደ አውደ ግንባር የተቆጠሩት የተለያዩ የፌስ ቡክ ግሩፖቻችን ነው።) ባለፈው ግዜ አንድ ስሙን የዘነጋውት የፌስ ቡክ ወዳጃችን “ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ መብቴ መብራት ሲመጣ ሆ! ብሎ መጮህ ነው!” የሚል አስተያየት ለጥፎ አይቼዋለሁ። በፌስ ቡክ ላይ ግን የሚከለከል መብት የለም።
አዛዡ ሞራሉ ብቻ ነው። አዕምሮ ላለው ሰው ሞራልን የመሰለ ጥሩ ገዥ የት ይገኛል? እንደውም ሌላ ሰው ሳይቀድመኝ አዲስ አባባል ልፈጥርማ… “የገባው ሰው ከመሪዎቹ ይልቅ ሞራሉ ይገዛዋል” አደራ በስሜ ይመዝገብልኝ!

እናም ፌስ ቡክን ጥሩ መዋያ እና መደራጂያ ሰፈር ነው። ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወጣቶችን ሲመክሩ “ሶስት ምክር ልምከራችሁ አንድ ተደራጁ፣ ሁለት ተደራጁ፣ ሶስት ተደራጁ” ብለው ነበር። በርግጥ እርሳቸው የሚፈልጉት በጥቃቅን እና አነስተኛ ብቻ እንድንደራጅ ነው። እኔ ግን ከጥቃቅን እና አነስተኛ ከፍ ባለ መልኩ እንደራጅ እላለሁ። ተደራጅተን እናውጋ…! እንዋጋ አላልኩም። እናውጋ፣ እንወያይ። ከዛ ውይይታችን ወደሚመራን ቦታ አብረን እንጓዛለን!

ወዳጅነታችን ለዘላለም ይኑር! ልዩነታችንም አብሮን ይዝለቅ (መጋደያችን አይሁን እንጂ)
በለው የዛሬው ጨዋታ የአቋም መግለጫ ነው የሚመስለው ልበል ወይስ አልበል!?
ቻሉኝ እንግዲህ!
ሰላም ይግጠመን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

12 responses »

 1. Dertogada says:

  “የገባው ሰው ከመሪዎቹ ይልቅ ሞራሉ ይገዛዋል”

  ይህ ሰው፤ ማለትም ሞራሉ የሚገዛው ‘ሰው’ በእኔ እይታ እንዲህ አይነት ሰው ይመስለኛል………..
  በመንፈሣዊ ሕይወቱ፣ በአለማዊው እውቀቱ የጎለበተ፤
  ከነስብዕናው ያለ፣ ማንነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ፤
  ሰው የመሆን ሚስጥር የገባው፣ በሕገ አራዊት የማይመራ፤
  እይታው ከሞራል መለኪያ አንፃር የሆነ፤ (His/her judgments are in terms of Moral Values.)
  ይህ ‘ሰው’ ሃገሩን ወዳድ፤ የወገኑ ችግር፣ስቃይና እንግልት የሚያንገበግው፤ ስለ ሃገሩ እና ስለ ወገኑ ነፃነት ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሃያል ሰው ስለመሆኑ ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለውም፡፡

  እግዚሃብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!!
  እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ያብዛልን፡፡

 2. Abi says:

  Abetokichaw, the brilliant writer!! I like the way you discribe things, very much.Keep it up.

 3. ሽብር ሽብር ፧ ይላል ፡፡ says:

  በጠቅላይ ሚንስትሩ መሰቀል ተቃውሞ የለኝም ፡፡ በደንብ ይሰቀሉ ፣፣፣፣፣፣፣፣ ወይ አቤ ግሩም አባባል ፡፡

 4. aziz says:

  እናልዎ በየቦታው የጠቅላይ ሚኒስተሩ ፎቶ ተሰቅሎ አንዴ፤ “አባይን የደፈሩ፣ አንዴ ኢትዮጵያን የደፈሩ” ተብሎ በመለጠፍ የሚወጣው ወጪ ቀለላ አይደለም። ለነገሩ ግን ይሁን እድገታችን ለእርሳቸው ፎቶ የሚወጣውን ወጪ ካልሸፈነ ታድያ ለምን ሊሆን ነው!? እናም በጠቅላይ ሚኒስተሩ መሰቀል ተቃውሞ የለኝም! በደንብ ይሰቀሉ! arefe ababl temcghe

 5. aziz says:

  abyey yah demo betame yaskadal ጠቅላይ ሚኒስትራችን “ፀሐዩ መንግስታችን” ሳልለው እጅግ የሚያበራው፣ ከማብራትም አልፎ የሚሞቀው፣ ከመሞቅም አልፎ የሚያቃጥለው፣ ከማቃተልም አልፎ የሚፋጀው፣ ከመፋጀትም አልፎ የሚያፋጀው …

 6. Dokle says:

  አርእስቱ ኤዲት ይደረግልን!!….አንሰባሰብ……እንሰባሰብ:: ጽሑፉ አሪፍ ነው አልልም:: አሪፍ ያልሆነበት ቀን ስላልነበረ::

 7. በለው! says:

  መልካም ነው ብለናል! ተለያዩ ስትባሉ እንሰብሰብ ማለት ከዚህ የበለጠ ያቋም መግለጫና መገለጫ ከየት ይምጣ ?

  ጠ/ሚኒስትራችን “የግለሰብን ገፅታ መገንባት ከድርጅታችን ህግ እና ስርአት ውጪ ነው።” ብለው ነገረውን አልነበር…? “በግልፅ ቋንቋ “የኛ እንጂ የሌሎችን ምስል መስቀል ነውር ነው!” ማለታቸው ነበር…ከኮሎኔር መንግስቱ የሚያንስ ጀብዱ ያላቸው አይመስልም እንደሰሞኑ የደጋፊዎቻቸው ማሽቃበጥና ማሽቋለጥ…”ጦርነት ሲነሳ ድንበር አቋርጠው ኤርትራ የቀበሮ ጉድጓድ ተደብቀው ተገኙ “የሚለውን “መድፍ ሲያገላብጡ የነበሩ ናቸው አይፈሩም ፤አልደነገጡም፣አይደነግጡም ይላሉ… ስለዕውቀታቸውና የማንበብ ክህሎታቸውም ሲመሰክሩ “መድፍ ተደግፈው ጦርነት ውስጥ ሲያነቡ የነበሩ ናቸው” ይላሉ ሲያነቡ የሚለው ሲያ’ነቡ ብላችሁ አልቃሻው መሪያችን ብላችሁ እንዳታማርሯቸው በሰንበት !የኮሎኔር ማዕረግ አንሰጥም ካላችሁ ይገጠምላቸው …
  ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
  መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
  መለስ ብለን ስናይ ተደገፈ ብቻ ።

  “መረጃ አለህ ማስረጃ ግን የለህም!” አትበሉኝ ከዕንባ ጠባቂ ወዳጃቸው ከአቤ ቶኪቻው ከ…. በላይ! ከ….በታች !
  “እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የቋንቋ ፈሊጥ አስተማሪ ሁሉ ይመስሉኛል። አረ እንዲያውም ተዳፈርካቸው አትበሉኝና ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ይልቅ ፈሊጠኛነታቸው ይበልጥብኛል!”

  *ፈሊጣቸውን ጠንቅቃችሁ ለማወቅ፤ ለማሳወቅ፤ገብቶአችሁ ለማስገባት ፍቃደኛ የሆናችሁ ተደራጁ ።
  መብራት ሲመጣ ሆ !ማለት መብት ካላችሁ ሲጠፋም በጋራ ሆናችሁ ‘እልል’ እልል’ በሉና በድምፃችሁ መብራት ፍጠሩ “እያነቡ እስክስታ ነው ያላችሁት” ? ? ዝም አትበሉ ደውሉ ? የአባይ ወንዝ የተገደበው ለመብራት እንጂ ለመብላት አደለም! አባይ እንኳ ሲፈስ ድምፅ አለው!! ከአነስተኛ እና ጥቃቅን… ታላቅነት እና ጥልቅነት !!!
  በቸር ይግጠመን ! በለው!

 8. ወይ ኑሮ says:

  ወይ አቤ ኔትዎርኩ ቀርፋፋ ሆነ ነው ያልከው? ጥሩ ብለሃል ግን ማን ነገረህ ባክህ? እኔ አሁን ይቺን ያንተን ወሬ ለማንበብ ምን ያህል ሰዓት እንደቆየሁ አልነግርህም፡፡በነገራቸን ላይ ቴሌ ያለ አግባብ ብር እየወሰደብን ነው፡፡10 ብር የነበረው ስልክ ከደቂቃ ወሬ በኋላ 10 ሳንቲም ይቀረዋል፡፡ነገሩ እንዴት ነው ስንል ደግሞ 10 ሳንቲሙ 4 ወይም 5 ብር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡በርግጥ መመለሱ ደስ ቢያሰኝም የተመለሰው ግን የተወሰደውን ያህል መሆኑ አይታወቅም፡፡እኔ ይቺን የቴሌን ሌብነት ልማታዊ ስርቆት ብያታለሁ፡፡ያው መቼም ለልማት እንጂ ለጥፋት አይሰርቁም ብዬ እኮ ነው፡፡

 9. […] ቶኪቻው ኑ… ፌስ ቡክ ሰፈር እንሰባሰብ! ይላችኋል:: ለምን ብትሉ አንድ አንቀጽ […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s