ዛሬ የግጥም አዚም በላይ ላይ ሰፍሮ ነበር። (እውነቴን ነው አይሳቁ ወዳጄ…)  ታድያ ውረድ አትውረድ ስታገል ከቆየሁ በኋላ በዚህ መልኩ ግጥም ሳይሆን ግጥም ብጤ ሆኖ ወረደ። ታድያ ከእርስዎ ደብቄ አጀንዳዬ ላይ የማስቀምጠው ምን ጉዳይ አለኝ…?  አልኩና እነሆ በረከት አልኩኝ…!

ማሳሰቢያ ይህንን ግጥም ለየት የሚያደርገው ግልፅነት እና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ እርማቱ ፊት ለፊተችሁ መደረጉ ነው…!

ርዕሱ ምን ይሁን…? በነገራችን ላይ ለግጥም ርዕስ ማውጣት ከባዱ ስራ እንደሆነ እውቅ ገጣሚያን ሁሉ ሲናገሩ ሰምቼ አውቃለሁ። ስለዚህ ርዕሱ ቢከብደኝም ብርቅ አይደለም ማለት ነው። “ኦ… ርዕስ ከየት አለህ አንጀት አርስ…” አያችሁልኝ ግጥም እንዴት እንደሚዥጎደጎድልኝ…!  ዛሬማ ወሬዬ በሙሉ በግጥም ሳይሆን አይቀርም።  ለማንናውም ርዕሱን ምን ልበለው….?  በቃ ባዶውን ከሚሆን፤ “ተዉት አትምከሩት”  ብዬዋለሁ። እንጀምር…

ተዉት አትምከሩት

ተዉት አትከልክሉት ያብዛብኝ መከራ።

ችግሬን ያግዝፈው እንደ ዳሽን ጋራ!

ይዝለፈኝ፣

ያሳደኝ፣

ያግዘኝ፣

ይግረፈኝ፣

ዝም በሉት ብቻ፤

ያረገኝ መጫወቻ።

“ይሄን አስተካክል ይሄን ባክህ አርቅ” ብላችሁ አትምከሩት

ብትመክሩም ላይሰማ

ምን አስጨነቃችሁ ለዚህ ለገገማ… (… እዚህ ጋ የምር ሳቄ ነው የመጣው። “በግጥም የተማርናቸው እነ ቃላት መረጣ ምናምን የሉም እንዴ…?” ብለው እርስዎ ወዳጄ አጓጉል ሲተቹኝ ታወቀኝ። ሌሎችም “ሆድ ያባውን ግጥም ያወጣዋል” ብለው ሲተርቱብኝ ወለል ብሎ ታየኝ። ይቅርታ ጠይቄ ቀጥሎ የተሻለ ስንኝ ለማምጣት እሞክራለሁ…!

“ይሔን አስተካክል ይሄን ባክህ አርቅ” ብላችሁ አትምከሩት።

ብትመክሩም ላይሰማ፣

የሚያደርገው ሁሉ በርሱ ቤት እውቀት ነው፤

የመሰልጠን ማማ!

ስለዚህ ዝም በሉት ለማረም አትሹ፣

ላይሰማችሁ ነገር፤ አፍ አታበላሹ፣

              ቃል አታኮላሹ፣

ለእርሱ ሽብር ወሬ ለእርሱ ድንፋታ፤

መልሱ ነው ፀጥታ፣

ዝም ያለ ዝምታ።

ያንጠባጥብ በደል፤

ያጠራቅም መከራ፤

ፅዋዬ እስክትሞላ፤

ያኔ እርሱን አያድርገኝ!

አይኑን አያሳየኝ።

የበደል ፅዋዬ ሞልታ ከፈሰሰች፣

እንኳን እርሱን እና አለም ታፀዳለች!

(ይሄን እርሱም ያውቃል)

ስለዚህ ዝም በሉት ያብዛብኝ መከራ፣

ጠራርጋ የምትወስደው ፅዋዬ እስክትሞላ!

ትንሽ አመረርኩ አይደል…? እንግዲህ ምንም ማደረግ አይቻለም የግጥም ውቃቢ በላይዎ ላይ ሲያድር በል ያልዎትን ነው የሚሉት። እናም ይህንን የተናገረው በላዬ ላይ ያደረው ነውና!  መረረ ጣፈጠ ለእርሱ ትቻለሁ!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

5 responses »

  1. elshanovoski says:

    i like ur WUKABE….ENDE JEMARI TIRU GITIME NEWU TINISHE BABIZAGNAWU YEGITIMIHE MECHERESHA LAYE “HARABIE(4TH) AND HASADISE(6TH) TABEZALEHE..YIMESILEGNALE ፅዋHE እስክትሞላ EYETEBEKE NEWU ….የበደል ፅዋHE ሞልታ ከፈሰሰች HULUNIME KALOCHE YEMITITEKEME YIMESILEGNALE

  2. ተዉት አትከልክሉት ይህንን ተልካሻ
    ይሰረን፣ ያባረን ያሳጣን መድረሻ
    የበትሩ ብዛት ያበረታል እንጂ አያዳክመንም
    የጥላቻው ብዛት አንድ ያረጋል እንጂ አይበታትነንም
    በስተመጨረሻ፣ ሆ ብለን ስንወጣ
    ያን ጊዜ ፍርዳችን ያየኸው ተቀጣ::
    —— ኡኡቴ ግጥም (ሐሳቡ ይበቃል)

  3. Abel says:

    የእኔው ጅኒ ደግሞ እንዲህ በል አለኝ፡-
    ጠላቴ አትተወኝ፣
    በደምብ አርገህ ምታኝ፤
    አጥብቀህ ቀጥቅጠኝ፣
    የዞርኩብህ ዕለት ምላሹ እንዳያንሰኝ።

  4. Kulich says:

    I wish I could add more :)))

  5. በለው! says:

    እኔስ ተው እላለሁ…!

    ዝም አልልም ገደል ሲገቡ እያየሁ
    ሕዝብ ይሰማ ይከበር በዝቷል መከራ
    ኑሮው ከፍቷል ድሎት አይዘንብ በተወራ
    አትዝለፉት… ይህ ሕዝብ ታጋሽ ነው
    አታሰድዱት… ይህ ህዝብ መብት አለው
    አትሰሩት… ሲውለድም በነጻነት ነው
    አትናቁት… የአለም ህዘብ የሚያውቀው ታሪክ አለው
    አትግረፉት… በባሕል በሐይማኖት የታነፀ ነው ።

    እኔስ ተው እላለሁ…!

    ይህ የዋህ ድሃ ሕዝብ አደለም መጫወቻ
    ፅዋው ሲደርስ እናንተን አያድርገኝ ብቻ
    ሁሉም ዕኩል ድርሻ አለው በሀገሩ
    የመሥራት የመጻፍ የመናገር መምህሩ
    ጋዜጠኛው ሠራተኛው ተማሪ አረሶ አደሩ
    ሳይለይ በፆታ በዕድሜ በሃይማኖት ሳይጠቀስ ዘሩ።

    እኔስ ተው እላለሁ…!

    ልባችሁ የአይጥ ጆሮአችሁ የዝሆን
    ውይይትን ልመዱ ማር እሰጥ አገባን
    ዕውቀታችሁ ይፈተሽ እንደወረደ ኩረጃችሁ
    እራሳችሁን አድንቃችሁ ተመልካች ሳቀባችሁ
    ቤታችሁ ሆኖ የሁሉን አውቃለሁ ማሳ
    ማረም ካልተቻለ ቢነቀል እሳ ?
    እኛም ታከትን ሁሌ ተው ማለትን
    ለሚቀርቧችሁም መልዕክት ንገሩ አልን
    ጆሮአችሁ ሲያፈስ በቃ ማለትን
    ጎረመሳችሁ ጠገባችሁ ይዛችሗል መበተንን
    ልንያያዘው ነው “እንቢኝ”ማለትን
    ከቤታችሁ በላይ ቀፎ ሠቅላችሁ
    ቅን ብትሆኑ ተማሩ ነው ያልናችሁ።

    እኔስ ተው ተውን እላለሁ…!

    >>>>በ>>>>ለ>>>>ው>>>>!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s