abetokichaw@gmail.com

በመጀመሪያም

ጋሽ ግርማን አየኋቸውኮ!

በዛን ሰሞን “ሞቱ” ተብሎ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ከተውን የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ድንገት ተከስተው “እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሳችሁ” ብለው ፡”ሰርፕራይዝ” አድርገውናል። ትንሽ ሸንቀጥ ቢሉም እየተነፈሱ እንደሆነ በማየታችን እኛም ከመቀመጫችን ብድግ ብለን “እንኳን አብሮ አደረሰን!” ብለናቸዋል።

ኢህአዴግ አዲሳባን ከተቆጣጠረ 21 ዓመት ሞላው። ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ ጠዋት አዲሳባ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላታል። ለገና እና ለመውሊድ 9 ጊዜ ብቻ እንጂተኮስ የተወሰነው መድፍ ለኢህአዴግ ልደት ሃያ አንድ ግዜ መተኮሱ መንግስት “ከሁሉ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” ሊለን ፈልጎ እንደሆነ ግልፅ ነው።

እንግዲህ ኢህአዴግ አሁን በደንብ ጎረመሰ ማለት ነው። ይህ ወቅት ጡንቻ የሚፈረጥምበት ጢም የሚቀመቀምበት ከመሆኑም በላይ እግዜር ላልባረከው፤ ልብ የሚነፋበት ጆሮ የሚደፈንበት አስቸጋሪ ወቅት ነው። በዚህ ዕድሜ ላይ ያለ ያልተባረከ ጎረምሳ ኮረዳዎች “ሳመኝ” ሲሉት እንጂ አዋቂዎች “ስማኝ” ሲሉት ጥሪ አይቀበልም። ከላይ ከላይ መናገር እና ከኔ በላይ ላሳር ማለት ልዩ ባህሪያቱ ናቸው። (አይ ጉርምስና!) እናም ኢህሃዴግ አሁን ዋናው የአፍላ ጉርምስና ወቅቱ ላይ ይገኛል። በአራዶች ቋንቋ “ፍንዳታ” ሆነ የሚባለው ማለት ነው። ወደ ጨዋታችን ዘልቀን ከመግባታችን በፊት “ኢህአዴግዬ ጉርምስናውን በቅጡ ያድርግልህ” ብለን እንመርቀዋለን!

“ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬድዬ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ግንቦት 20 ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት አመተ ምህረት!” የተባለ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነትን እና አባታችን ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለው ቴሌቪዥናችን በአሁኑ ግዜ ዋና የኢህአዴግ ፓስር ሆኖ ስብከቱን ሲያሰማ ውሎ ያድራል። በተለይ ሰሞኑን ኢህአዴግ ጉርምስናውን ሲያከበር ኢቲቪ ውዳሴ እና ዝማሬ በማዝነብ የሚስተካከለው አልተገኘም። እኛም በተለይ ከህዝቡ ዘንድ የተደበቀውን ጥጋብ ለመየት የታደለው ኢቲቪ ይህንን ይመለከት ዘንድ የተቻለው “እንደምን ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መንፈስ ቢሰርፅበት ነው!?” ስንል አድንቀናል።

አፈር ስሆን ትንሽ ቆየት ባለ ጨዋታችን ላይ ያወጋነውን የአንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ገጠመኝ እዝች ጋ እናምጣት፤

ጋዜጠኛው በልማታዊ ዘገባ የሚታወቅ ነው። ፐርሰንትን ማውራት ለጥጋብ የሚዳርግ ቢሆን ኖሮ ከሁሉም በላይ ይህ ጋዜጠኛ ለመንደሩ ሰው ሁሉ ጥጋብን የሚያከፋፍል በሆነ ነበር። የሆነ ግዜ ቤቱ እንግዳ መጣበት። ከዛም በአባወራ ደንብ ሳሎን ቁጭ ብሎ “እስቲ ምሳ አቀራርቢ” ብሎ ለሚስቲቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ከእንግዳ ጋር ይመጣል ብላ ያልገመተች ሚስትም “ምናባቴ ይሻለኛል ባዶቤት እንግዳ ይዞብኝ መጣ…!” ብላ እየተጨነቀች ለእርሱ የተዘጋጀውን እንደነገሩ የሆነ ምሳ አቀረበች። አባወራ ሆዬ እንገዳውን፤ “ብላ እንጂ አልጠፈጠህም እንዴ?” ብሎ አየጋበዘ አንገቱን ወደ ጓዳው ቀለስ አድርጎ “ትንሽ ቅቤ ጣል አድርገሽ ወጥ ጨምሪልን እስቲ…” ሲል አዘዘ። ሚስት ክው ብላ እየደነገጠች እንግዳ ፊት “ከየት አምጥቼ…” አይባልም እና፤ “እሺ” በማለት እዛው ጓደ ቁጭ አለች።

ባልም ትንሽ ከእንግዳው ጋር ከተጨዋወተ በኋላ “የት ጠፋሽ አረ እንጀራም ጨምሪልን እንጂ…” አለ እና “ይሄውልህ ያ አለቃችን ደግሞ…” እያለ መውጋቱን ቀጠለ። ሚስት “እሺ መጣሁ” ብላ አሁንም ጓዳዋ ቁጭ ማለትን መረጠች… ቢጠብቋት… ቢጠብቋት አትመጣም፤ ከዛ ባል ሆዬ “የት ሄድሽ ቡናስ አታፈይልንም እንዴ…?” ብሎ ተጨማሪ ትዕዛዝ ቢያዛት ከቡናው ቀድሞ ደሟ ፈልቶ እየተብከነከነች፤ ጓዳዋ ኩርምት ብላ ቁጭ! በዚህ ግዜ ባል እንግዳውን ሳሎን ጥሎ “ቀረሽ እኮ!” እያለ ወደ ጓዳው ሲገባ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ “ስማ እንጂ ይሄ እኮ በኢቲቪ የምታሳየው የልማት ፕሮግራምህ ሳይሆን መኖሪያ ቤትህ ነው… ቅቤ ጣል አድርጊ፣ እንጀራ ጨምሪ፣ ቡና አፍዬ… ትለኛለህ ቤቱ ባዶ እንደሆነ አታውቅም…!?” በማለት ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።

የኢቲቪ ጋዜጠኞች በቤታቸው የሌለውን ምቾት በሀሪቱ ሞልቶ ተትረፍርፏል ብለው ሲሰብኩን ትንሽም ድንቅፍ አይላቸውም። ይሄ በእውነቱ ከፍ ያለ “ምንፍስናን” የሚጠይቅ የፃድቅ ሰው ስራ ነው።

የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ከመቼውም ግዜ በበለጠ ቴሌቪዥኔ ዋና ካድሬ ሆኖብኝ ከርሟል። ላለፉት ስምንት አመታት ተከታታይ እደገት ማሳየታችንን፣ አራት ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ማከናወናችንን፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጣችንን፣ በምግብ ምርት ራሳችንን መቻላችንን፣ ከአገር አልፈን የአፍሪካ መኩሪያ መሆናችንን አስረግጦ ነግሮኛል። (“ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ የት ነበርኩ!?” ብለው እንዳይጠይቁኝ ብቻ)

እኔ የምለው ግን ኢህዴግ ይህንን የጉርምስና ግዜውን በሚያከብርበት ወቅት አዲስ ስድብ ማስመዘገቡን ልብ ብላችሁልኝ ይሆን? “ሟርተኛ” የሚለውን ስድብ በቴሌቪዥኔ ስንት ግዜ እንደሰማሁት ለመቁጠር ፈልጌ ደክሞኝ ነው ያቆምኩት። ይህንን ስድብ ከኢህአዴግ አደረጃጀት ሃላፊው አቶ ሬድዋን ጀምሮ ሁሉም ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች እንደየ ሃላፊነታቸው መጠን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ሰምቼ አንድ ስድብ ላይ ከሚሻሙ ለምን፤ “መተተኛ” “አስማተኛ” “ድግምተኛ” “ሰላቢ” እና የመሳሰሉትን ተመሳሳይ ስድቦች እየቀላቀሉ አይጠቀሙም? ስል ተጨንቄላቸዋለሁ። ለነገሩ ለቀጣዮቹ ግዚያት እንቆጥብ ብለው እንጂ ከእኔ ያነሰ የስድብ ዕውቀት አላቸው ብዬ አላስብም። እውነትም ደግሞ ቁጠባን ባህል ማደረግ ጥሩ ነው።

ለማንኛውም ዛሬ የኢህአዴግ ልደት ነው። ልደቱን አስመልክቶ ምን ያህል ጥጋብ እና ተድላ ላይ መሆናችንን መንግስታችን ነግሮናል። አልጠገብንም ብሎ መከራከር አይቻልም። በአገሪቱ የመፃፍ እና የመናገር ነፃነት ያለ ምንም ገደብ እንደተፈቀደም ተነግሮናል። የለም እየታፈንን ነውኮ! ብሎ መጨቃጨቅ አይቻልም። ምንያቱም ይሄ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ጠግባችኋል ተብለናል። አዎ ጠግበናል። ዴሞክራሲ ሰፍኖላችኋል ተብለናል አዎ ሰፍኗል።  እግዜር ይስጥልና! (ይቺ እግዜር ይስጥልና እንዴት ያለች ምርቃት መሰለቻችሁ…!?)

ከሁሉ የሚያስገርመኝ 1

ህገ መንግስቱ

ኢህአዴግ እጅግ በጣም ከሚመካባቸው ትህምክቶቹ መካከል “ህዝብ ተወያይቶበት” ያፀደቀው ህገ መንግስት ባለቤት አደረኳችሁ” የሚለው ይገኝበታል። ነገር ግን በዚህ ወቅት በርካታ ተንታኞች ኢህአዴግ ራሱ ህገ መንግስቱን እያከበረ እንዳልሆነ ይናገራሉ። (እንደው ለትህትና ተንታኞች አልኩ እንጂ እኔ ራሴ አረ ብዙ ታዝቤያለሁ)

ህገ መንግስቱ “ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረኑ ማነኛቸውም አዎጆች ደንቦች እና መመሪያዎች ተቀባይነት የላቸውም” ይላል። ግን ማን ይሰማዋል…? መንግስታችን የሚያወጣቸው የተለያዩ አዋጆች እና መመሪያዎች ህገ መንግስቱ ከሚለው በተቃራኒ እየታወጁ እና ተግባራዊ እየተደረጉ ተመልክተናል። በትሹ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት በተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች “ተከልክሏል” ለማለት ያስደፍራል። የቅርብ ግዜ ምሳሌ ብናመጣ እንኳ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ዳግም የታሰረች ግዜ ደጋፊዎቿ ሰልፍ ሊወጡ ሲሉ “ከ250 በላይ ሰው ማሰለፍ አይቻልም” ተብለዋል። በአዲሳባ “መድረክ” የመሰብሰቢያ አዳራሽ አጥቶ ሁልግዜ ኡኡታውን የሚያሰማው ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን መመሪያ ሰለባ በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጪ ሀገር ተቃውሞ ሰልፍ እና የህዝብ ቁጣ ሲያጋጥማቸው “ክው” የሚሉት። ሀገር ውስጥ ቢፈቅዱልን ይለምዱት ነበር። (የሚሉ ወገኖች አሉ ብለው ይጨምሩልኝ)

በደንብ እናጥና ካልን ሌሎችም መመሪያዎች እና አዋጆች ህገ መንግስቱን ሲረመርሙት ማየት ብርቅ አይደለም። በቅርቡ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እንኳ ከአቅሟ የማትመው “ፅሁፋችሁን መጀመሪያ መርምሬ ነው” ብላናለች! አረ ህገ መንግስቱ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱርን) ይከለክላል ብለው ዋይ ዋይ ቢሉ “ይሄ የማተሚያ ቤቱ መመሪያ ነው” ይባላሉ!።

ከሁሉ የሚገርመኝ 2

ኢህአዴግ ልደቱን ባከበረ ቁጥር የጦር ገድሉን አንስቶ አይጠግብም። በገድሉም ይህንን ትግል ለማድረግ ያነሳሳውን ምሬት እና ብሶት ደጋግሞ ያነሳል። ቀጥሎም ከዚህ ምን እንማራለን? ብሎ ይጠይቃል? በርግጥ መልሱ “አሁንም ብሶት ከበዛ ቆርጦ መታገል ነው” የሚል ነው። (በቅንፍ የትግሉን አይነት የሚመርጠው ታጋዩ እንደሆነ አስታውሳለሁ።) ግን ይህንን ጥያቄ መጠየቅ በዚህ ወቅት ተገቢነውን?

ከሁሉ ያሳቀኝ

አሁን የግንቦት 20 ልደት እያከበረ ያለው ኢቲቪ አንድ ነገር ሲናገር ሰማሁት “ከዚህ ቀጥሎ ምርጫ ከድምፅ ካርድ እንጂ ከጠመንጃ አፈ ሙዝ አይገኝም” የሚል ንግግር። እኔ የምለው “ተኳሾቹ” በምርጫ 97 የነበረውን ሰው በሙሉ ገድለን ጨርሰናል። ብለው ነው እንዴ ሪፖርት ያደረጉት… (አረ ፍሬንድ ወቅቱን የታዘቡ ብዙ አሉ!) “ከጠመንጃ አፈ ሙዙ ስልጣን አይገኝም…” የምሬን ነው የሳኩት… አሃ ምናልባት የአጋዚዎች ተኩስ የጠመንጃ አፈሙዝ አይባልም ይሆን…? ይቺ የጦር እውቀት ማጣት እኮ የምታስጠቃው ይሄኔ ነው!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

7 responses »

 1. betu says:

  ye 21 ametachiwe jemer enkone yedem gefetachiwen kefe selaregebachiw yechine amete yemechiresote ayemeselegem lol

 2. Mami says:

  የኢቲቪ ጋዜጠኞች በቤታቸው የሌለውን ምቾት በሀሪቱ ሞልቶ ተትረፍርፏል ብለው ሲሰብኩን ትንሽም ድንቅፍ አይላቸውም። ይሄ በእውነቱ ከፍ ያለ “ምንፍስናን” የሚጠይቅ የፃድቅ ሰው ስራ ነው።

 3. ጦቢያ says:

  አቤ በመንግስተኛ አቆጣጠር ጎርምስዋል ሳይሆን የሚባለው ወያኔ ጃጅቷል ነው የሚባለው:: ከጃጁ በኍላ ቀጥሎ እሚመጣውን መቼም ላንተ አልነግርህም ::

 4. mengistu says:

  gude belu enzh metatgch 21 amet molach gale weye amelaka wesat, kitefat ,gedgay ,zerfa egftsmu yehaw 77000 kenoch honcew BEKA ENBAL BEKA, BEKA ,BEKA ,BEKA ABE E/G YEBARKH TRU KEN YEMETALN YHONE?

 5. ሽብር ሽብር ፧ ይላል ፡፡ says:

  አዎ ኢሃዴግ ጎርምሶአል ፡፡ ጉርምስናውም ልቡን ደፍኖት የዜጎችን ብሶት መሰማት አቅቶታል ፡፡ በዚ የጉርምስና ጊዜው እልቆ መሳፍርት የሆነ ሰራ ጥፋት ሰርቶአል ፡፡ ኢሃዴግ እየጎረመሰ በሄደ ቁጥር ብዙ ሰው አገሩን ጥሎ ወደ ሰደት ሂዶአል ፡፡ ሌላው ዳግም ላይመጣ አሸልቦአል ፡፡ የጎረመሱት የኢሃዴግ መሪዎች በጥጋብ ሲኖሩ ፡ 80 ሚሊዮኑ ጨቅላ ህዝብ ግን ፡ በእራብ ፣ በሰቃይ ፣ በሰደት እናቱ ጥላው እንደሄደች ልጅ ያለቅሳል ፡፡
  ትክክል ነው ፡ ኢሃዴግ ጎርምሶአል ፡፡ በየትኛውም አገር ታይቶ የማይታወቅ ጉርምስና ነው የጎረመሰው ፡፡ ይህ ጉርምስናው ግን እንደ እሳት እራት አገርንም ፣ ህዝብንም ፣ እሳት ውስጥ መክተቱ ነው የሚያሳዝነው፡፡ ብቻ ፈጣሪ ጉርምስናውን ያብርደው ነው የሚባለው ፡፡

 6. በለው! says:

  አዎን በልታችሁ ለምታገሱብን፤ ጠግባችሁ ቁንጣን አላስችል ያላችሁ፤የምትናገሩ መስሎአችሁ ለምትተፉ፤ልማትን ከድህነት መለየት ለተሳናችሁ፤ያለጫማ መወለዳችሁን እረስታችሁ መሬትንም ሰውንም ከተጠየፋችሁ፤ “ኢህአዴግ አዲሳባን ከተቆጣጠረ 21 ዓመት ሞላው። ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ ጠዋት አዲሳባ 21ጊዜ መድፍ ተተኩሶላታል….” እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ይከብዳል እንኳን አደረሰንም ለማለት እናንተ ጣራ ስትነኩ ድሃው እዚያው በባዶ እግሩ ባለበት ይሄዳል!! የት ትደርሱ ይሆን ብለን…(ቆመናል)።
  ይቅርታ ባለፈው ወዳጅህን ” ሰውዬው እነዲህ በቀላሉ ሊደነግጡ መድፍ ሲያገላበጡ እንደኖሩ አያውቁም እንዴ!”
  ያለው ቤን ከበደ ለበዓሉ ድምቀት ሲያጎርሱ አይቷቸው ነው ?።

  ኢህአደግ ከሚመካባቸው ትህምክቶቹ መካከል “ህዝብ ተወያይቶበት” ያፀደቀው ህገ መንግስት ባለቤት አደረኳችሁ”ነው። “ያላዩ ልጅ ዳቦ ፍሪዳው ነው” አሉ ህገ መንግስቱን ለመጻፍ ሁለት ነገር ተሞርኩዘናል ይላሉ።ቀድሞ የነበሩ ህገመንግሰቶችን ፲፱፳፫ ፍትሀ ነገስት ፲፱፬፰ የተሻሻለውን ፲፱፹ የኢህድሪ.ከዚያ ተሳታፊውና ውይይቱ ቀጠለ፳፬/ ፲፱፰፬ ቻርተር ኮሚሽን….

  በተወካዮች ም/ቤት ፯ ድርጅት፤ መቀመጫ ከሌላቸው ፯ ፤ ሠራተኛ ማህበር ፫ ፤ ከመምህራን ማህበር ፪ ፤ ንግድ ም/ቤት ፫፤ የጤና ማህበር ፪፤ የህግ ማህበር ፪፤ የሴቶች ማሕበር ፫፤ በጠቅላላ ድምር ፳፱ አባላት ነበሩ። እነኝህ የብሔር ብሔረሰቦች ናቸው እንበል አስገራሚው የሀገሪቱ የባለ ድርሻ አካላት ኢንቨስተር (ተሞከሮ ያላቸው) የሚባሉት ግን ቁተራቸውን እንመልከት እና ሕዝቡ ይህ ህገ መንግስት ገብቶታል? ወያኔ ህገ መንግስቱን ተከትሏል? ወይስ ለራሱ በሚያመቸው መንገድ አስቀምቶታል ? በእርግጥ ህገመንግስቱ ትክክለኛ ቢሆን ሕዝብ በሕግ አምላክ ማለት ያቅተው ነበርን?
  የባለድርሻ ሀገራት ተሞከሮ እና ተሳትፎ ዛሬ የት ናቸው። የአሜሪካ የፖለቲካ ጠበብት(ጠበቆች) ፕ/ ሳሙኤል አንቲክተን አዲስ.አ.ዩ ፕ/ ጂም ፖል እና ሆም ፍሬር እንዲሁም ከፈረነሳይ፤ ከሕንድ፤ጀርመን፤ግሪክ፤ኖርዌይ፤ግብጽ፤ፓን አፍሪካ ኮነግረስ ተወካዮች ተሳትፈዋል። እነዲያውም አጼ ቴዎድሮስ ያለ ህገ መንግስት በጉልበት ኢትዮጵያን አነድ አደርጋለሁ ብለው ሲዞሩ ሲደክሙ እራሳቸውም አላረፉም ህዝቡም አነድ አልሆነም ችግር ፈጠሩ ይሏቸዋል።ወያኔ የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች እንዲሉ… ለአለፈፉት ፳፩ ዓመት ሱማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የድሃ ልጆች ጭዳ ይገበራል። ባለ ድርሻ ሀገራት በሕገ መንግስቱ ድምፃቸውን አጥፍተው ገለው ያላቅሳሉ እንደጻፉት ተጠቅመዋል።!!!!!

  በዓሉን አስመልክቶ ብሶት የወለዳቸው የጠ/ሚ አማካሪ ሰሞኑን ያሰሙት መግለጫ የ፳፩ ዓመቱን ግስጋሴ ሲጠቅሱ ዕንባ ይተናነቃቸዋል ሬዲዋን ሁሴን ፲፪ ዓመት “የተሐድሶ እንቅስቃሴ” ፱ ዓመት “ባለሁለት አሀዝ ዕድገት ተመዘገበ” ይላሉ። የጨለማው ዘመን ተገፎ ብርሃን ታየ ይላሉ ግለሰቡ ስንት ዓመታቸው ነው ? በዚያ የጨለማ ዘመን ተወልደው እንዲህ የሚያነበነቡ ከሆነ በጣም ያስፈራል። በዚህ ብርሃን ዘመን ተወልደው እንዲህ የሚቀሳፍቱም ከሆነ ቸኩለዋል ሰከን ቀዝቀዝ በሉ እንላለን። ሟርተኞች ሙሾ ሲያወርዱብን ዕድገታችንን የአለም ህዝብ እያደነቀው ነው የሚሉት ቧልት የዓለምን ምንነት ወይም ካርታውን ባለማወቅ እነጂ የመኸርና የበልግ ዝናብ በሌለበት ፹ከመቶ ድሃ ገበሬ በበሬና በዝናብ ጥገኛ ሆኖ ስለጥጋብ ማውራታችሁ በጣም ወራዳ እና ፈጣጣ ውሸታም መሆናችሁን ፳፩ኛውም ልደታችሁ መሰከረ።
  ሕዝብ ትልቅ የምግብ ዕጥረት ውስጥ እየሄደ ነውና ሳታዋርዱት ውረዱ ለዚያውም ያገማችሁትን ለማጽዳት ሌላ ፵ ዓመት ይፈጃል።!!! ለዛሬው እዚህ ያብቃ በበዐሉ ሰሞን ከተዋሹ ውሸቶች ላይ እንወያያለን :: እስከዚያው
  ፫ አፋልጉኝ…..
  የተወደዳችሁ አንባቢያን ባለፈው ለኦባማ ሁሴን “ከኢህአዴግ በተሰጠኝ ብድር የራሴን እና የቤተሰቤን ኑሮ ለመለወጥ ችያለሁ ያለው ገበሬ የት አግኝቷቸው ተነጋገሩ? ለመሆኑ ገበሬውም ለስብሰባ መጥቶ ነበር? ወይንስ ኦባማም ቁጩ ለመዱ(ተማሩ) ? ወይንስ ገበሬው ደንግጦ እዚሁ ቀረ ? ገበሬው ከአቤ ቶክቻው ኮርጆ ብሎግ አለው?
  ማሽላ ሲያር ይስቃል አሉ….. በቸር ይግጠመን!

 7. […] exiled satirist Abe Tokichaw wrote: እንግዲህ ኢህአዴግ አሁን በደንብ ጎረመሰ ማለት ነው። ይህ […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s