ይቺ ጨዋታ ዛሬ ቀን ላይ ለኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ የነበረው ብሎጋችን ላይ ለጥፈናት ነበር። በዋናው ቤትስ ለምን ይቅርባት ተብላ እነሆ እዚህም መጣች!
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ሁልግዜም እከታተለዋለሁ። ወደኔ የሚመጣውን ካላቋረጡት በቀር… ወደፊትም በትጋት ማየቴን እቀጥላለሁ። ታድያ ሁልግዜም እንዳስደነቀኝ ሁልግዜም እንዳስገረመኝ ነው። እንደውም አሁን አሁን “ከሪሞት” ላይ ወደ ኢቲቪ የሚወስደውን ቁጥር ስጫን በለሆሳስ “ታምረ ኢቲቪን ልከታተል” እያልኩ ነው።
እኔ የምለው ዜና አንባቢዎቻችን በተለይ መሰለ እና ተመስገን አለቅጥ ሽቅርቅር ያሉበትን ምክንያት ሊነግረኝ የሚችል አለ? እንዴ ሞዴሎች እኮ ነው የመሰሉት። አንዳንዴማ የፍትሁ ወዳጃችን ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ግዜ “መለስ ሆይ ባልተመቸው ህዝብ ላይ የተመቸው መሪ መሆን አስከመቼ…?” ብሎ የፃፈውን እያስታወስኩ እናንት ዜና አነብናቢዎች ሆይ በጎስቋላው ህዝብ ላይ እንዲህ መሽቀርቀር እስከመቼ? ብዬ ልጠይቃቸው ይቃጣኛል።
ስለ ኢቲቪ በደንብ ቁጭ ብለን በሰፊው የምንነጋገርበት የሆነ ቀን ይመጣል። አሁን ግን በተለይ ለኢትዮጵያ ወዳጆቼ ብሎጓም ሳትዘጋ ገብስ ገብሱን እንጨዋወት ገብስ ገብሱን ተብሎ የተገለፀው የኢቲቪ ማስታወቂያዎች ናቸው፤
ገብስ ገብሱን 1
እኔ የምለው በኢቲቪ አንድ ማስታወቂያ አይታችሁልኛል? ማስታወቂያው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማስታወቂያ ነው። ልማታዊቷ ሙሉአለም ሆዬ ብቅ ብላ “የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊሸልማችሁ ነው በኤስ አም ኤስ የሆነ ነገር ብላችሁ ላኩልንና በሽልማት እናንበሻብሻችኋለን” ትለናለች። ለምንድነው የምትሸልሙን? ብለን ብንጠይቅ መልስ የለውም። ዝም ብሎ ያለምንም ምክንያት ምን በወጣቸው ነው የሚሸልሙን? ወይስ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን እድላችንንም እንዲያሯሩጥ መብት አለው? ፌዴሬሽኑ ነጋዴ ቢሆን “ለማስታወቂያ ግብአት ነው” አንላለን። ወይም ደግሞ እንደሰዉ በጨዋ ደንብ “ተቸግሬ ነው የማስቸግራችሁ ለገቢ ማሰባሰቢያ ተባበሩን እግረ መንገዳችሁንም ዕድላችሁን ሞክሩ” ማለትም የአባት ነው። አለበለዛ እኮ ነገ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሮ ተነስቶ “በኤስ ኤም ኤስ ሽልማት በሽልማት ልናደርግዎ ቆርጠን ተነስተናል!” ሊለን ነው። (ውይ እኔ ደግሞ ዘልዬ እርሳቸው ቢሮ ላይ ይቅርታ…) የምር ግን ካለ አንዳች ምክንያት “ልሸልማችሁ እጣ ቁረጡ” ብሎ ማለት ከቁማር ተለይቶ ይታያል? ቁማር ለማጫወት ደግሞ ለአስቆማሪ ድርጅት እንጂ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መብት ያለው አይመስለኝም ስራውም አይደለም። ኢቲቪም ይህንን ማስታወቂያ ከመስራቱ በፊት ፈተሽ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ። ለማንኛውም እርስዎ ሁለት ብርዎን ከመቅለጥዎ በፊት ለምን ብለው ፈተሽ ያድርጉ?
ገብስ ገብሱን 2
ይሄኛው ማስታወቂያ ደግሞ የኮንደም ማስታወቂያ ነው… ልጁ በአንድ የግንባታ ስራ ላይ የተሰማራ ነው። በስራ ላይ እያለ አንዲት ምስኪን ኮረዳ የሚሸጥ በቆሎ እሸት ቅቅል (መሰለኝ) በእቃ ታቅፋ ስታልፍ ያያታል። ከዛም ተንደርድሮ ወደ ልጅት ይሄዳል። በቴሌቪዥን ስናየው የበቆሎ ቅቅሉን ዋጋ እያስቀነሰ ነው የሚመስለን። ታድያ አንዲት ሴት በመኪና በአጠገባቸው ስታልፍ ምን ሲያደርግ እንዳየችው እንጃ መኪናዋን ቀጥ አድርጋ አቁማ እየተጣደፈች ኮንደሟን መዥረጥ አድርጋ ታሳየዋለች። ከዛም የስራ ባልደረባው ሽማግሌ ከኪሳቸው ኮንደማቸውን አውጥተው ያሳዩታል፤ እያለ እያለ በአካባቢው ያለ ሁሉም ሰው ኮንደሙን እያወጣ ለጎረምሳው ሲያሳየው እርሱም ከኋላ ኪሱ ብቅ ያደርገዋል። ምን ማለት ነው…? በቆሎ ቅቅል እና ወሲብን ምን አገናኘው? ኢቲቪ ምንድነው የሚመክረን….? “ጎረምሶች ሆይ ማንንም ሴት እንዳታልፉ የስጋ ፈቃዳችሁን አላፊ አግዳሚው ላይ መፈፀም ትቻላላችሁ ማለቱ ነው?” ወይስ ምንድነው? ግራ ያጋባኝ ማስታወቂያ ነው።
ገብስ ገብሱን 3
ይቺን እንኳ ከዚህ በፊትም ብያታለሁ። ግን ከጓደኞቿ ጋር ትደገም ብዬ ነው። “መግብ ልጅን መግቡ በእድሉ ያድጋል እንዳትሉ” የምትል ህፃናትን ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ እንዳለብን የምታስገነዝብ ማስታወቂያ ነች። እዝች ላይ ሁሌ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ። ልጆቻችንን የማንመግበው እና “በእድሉ ያድጋል” የምንለውኮ እጅ አጥሮን ነው እንጂ ቢኖረንማ… “ጎሽ ለ ጇ ስትል…” ብለን የተረትነው እኛም አልነበርን? የኛ ሰፈር መዋል ህፃናት ተማሪዎች ያሉትን በሀይሉ አልነገራችሁም እንዴ? “ልጆች ከኮልስትሮል ነፃ የሆነ ቅቤ ብሉ እሺ” ብላ መምህሯ ትመክራለች። ተማሪዎቹስ ምን አለ…? “ከየት አምጥተን ቲቸር!?”
ማን ነበር “ማበል ነው” ማ..በል “ማዕበል ነው” ያለው አርቲስት(ከያኒ)? ? ? የኢቲቪ ዜናና ጋዜጠኞችንን የታዘበ ወዳጄ የኤርትራ የአማርኛውን ዜናና ጋዜጠኞች አቀራረብ አወዳድሮ የተገነጠልነው እኛ ነን ወይስ እነሱ ? ? ሲል ጠየቀኝ መልስ የለኝም! ኮ/መንግስቱስ ምን ተነካን ብለው ነው እንገንጠል የሚሉት ጋራዡ፣ሆቴሉ፤ቡና ቤቱ፤ነዳጅ ማደያውን (ቦቴው) የነሱ ነው ብለው ነበር። የኢቲቪ ጋዜጠኞች ፲፩በመቶ እድገት በተከታታይ ያስመዘገበች ሀገር ከቀረጥ ነፃ የሆነ ሱፍ ለሹማምነቶች ሲታዘዝ አብሮ ቢመጣላቸው በመርቃትስ መልክ ቦነዳው ላይ ቢለጠፍ፤ወሬ ለማዳመቅ አበረው የተጓዙ በሽልማት መልክ የጉዞ አበል(ክሬዲት ካርድ) ተሰጥቶአቸውም ሊሆን ይችላል።አለበለዚያ የማዳመቅ ተነሳሽነት እንዲሁ በቀላሉ አይገኝም። በጣም የሚመስጠኝ የኢቲቪ ዓርማ ነው፤ ይዜምለት …. ማበል ነው … ማ…በል
“መብረቅ ነው” መድረቅ ነው” ፤
ኢቲቪ ዜናው ቁም ነገር ጣዕም የለው፤
እንዲሁ ጠዋት ማታ መዋሸት ነው፤
ሕዝብ አዘነ ለዓይንና ለጆሮው፤
ኸረ ማነው ጀግና የሚያድነው፤
ደርግ ሄደ ብለን እሰይ እልል ብለን፤
ወያኔ ቀስ ብሎ መሠለ ተመስገን፤
*****************************
ኢቲቪቪቪቪቪቪቪቪቪ ፡ ያላደረገን ምን አለ ፡፡ አኔ በነሱ ምክንያት ቴሌቪዥኔን ሽጬ በላው ፡፡