ከዚህ በፊት ሳይገባኝ “ሪፖርተር” የሚል ማዕረግ ሰጥታኝ የነበረ አንድ ጋዜጣ ነበረች። “ሆመር” ትባላለች። እንዴት በፍቅር ምንወዳት ጋዜጣ ነበረች መሰላችሁ። በአሁኑ ወቅት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ጋዜጣ ወግ ደርሷት “ነብስ ይማር” ለመባል በቅታለች። በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የፕሬስ ቀን እየተከበረ ነው አሉ ስላቅ በየፈርጁ ማለት ይሄኔ ነው! ግን እንኳን አደረሰን ማለት ይገባል።
በዛች ጋዜጣ ላይ የሚወጣ “ዶሮዋ መንገዱን አቋረጠች” የሚል አንድ አምድ ነበረን። በነገራችን ላይ በዚህ “ዶሮዋ መንገዱን አቋረጠች” ጨዋታ ከባለቤቷ ሆመር ጋዜጣ ይልቅ የነ ብርሃኔ ንጉሴ ኢንፎኢቴመንት ታዋቂ ሆናበታለች።
የሆነው ሆኖ በተለይ ዶሮዋ መንገዱን ስታቋርጥ የተለያዩ መሪዎቻችን የተናገሩትእውቅና ያገኘ ጨዋታ ነበር።
አሁን በቅርቡ በዋልድባ ገዳም የሚገነባው ስኳር ፋብሪካ ሂደቱን ክፉ እንዳያጋጥመው መንግስት ከመደባቸው ፌደራል ፖሊሶች ውስጥ አራቱን ጅብ በልቷቸው ነበር። ይህ አስደንጋጭ ዜና ነው። ልብ ላለው መንግስት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥም ነው። አፍሮ ሬድዬ በሚል የፌስቡክ አድራሻ አንድ ወዳጃችን ኢቲቪ ይህንን ዘገባ እንዴት ሊያቀርበው እንደሚችል አስነብቦናል። ታድያ እኔም ከሆመር ጋዜጣ ትዝታ እና ከአፍሮ ራድዮ ጨዋታ በመነሳት ለዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሁኔታ በተለያየ ግዜ እንዴት እንደሚያወጉን እንደሚከተለው እገምታለሁ… (ጨዋታ ነው እሺ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር)
ከድርቅ ጋር ተያይዞ
እ… የተከበሩት የህዝብ ተወካይ ልብ ያላሉት አንድ ነገር ያለ ይመስለኛል። በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ጅቦች የሚበላ ነገር አጣን በሚል የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለማጠልሸት፤ ፖሊሶችን መብላታቸው በአካባቢው የምግብ እጥረት ያለ ለማስመሰል እንጂ፤ ከዚህ የዘለለ አላማ አለው ብዬ አላምንም። ይህንን የተከበሩ የፓርላማ አባሉም ሳያውቁት አይቀርም ። አበዛኛዎቹን ጅቦች ሀገሩ ተርቧል ድርቅ ገብቷል ብሎ ለማጯጯህ ሲሉ የመድረክ አመራር አባላት በርቱ እና ምግብ ትታችሁ የፖሊስ አባላትን ተመገቡ እንደሚባሏቸው፣ እንዲሁም የውጪ ሀገር ጋዜጠኛ እቦታው ድረስ እየወሰዱ ይኸው ጅቡ የሚመገበው አጥቶ ፖሊስ እየበላ ነው እያሉ እንደሚያለቃቅሱ እናውቃለን!
ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን አስመልክቶ እያደግን ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ጥያቄው አሁን የቁጥር ጉዳይ ነው። ዕቅዳችንን ስናቅድ አንድ ጅብ ቢያንስ ሶስት ፖሊስ ከበላ ይበቃናል ብለን ነበር። አሁን ግን አ…ራ…ት ፖሊስ ተመግቧል። ይሄ ከዕቅዳችን አንፃር ስናየው ከበቂ በላይ ነው።
ስለዚህ ሁሉም፤ ተቃዋሚውም ጭምር የኢኮኖሚ እድገቱ አልዋጥ ቢላቸውም ለመቀበል እየተገደዱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ በየትኛውም ሀገር ታይቶ የማይታወቅ የእድገት ማሳያ ነው። ቻይና በአሁኑ ግዜ ለምዕራባዊያኑ ሁሉ ስጋት እስክትሆን ድረስ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ ይታወቃል። በቻይና አንድ ጅብ አንድ ፖሊስ እንኳ በልቶ አያውቅም። በህንድም ተመሳሳይ ነው። የእኛ ጅቦች ግን በአንድ ጀምበር አራት ፖሊሶችን መብላት እንደሚቻል አሳይተዋል። ከዚህ የበለጠ የእድገት ማስረጃ ከየት እንደምናመጣ አይገባኝም።
ከሙስና ጋር በተያያዘ
በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ትልቁ ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ነው። በዋልድባ ጫካ ብትሄዱ ጅቦቹ እንደ እንዝርት እየሾሩ… ይሄ እናቶቻችን የሚፈትሉበት እንዝርት ልክ እንደሱ…እየሾሩ በተለያየ ስልት እና ፊሊክሴብሊቲ በሆነ መልኩ አራት ፖሊሶችን በልተዋል። እሺ ፖሊሶቹ ይበሉ። ነገር ግን እነዚህ ጅቦች ለመንግስት ታክስ ከፍለዋል ወይ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መንግስት ካዝና የገባ አንድም ፖሊስ የለም። ይሄ ነው አሁን የቸገረን ነገር። ይሄ ከመሰረቱ ልናጠፋው የሚገባ የሙስና ችግር ነው። አሁን ያለን ምርጫ አንድ እና አንድ ነው። ወይ ጅቦቹ ፖሊሳቸውን እንደፈለጉ እየበሉ ይኖራሉ፤ ወይም ደግሞ አንድ ፖሊስ በበሉ ቁጥር ሌላ ፖሊስ መንግስት ካዝና የሚያስገቡበት ስርዓት ይዘረጋል። አራት ነጥብ!
ከአሸባሪነት ጋር በተያያዘ
በዋልድባ ገዳም አካባቢ ጅቦች የፈፀሙት ተግባር ሰሞኑን ተከታትለናል። ይሄ የአሸባሪነት ህጋችን በግልፅ አስቀምጦታል። እልም ያለ የሽብር ተግባር ስለመሆኑ ምንም አያከራክርም። ጥያቄው ከእነዚህ ጅቦች ጀርባ ማን አለ? የሚለው ጥያቄ ነው። ይህንን በተመለከት የቀለም አብዮት ማካሄድ የሚፈልጉ ሀይሎች፣ አክራሪ የሀይማኖት ሰዎች፣ ግንቦት ሰባቱ፣ ኦነጉ፣ ኦብነጉ፣ ሻቢያው እና የውስጥ አርበኛው ሁሉ ድጋፍ እና አይዞህ ባይነት እንዳለበት እናውቃለን።
በየሰዓቱ ለጅቦቹ ከተለያየ አገራት ስልክ እየተደወለ፤ “አስከ አሁን አራት ፖሊስ ብቻ ነው እንዴ የበላችሁት በርቱ እነጂ በቀደመው ግዜ የነበሩ ጅቦች እኮ ይሄን ስንት ፖሊስ በልተው ነበር…” እያሉ እንደሚወተውቷቸው እናውቃለን። በዚህ አጋጣሚ ለመድረክ አመራር አካላት ማሳወቅ የምፈልገው ነገር ከጅቦቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖራችሁም ውስጥ ውስጡን እንደምትገናኙ እናውቃለን። በሽብርተኝነት አዋጁ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ከጅቦቹ ጋር ወዳጅነት የመሰረተ ከአንድ ቀን በላይ ሻይ ቡና ያለ ሁሉ እንደሽብርተኛ እንደሚቆጠር ትረዱታላችሁ የሚል ግምት አለን። እንደውም በዚሁ ፓርላማ ውስጥ ከአጠገባችን ቁጭ ብለው ከጅቦቹ ጋር ግንኙነት ያለው እንዳለም እናውቃለን። ነገር ግን ማስረጃ የለንም!
የጨዋታው አሳብ አመንጪ አፍሮ ሬድዮን እና እናት ሆመር ጋዜጣን አመሰግናለሁ!
ይህ በጣም ጥሩ የሆነ መልክት ነው ፤ጨዋታ አስመስሎ የፈለጉትን መንገር ማለት ይሄ ነው አቤ በርታ ፤እኔ በግሌ ወድጄዋለሁ ለነገሩ እዚህ ብሎግ ላይ የሚወጣው ያንተ ብቻ ነው ወይስ ሌላ ሰውም ሊስተናገድበት ይችላል?
Even if ur blog is blocked, we read it,
“no retreat no surrender ” Aba
“ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የፕሬስ ቀን እየተከበረ ነው አሉ ስላቅ በየፈርጁ ማለት ይሄኔ ነው! ግን እንኳን አደረሰን ማለት ይገባል።” አልግባንም!! “press OR oppress”
*ከድርቅ ጋር ተያይዞ …ድጋፍ ከተወካዮች ምክር ቤት አባል “አመሰጊናሎ የተኮቦሩ አፈ ጉባዩ የተከቦሩ ጦቅላይ ሚ/ር እወዶታለሁ፤ እነኚ ጆቦች የኢቲዮጲያ ናቾ ? ወይስ የቀጠና አተራማሽ ኢርቲራ መሊክተኛ ናቾ ? ማቡራሪያ አመሳጊናሎ! *ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ… “ይህን የእድገት ተሞክሮ በተለያዩ ሀገራት ባሉን ዲፕሎማቶች አማካኝነት በቪዲዮ ተቀርጾ ለማሳየት በተለይ ለጽነፍኛው የጭፍን ተቃዋሚ ለሆነው ዲያስፖራ ለማሳየት “የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ ካድሬዎች ከኢቲቪ ጋር በመተባበር አንድ “የጅብ ገድል በዋልድባ” የተሰኘ ፕሮገራም እነዲሰራ የአምስት ዓመቱ ትራንሰፎረሜሽን እና የሕዳሴው ጉዞ እንኳንም ህዘቡ ጅቦችም ከልማታችን ተጠቃሚ እንደሆኑ IMF, WEB, AU. ይወቁት! *ከሙስና ጋር በተያያዘ…ለመሆኑ ጅቦቹ ፖሊሶቹን ከመበላታቸው በፊት በመን ሥራ ይኖሩ ነበር ?ገቢያቸውስ? አካባቢው ለኮንትሮባንድ ያለው ቅርበት? ማስረጃው የአካባቢውን ፀጥታ ተገን አድርገው ለዘመናት መኖራቸው ሳይታወቅ ቆይተዋል አሁን ሀገሪቱ በያዘችው የእድገት ግስጋሴ መንግዱ ስለጠፋባት ዋሻቸው ድረስ የሄዱት አራት ፖሊሶች የመንቀሳቀስ መብት ቢኖራቸውም ሰውና ጅብ መለየት ካልቻሉ ችገሩ ከውስጥ ያለው የሙስና ትስስር አይናቸውን ጋርዶት ስለሆነ መንግስት በአንድ እጁ የሚያደርገውን (ቱ ቱ) ይቅርታ ቀለም አጥሮ ነው! በሁለት እጁ ይሞክረዋል። *ከአሸባሪነት ጋር በተያያዘ…የአሸባሪዎች አዋጅ ከታላላቅ ሀገራት ነጠላ ሰረዝ እና አራት ነጥብ ሳይቀር እንደአለ የተገለበጠ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል ሆኖም በሐረር መስተዳድር ለቱሪስት መስዕብ ተብሎ ሥጋ በእንጨት ላይ እየሰኩ ለጅብ የሚያበሉትን አይመለከትም ይህም ኢትዮጵያ እንኳን ሰው ሕዝብ እና አራዊቱ አብሮ በሰላም ኖሯል የሚሉ የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ የሚመጣ የሚመስላቸው አነድ ነን አንበታተንም እያሉ ህዝብ እንዲመርጣቸው ለፖለቲካ ፍጆታ የበሬ ሥጋ ለጅብ ፍጆታ የሚያውሉ ሥራ ፈቱን እና የውጭ ምንዛሪ የማያመጣውን ፖሊስ ማስበላቱ የተሻለ የእድገት አማራጭ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል።(አራት ነጥብ) ስለዚህ ሕዘቡ ከመንግሰት ጋር እጅ እና እግር ሆኖ ለመበላት ይመጥናሉ የሚላቸውን የክልልም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን እንደተለመደው በመጠቆም እነዲተባበረን እንጠይቃልን! ማነህ ባለ ተራ ? ? ? በለው!
ABE THARIM Gerbkute