እኔ የምለው ወዳጄ ሳሱር ነብሴ ድጋሚ መጣች አይደል እንዴ!? እሰይ! እልል በሉ እንጂ። ድግስ አትደግሱም እንዴ!? ጠላው ይጠመቅ፣ ድፎው ይደፋ፣ ቡናውም ይፈላ፣ ፈንዲሻው ይፈንደሽ፣ እጣን ሰንደሉ ተጫጭሶ ቄጤማውም ይጎዝጎዝ። በዓሉ የትንሳኤ በዓል ነውና ሁሉም ሰው ይደሰት።

አዎ አሁን ወቅቱ የትንሳኤ ነው። ሞቱ ተቀበሩ ያልናቸው ችግሮቻችን በሙሉ በስንተኛው ቀን እየተነሱ ዳግም ህያው እየሆኑ ነው። ይህ እንዲሆን ያደረገው እርሱ ኢህአዴግ ተዓምረኛ ነው። ያደረገውም ተዘርዘሮ አያልቅም።

መቼም ትዝ ይልዎታል… የዛሬ ሃያ አመት ኢህአዴግ አዲሳባን ሲቆጣጥር መጀመሪያ ይፋ ያደረገው ነገር፤ እናንት ነፃ ህዝቦች ሆይ ከእንግዲህ ያለ አንዳች ገደብ እንዳሻችሁ መናገር፣ እንደፈቀዳቸሁ መፃፍ፣ ደስ እንዳላችሁ መሞዘቅ ትችላላችሁ። ብሎ ነበር።

እኛም የዛኔ በልጅነት ጀብደኝነት ተነሳስተን “እውነት ዴሞክራሲ አለ?” የሚለውን ለመፈተን ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ እና ስንመጣ በየመንገዱ፤ እንዲሁም በትምህርት ቤታችን ቅጥር ግቢ ድምፃችንን ዘለግ እያደረግን፤

“በመለስ መላጣ ቅማል ትሄጂና

እንዳትሰበሪ ያዳልጥሽና፣

መለስን ለመሳል በጣም ቀላል ነው

ፍየሊቷን ስሎ ቀንዷን መተው ነው”

እያልን የግጥም ችሎታችንንም የዴሞክራሲ መብታችንንም እንፈትን ነበር። አዎ እውነትም ማንም የሚናገረን ሰው አልነበረም። እውነትም ዴሞክራሲ ተከብሯል ስንል የግንቦት ሃየ ሰልፎች ላይ “…ግንቦት ሃያ ለዘላለም ኑሪ” የሚለውን መዝሙር እየዘመርን በደስታ እንሰለፍ ነበር። እያደግንም ስንመጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መለስ መላጣ ብሎ መሳደብ ይቻላላ  መላጣዬን መንካት ግን አይቻልም” ብለው ጭራሽ አስደሰቱን። (በቅንፍ በዚህ ንግግር የደነገጠ አንድ ግለሰብ ቢኖር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፀጉር አስተካካይ ብቻ ነበር አሉ። መላጣቸውን ሳይነካ እንደምን ቀሪ ፀጉራቸውን መከርከም ይችለዋል…? ብለን እንቀልዳለን! ቅንፍ ለዘላለም ትኑር!)

ቀልዱ ቀልድ ነው የምር ግን በግንቦት ሃያ ማግስት ሀገሪቷን ያጥለቀለቋትን የህትመት ውጤቶች ስናስታውስ ለካስ ህዝቤ ታፍኖ ኖሯል፤ ያስብላል። እዝችጋ ተወዳጁን እስክንድር ነጋን ሳይጠቅሱ ማለፍ ነውር ነው። አዲስ መስመርም ይገባዋል፤

አስክንድር ነጋ ሲኖርበት ከነበረው ፈረንጅ አገር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሳንሱር መቅረት እና የነፃው ፕሬስ መፈቀድን ተከትሎ ነበር። እንደመጣም “ኢትዮጵስ” የተባለች በሃምሳ ሳንቲም የምትሸጥ ጋዜጣ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን ለተሰጠው የፕሬስ መብት ዱላ እና እስር ያስከፍል ጀመር። በዚህም አስክንድር ብቻ ሰባት ግዜ ታስሮ ብዙ ሰባት ግዜ ተደብድቧል። ይህንን ስናይ አዋጁ ወጥመድ ነበር እንዴ…? ብለን ጠርጥረናል።

“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ መሄድ ትጀምራለች” (ይቺ አባባል የት ጠፍታ ከርማ ነበር ባካችሁ?)  ብቻ ቀስ በቀስ የፕሬስ ህግ ሲወጣ ቀስ በቀስ የአሸባሬነት ህግ ሲወጣ ህገ መንግስታችን የፈቀደልን ያለ “ሳንሱር” ቅድመ ምርመራ የመፃፍ መብት ራስን በራስ ወደመመርመር ተሸጋገረ። እኛ “ፀሀፊ” በሆንበት ዘመን ራሳችንን ሳንሱር እያደረግን መፃፍ ጀመርን። ከዛም አልፎ በግልፁ መፃፍ የሚያመጣውን ጦስ እየፈራን ያለ አመላችን አሽሟጣጭ ሆነን ቁጭ አለን (እዝች ጋ ሳይስቁብኝ አይቀሩም… ግን የምሬን ነው!) አሁንም እያደር ሽሙጡም ቢሆን እሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የማያስቀይም እንዲሆን መከራችንን ማየት ጀመርን። (ቤተሰባቸው ተብሎ የተገለፀው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ነው) እሱም አልተሳካም!

ወዳጄ ለማንኛውም አሁን በይፋ ሳንሱር ተጀምሯል። ከዚህ ቀጥሎ ማተሚያ ቤቶች የሚያሳትሙትን ማነኛውም የህትመት ውጤት ላይ ምርመራ እንዲያከናውኑ ተወስኗል። አንጋፋው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራውን መጀመሩን ሰምተናል። ሌሎቹም ይቀጥላሉ… ባለፈው ሳምንት ውስጥ ማህሌት የተባለች የልብ ወዳጃችን ፌስ ቡክ ግድግዳዋ ላይ ይህንን ለጥፋ ነበር።

“የብርሃና ሰላም አዲስ ህትመት ስራ ውል አንቀጽ አንቀጽ 10 የሚከተለውን ይላል፡፡ ምን ማለት ይሆን?!

አንቀፅ 10
ሕግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም
10.1 አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የፅሁፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ በቂ  ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው፡፡

10.2 አታሚው አሳታሚው የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል፡፡”

ወዳጃችን ማህሌት፤ ምን ማለት ነው? ነው ያልሽው…? ምን ማለት መሰለሽ ፅሁፍሽ ከመታተሙ በፊት በብርሃን እና ሰላም የምርመራ ዋና ስራ ስራ ሂደት ባለቤት ይመረመራል። ሳንሱር ይደረጋል ማለት ነው።

እነሆ መንግስታችን ተዓምረኛ ነው! በህገ መንግስቱ ሞተ ያልነውን ሳንሱር አስነስቷል እና ደስ ይበላችሁ!!!

ይህንን በሂሳብ እናስላው ካልን ህገ መንግስቱ ሲባዛ በዜሮ ይሆናል ዜሮ! ይሆናል ማለት ነው። ታድያ ማሽኑ የመንግስት ነው!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

3 responses »

  1. Alenagerem says:

    I’m sure you have read “Animal Farm”, if not try to read it. As much as it seems funny, most of the things that are happening in Ethiopia are the exact (in a way; kenef lezelalem tenur bayalehu enem) replica of them.

    Here is my favorite line from it “All animal are equal but some are more equal than others” meaning that “All human beings are equal but some are more equal than others”

  2. Tulu forza (Austria) says:

    Plus ça change (plus c’est la même chose) ይላል የቅንፍ አባት ፈረንሳይ ነፍሴ ሲተርት። “የለውጥ ትርጉሙ፤ባሉበት መቆሙ” እንደማለት።
    “ ዲሞክራሲ በገደብ” ብሎ ነበር ደርግ፤ የብዕር ፍልሚያው ሲከብደው (ወይም የጥይት ፍልሚያው የሚቀል እንደሆን የገባው ዕለት)። እናም አሸነፈ፤ ኋላም ተቸነፈ (አቤት የ ሸ እና የቸ ታሪክ!)።
    መለስ ዳግማዊ መንግስቱ አይደለም የሚል እጁን ያውጣ፤ እኔም ሂሴን እውጣለሁ (እገመገማለሁ፤ በገገማ ቋንቋ)።

    አኮቴት ለብዕርህ ትባት፤ አቤ።

  3. በለው! says:

    “የብርሃና ሰላም አዲስ ህትመት ስራ ውል አንቀጽ 10 የሚከተለውን ይላል፡፡ ምን ማለት ይሆን?!
    “የፅሑፍ እስክሪብት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ በቂ ምክንያት አለኝ በማለት የተቀናቃኝ ሐሳቦች ሲቀረቡልህ መልሳቸው! ሁልጊዜ መንግስት ብቻ ተደጋጋሚ ሕግ ሲያወጣ ጥሩ አደለም እና።” የጠ/ሚሩ ቀጭን ትዕዛዝ ነው! 10.1 ሌላው” 10.2 አታሚው አሳታሚው የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው… “ለሕገ መንግስቱና ለሕገ መንገስታዊ ሥርዐቱ አደገኛ፣ቀስቃሽ፤አንቀሳቃሽ፤አሸባሪ፤ መስሎ ስለታየኝ ፣መብላት ተሳነኝ፤እንቅልፍ ከለከለኝ፤ለማተም እጄ ተንቀጠቀጠ፣ ማሽኑ ቀለም አልተፋም፤ወረቀት አጠረ በማለት እራሰህን እነደተከላከልክ አስመስለህ አውራው ፓርቲ ብቻ ሕዘቡን በፈጠራ ወሬ በሬዲዮ፣በቲቪ፤በጋዜጣ እና በመጽሔት በአንድ አርዕስት በተለያዩ አፈ ቀላጤዎች እንዲወናበድ ማድረግ፤የዕለት ገቢውንም ለፓርቲው በተዘዋዋሪ እንዲርዳ የውሸት ወሬ ኢንዲገዛበት ማድርግ ነው። ይህ ያነበባችሁት አንቀጽ የብርሃንና ሰላም አደልም…የጭለማ እና የብጥብጥ ነው። ተበጣበጡ አልልም ግን “እንቢኝ በሉ” እላለሁ።ከሀገረ ከናዳ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s