በአንድ ቤተሰብ ውጥ የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። የቤተሰቡ ሃላፊ የሆኑት አባወራ ሲያገኙ በድፍረት ሲያጡም በሌላ ድፍረት ጠጥተው ሞቅ ብሏቸው ነው የሚገቡት። ስጠረጥር የዘንድሮ ኑሮ እንደምንም ብለው ሞቅታ ውስጥ ካልተደበቁ በስተቀር እንደማይቻል ገብቷቸዋል።

አሁንም ስጠረጥር አባወራው በዱቤም ይሁን፣ በብድርም ይሁን፣ በቅልውጥ መጠጥ ቤት ካላመሹ በቀር በጊዜ ቤታቸው ቢገቡ የቤተሰቡ አባላት የሚጠይቋቸውን ጥያቄ መመለስ እንደማይችሉ  ስለሚረዱትም ይመስለኛል።

ታድያልዎ ከእለተታ አንድ ቀን አንዱ ልጃቸው “ዛሬስ አባዬ ሲመጣ ጠብቄ የማናግረው አለኝ” ብሎ ሲጠብቅ፣ ሲጠብቅ፣ ሲጠብቅ ተስፋ ሊቆርጥ ትንሽ ሲቀረው መጡ…ማ…? አባወራው! ልጅም ገና እንደመጡ የተበጫጨቀ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሙን እያሳያቸው “አባዬ… ይኸውልህ ትምህርት ቤት የምለብሰው ዩኒፎርም ይሄ ነው… ጓደኞቼ እብዱ እብዱ… እያሉ ያበሽቁኛል። ደሞ ደብተሬም አልቋል። ሌላ ደግሞ …” እያለ ጥያቄ ቢያከታትልባቸው ግዜ በሞቅታ እና በመልስ እጦት ውስጥ ያሉት አባት ምን አሉት መሰልዎ… “አንተ ልጅ ዘወር በል ፖለቲካ አታውራብኝ!”

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ቀልዱ አላስቆትም!? እንግዲያስ ከቀልብዎ አይደሉም ማለት ነውና ደግመው ያንብቡት። ዘንድሮ እንደሁ ባለስልጣኑ ቀልብ ነዋሪው ደግሞ ቀለብ በፅኑ የተቸገረበት ሁኔታ ነው ያለው (አሁን እኔው ሳቄ መጣ!)

ይህንን ቀልድ ለምን አወራሁልዎ እንደው እስቲ ዘና ላድርጋቸው ብዬ ነውን? በፍፁም አይደለም አንበሳዬ… እህስ ይበሉና ይከተሉኝ ይምጡ አዲስ መስመር ላይ፤

አቶ መለስ የምሬን ነው የምልዎ ግራ መጋባት ይታይብዎታል። ትንሽ ይረጋጉ እንጂ… (አክብሬዎት እንጂ ሞቅታ ውስጥ ነው ያሉት!) ብዬ ልናገር ነበር። ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትሬ ነዎትና እንዲህ እንደዞህ አልልዎትም። ነገረ ስራዎ ግን ከላይ ካነሳውልዎ ሞቅ ያለው አባት ጋር ይመሳሰላል።

ከየትኛው ልጀምርልዎ…

የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ገዳማችን አይታረስ የአባቶቻችን አፅም አይፈንቀል… ብለው አቤት ቢሉ “ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው መነኩሴዎች አሏቸው” ይቅር ይበልዎ…! (አንድ ይበሉልኝ)

መምህራን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያቀረበብን ዘገባ ትክክል አይደለም “ህይወታቸውን የሚቀይር ገንዘብ ተጨመረላቸው ብሎ ዘግቦ ህይወታችንን አዘበራረቀው በይፋ የተናገረው ስህተት መሆኑን ይናገርልን” ብለው አቤት ቢሉ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው መምህራን!” አሉዋቸው። (ሁለት)

ከደቡብ ክልል አማራዎች መፈናቀላቸው አግባብ አይደለም በሚል እኔ ሳልቀር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ያደረጉት ነገር ለመንግስትዎም ጥሩ ስም አያሰጠውምና አንድ ይበሉዋቸው ብለን ብንጠይቅዎ፤ “በኢትዮጵያዊነት እንታወቅ የሚሉ ልዩ የፖለቲካ ጥቅም ፈላጊዎች…” ሲሉ ሃሳቡን አጣጣሉት (እየቆጠሩ ነው…? ሶስት ይበሉልኝ)

“እስልምና ሃይማኖታችን ላይ ጣልቃ አይግቡ አህባሽን ከወደዱት ራስዎ ሊያምኑ ይችላሉ እኛ ላይ ግን አይጫኑብን እኛ ሙስሊሞች አላህን እንዴት እንድምናምን መንግስት ሊያስተምረን አይገባም መንግስት ሌላ ሀይማኖት ሌላ!” የሚል ተቃውሞ ሲነሳብዎ “ይሄ አክራሪነት ነው የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ እንደ ቱኒዚያ፣ እንደ ግብፅ፣ እንደ ሊቢያ፣ እንደ የመን እና እንደ ሴሪያ መሆን የፈለጉ ሰዎች የሚያነሱት አጀንዳ ነው…!” ብለው በራሰዎ ላይ አሟርተው  እርፍ አሉ።

እንደው የቅርብ የቅርቡን ልንገርዎት ብዬ እንጂ ሌላም ብጨምር ማለቂያ የለውም… የተጠየቁት ጥያቄ በሙሉ ፖለቲካ እየመሰልዎ ግራ ገብትዎ ግራ አጋብተውናል።

ነገረ ስራዎን እስቲ ልብ ብለው ይመልከቱት ሁኔታዎ “አባዬ ዳቦ ራበኝ” ለሚል ልጅ “ዘወር በል ድብቅ ፖለቲካ አታራምድብኝ” ብሎ የሚመልስ ሞቅታ ከተጠናወተው አባት ጋር ይመሳሰላል።

ክቡርነትዎ ሞቅ ካልዎ ቀዝቀዝ ያለ ሽሮ ፍትፍት ይውሰዱበት እና ጥያቄዎቹን በሙሉ ድጋሚ ይስሟቸው። እውነት እውነት እልዎታለሁ እስከ አሁን የሰማናቸው ጥያቄዎች በሙሉ አንድም ፖለቲካ የላቸውም።  ይልቅስ እንዲህ ሲያደፋፍኑ የፖለቲካ ጥያቄው እንዳይመጣብዎ ይፍሩ! “ለምን እፈራለሁ ሙሉ ትጥቅ እያለኝ!” ካሉ አሁንም ሞቅታ ውስጥ ነዎት ማለት ነውና ሲነጋ እንነጋገራለን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

7 responses »

  1. Yigermal.. says:

    ክቡርነትዎ ሞቅ ካልዎ ቀዝቀዝ ያለ ሽሮ ፍትፍት ይውሰዱበት እና ጥያቄዎቹን በሙሉ ድጋሚ ይስሟቸው።
    “ለምን እፈራለሁ ሙሉ ትጥቅ እያለኝ!” ካሉ አሁንም ሞቅታ ውስጥ ነዎት ማለት ነውና ሲነጋ እንነጋገራለን!
    KKKKkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk, Abe You killed me in laugh!!!

  2. muslimu says:

    kkkkkkk tkkl neh wendimea ye dedebit kolo beltew esti yasbu

  3. Ethiopia says:

    abe beka sira fet honeh kereh? ere gobez mindinew endi fes neger hone yekerehew! sahame on you tultula weregna!

    • HGOS says:

      ለማነው ስሞ…. አንተ ጮምላቃ! አቤ ለስራ ፈታ የምትሎ… ወያኔን ምን ልትል ኖው…? ይሄስ እሺ ለግለሰብ ነው ስራ ቢፈታስ ሚስቱ ቢፈታስ ምን ጮነቆን እኛ! አለ አይደል እንዴ ለመለስ ዜናዊ ዋናው ሱረ ፎት! ኪኪኪኪ

    • Salewed Zeme says:

      tultula nefi ante nehe…….. what he has written all are facts….. show us which is wrong and makes him tultula nefi

  4. Habesha says:

    Love it Abe, for some reason the have no ears for 80 million ppl. Betam yasazenal.

  5. በለው! says:

    “ዘንድሮ እንደሁ ባለስልጣኑ ቀልብ ነዋሪው ደግሞ ቀለብ በፅኑ የተቸገረበት ሁኔታ ነው ያለው (አሁን እኔው ሳቄ መጣ!) አቤ…ት እኔ ሳቄ አመለጠኝ! እሳቸውም በፓርላማቸው ውስጥ ኮመከዋል “ማንም ሰው በኑሮው ደስተኛ አደለም” አዎን አንዴ ዕድገቷ ፲፩ ከመቶ ወደላይ የተስፈነጠረ ሀገር የወጭ ምንዛሪዋ ፲፯ በመቶ ወደ ታች የተፈጠፈጠ ፵፭ ከመቶ የሥራ አጥ ቁጥር ወደ ጎነ አጋደሎ ፲፫ ሚሊዮን ዜጋ በወጭ ደጎማ ቀምሶ እያደረ አደግን ተመነደግን ለሚሉት “አቶ መለስ የምሬን ነው የምልዎ ግራ መጋባት ይታይብዎታል። ትንሽ ይረጋጉ እንጂ… (አክብሬዎት እንጂ ሞቅታ ውስጥ ነው ያሉት! ” እኔም በበኩሌ ቡዳ እንዳይበላችሁ “አክ እንትፍ” ብዬአለሁ !!ለመሆኑ ምን ያህል በቀን ቢቅሙ ይሆን በዋልድባ ገዳም መሬት ላይ ባልተመረተ ሱኳር አልመረቅንም ብለው ቆርጠው የተነሱት? ጠ/ሚ ለመሆኑ የሀገሪቱ መምህራን የደሞዝ ማስተካከያ እና የደሞዝ ጭማሪ ሳያውቁ እንዴት? የት?በምን ተመረቁ?እንዴት ሥራ ተቀጠሩ?ለምን የደሞዝ ማስተካከያ እነዲደረግላቸው ተፈቀደ? እነዴትስ የሥራ ማቆም አድማው ዕለት መጥፎ መምህራን እነደነበሩ ማስረጃው ደርሰዎ አይ አባ ንፋው!ከደቡብ ክልል አማራዎች መፈናቀላቸው አግባብ አይደለም በሚል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ያደረጉት ነገር ለመንግስትዎም ጥሩ ስም አያሰጠውምና አንድ ይበሉዋቸው ተብለው ሲመከሩ ” ሕገ መንግስትዎ የማያጠቃልላቸው “ሞፈር ዘለል” ናቸው ብለዋል ለመሆኑ አርብቶ አደር፣አርሶ አደር፤የብሔር ብሄረሰብ እና ሕዘቦች ውጪ የሆኑ ናቸው ማለትዎ ነው?፡?፡?፡? ድሮስ የኩረጃ ነገር ትርፉ ይህ አደለም አራት ነጥብ። ነጠላ ዘረዝ ሳይቀር የተቃረመ ህገ መንግስትዎ በሽብርተኛ አዋጅ እና በጠመንጃ ባይደገፍ ኖሮ በቋንቋና በዘር ሕዘቡን ባያምታቱ ኖሮ ዕደሜዎ ያጥር ነበር ገና ድሮ መጠርጠር ነው ዘንድሮ ሥጋ ረከሰ መሰል የሕዘብ ምርጫው ሊሆን ነው ሊበላ ሽሮ!”ነገረ ስራዎን እስቲ ልብ ብለው ይመልከቱት ሁኔታዎ “አባዬ ዳቦ ራበኝ” ለሚል ልጅ “ዘወር በል ድብቅ ፖለቲካ አታራምድብኝ” ብሎ የሚመልስ ሞቅታ ከተጠናወተው አባት ጋር ይመሳሰላል።” ብሎዎታል አቤ ቶክቻው ሚስጥር ነው እንዳይነገሩብኝ አደራ ለራሰዎ አንብበው ይረዱት መቼም ልብ የለዎት አደራ!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s