ይሄ ወግ ትላንት አርብ አዲሳባ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው። ታድያ ለዲያስፖራ አንባቢዎቼ አዲሳባ በተዘጋችው በዝችኛዋ ብሎግ አቅርቤያለሁ። ኢትዮጵያ አላችሁ ወዳጆቼ ፍትህ ላይ ታነቡታላችሁ በሚል እሳቤ ነው  በዛችኛዋ መስኮት ያለጠፍኩላችሁ።

ወዳጄ እንዴት አሉልኝ ? እኔ ከእርሰዎ ሃሳብ እና ከፒያሳ ናፍቆት በሰተቀረ በጣም ደህና ነኝ። በዝች በምንወዳት እና በምትወደን፤ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ባለፈው ሳምንት እከሰታለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ግና እንዲሁ ስንደፋደፍ ሳይሳካልኝ ቀረ። ይህው እርሱ ባለው ቀን ተገናኘና!

እኔ የምልዎ ወዳጄ ሰሞኑን አባይ አንድኛ አመት ልደቱን ያከብራል ተብሎ ሽር ጉዱ ደርቶ የለ? እሰይ ይድራ እንጂ፤ ዋናው ነገር ሽር ጉድን ማድራት ነው። ሌላው ነገር ቀስ ብሎ ይመጣል። ካልመጣም ችግር የለም “እነሱ ተፍጨርጭረዋል!” የሚለው ስም ራሱ ግድቡ ከሚያመነጨው በላይ ሀይል ያመነጫል። እናም ሽር ጉድን የመሰለ ነገር የለም።

አንድ ወዳጄ ሰሞኑን በቴሌቪዥኑ “የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ እነሆ አመት ሊሞላው ነው!” ሲባል ሰምቶ ጠላትዎ ድንግጥ ይበልና “ክው” ብሎ ሲደነግጥ አየሁት። ምን አስደነገጠህ? ብዬ ብጠይቀው “አባይ ገና አንድ አመቱ ነው እንዴ?” በማለት አናቱን ይዞ ጠየቀኝ። ምነው ያለ እድሜው አረጀብህ…? አልኩት ጥያቄው ቢያስገርመኝ። እሱም በንግግሬ በስጨት እያለ፤ “አይ እዳዬ እኔን አስረጀኝ እንጂ እርሱማ ምን አለበት?” አለኝ።

ይህ ወዳጄ እንደሚለው አባይ ገና አንድ አመቱ ከሆነ (በመንግስት ስሌት እንኳ) ለቀጣይ ስድስት አመት መዋጮ ማዋጣት ይጠበቅብናል ማለት ነው። እኛ ደግሞ ከወዲሁ ተዳክመናል። እናም አባይ ገና ድክ ድክ ሲል እኛን ብርክርክ እያደረገን ነው። እናም መጨረሻችንን እንዲያሳምረው መፀለይ አለብን ብሎኛል።

ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን “አባይን የደፈረ መሪ!” ተብለው ከባንዲራችን እኩል ወደ ላይ ከተሰቀሉ… (ውይ የምን መሰቀል አመጣሁባቸው…? ከተውለበለቡ… ልበል ይሆን…? የባሰውን አመጣሁት… እኔ ልውልብለብልዎ። አግዙኝ እንጂ ጎበዝ፤ በቃላት እጦት አኮ ጠቅላይ ሚኒስትሬን አጎሳቆልኳቸው ባንዲራ ከፍ ካለ በኋላ ምንድነው የሚሆነው…? አዎ… ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከባንዲራው እኩል ከፍ ብለው ከደመቁልን…  አንድ አመት ሞልቷቸዋል። ብዬ ልገላገል)

በነገራችን ላይ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሰሞኑን ኬኒያ ውስጥ የላሙ ወደብ ግንባታ መጀመርን አስመልክቶ በተገኙበት ወቅት ባንዲራቸውን ዘቅዝቀው ይዘው የተነሱት ፎቶግራፍ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። አንድ ወዳጄ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንዲራችንን እንዴት ይገለብጣሉ…? ለዛውም ባለ ኮከቡን እኮ ነው። እኛ ብንሆን እንዲህ ያደረግነው “ባንዲራን የገለበጠ ይገለበጣል” የሚል አዋጅ ጠቅሰው ይገለብጡን ነበር። እሳቸው ባንዲራችንን ሲገለብጡ ማን ይገልብጣቸው…?” እያለ ያለቅጥ ሲያማርር ሰማሁት። ዝም ብለው ግዜም፤ እስከ ዛሬ የነበሩን መሪዎቻችን ለባንዲራቸው እንዴት ቀናኢ እንደነበሩ እያወሳ ወቀሳውን በጣም አበዛው።

በዚህ ግዜ እሳቸው ሲነኩብኝ የምታመመው እኔ፤ ተው እስቲ እሳቸው በስንት ስራ የተጠመዱ ሰው ናቸው። እና ልብ ላይይሉት ይችላሉ። አንዲት ባንዲራ ዘቀዘቁ ብሎ እንዲህ ማማረር ተገቢ አይደለም። ምንም ቢሆን አባይን የደፈሩ ባለውለታ ናቸው። ብዬ የወዳጅነቴን ላስረዳ ሞከርኩኝ። ይሄን ግዜ ወዳጄ የባሰውን ቱግ ብሎ “ይቅርታ አድርግልኝና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ባንዲራ ጨርቅ ነው አሉ ሲባል አላመንም ብዬ ነበር። አሁን ግን በአይኔ በብረቱ ባንዲራችንን ዘቅዝቀው ሳያቸው፤ ሰውየው አባይን ሳይሆን የደፈሩት ኢትዮጵያን ነው። ብያለሁ!” አለኝ። እኔም በሆዴ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ቢኖረው ነው ብዬ የመማረር ነፃነቱን ሰጠሁት።

እኔ የምለው ወዳጄ ሰሞኑን ታድያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአባይ ግድብ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ እንደሆነ ሰምተናል። አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ግን ገና ግድቡ ሲጀመር በየ ጓዳው፣ በየ አደባባዩ ሲጠየቁ የነበሩ ናቸው ታድያ እነዚህን ግርታዎች ለማጥራት የተከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አንድ አመት ሙሉ ተጨነቅው የሚሰጡን መልስ አላጓጓችሁም?

ለማንኛውም አባይ መገደብ ከጀመረ አንድ አመት ሞላው። በዚች አንድ አመት ግዜ ውስጥ ስንቱን አሳለፈው? እስቲ የተወሰኑትን እንቁጠር

አንድ ፤

አባይ ላይ ሊገደብ የታቀደው ግድብ (ውይ ይቅርታ የታቀደው አልኩ እንዴ…? የምን ዕቅድ አመጣሁኝ… ዕቅድ ምናምን ለሚል ዝባዝንኬ የምናባክነው ግዜ የለንም ለካ…) ዝም ብለን አባይ ላይ የሚሰራው ግድብ… ብለን እንቀጥል። ስያሜው መጀመሪያ “ታላቁ  የሚሊኒየም ግድብ ነበር” ከዛ በምን ምክንያት እንደሆን እንጃ ስሙ ተቀየረ።

ስለ ስም ቅያሬ እኔ የማውቀው አንድ ጨዋታ አለ። እንቃመሰው…

በሀገሬ በርካታ ገጠረማ አካባቢዎች የመዞር እድሉ ገጥሞኛል። ታድያ ከዙረት ብዛት አንዳንድ ሁነቶችን የት እንዳየዋቸው እዘነጋለሁ። ብቻ ከዞርኩባቸው አካባቢዎች በአንዱ፤ ገበሪዎች ስማቸውን ቶሎ ቶሎ ነበር የሚቀያይሩት። አምና እርገጣቸው የተባለ ሰው ዘንድሮ ታገሳቸው ሊባል ይችላል። የዚህ የስም መቃያየር ነገር ምስጢሩን በጠየቅሁበት ግዜ ምን ሆኖ ተገኘ መሰልዎ… “አዋቂ እያዘዘን ነው” አሉኝ። የምን አዋቂ…? አይባልም። የምድር አዋቂ ነው።

“ምርትህ እንዲሰምር ከብቶችህ ጤና እንዲያገኙ አትሻም?”

“አረ ጌታዬ ታድያ መባተሌ ለምን ሆነ…?”

“ስምህን ማን ነበር ያልከኝ…?”

“እልሁ… እሰኛልው ጌታዬ”

“እልሁ… እልሁ… ባዶ እልህ ምን ያደርጋል ማሸነፍ ያስፈልጋል… እልህ ብቻውን እህል አይሆንም… ትሰማኛለህ…?”

“አዎ ጌታዬ”

“እልሁ የሚለው ስም አይሆንህም። ጠላት ያበዛብሃል… ምርትህን ይቀንስብሃል… ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ አሸናፊ ብዬሀለሁ። አይዞህ ታሸንፋለህ…!”

ብለው ፈርደው የደንቡን ተቀብለው ይሸኙታል። እልሁም ዘንድሮ ስሙን አሸናፊ ብሎ ያማረ ምርት እንደሚገጥመው ተስፋ አድርጎ ይጠብቃል።

ትላንት አብዛኛውን ከገበሬው ማህበረሰብ የተውጣጡት ጀግና የኢህአዴግ ሰራዊት ታጋዮች፤ የዛሬ ባለስልጣኖች መጀመሪያ ሚሊኒየም ተብሎ ሲጠራ የነበረውን ግድብ “ህዳሴ ግድብ” ብለውታል። አዋቂ የሚለውን መስማት ጥሩ ነው። ብለን እኛም አልተጨቃጨቅንም እሺ ብለናል።

ሁለት፤

አባይ ግድብ ሲጀመር በአምስት አመት ግዜ ውስጥ ያልቃል ተብሎ ነበር። እያደር እያደር “በአምስት አመት ያልቃል የተባለው ለቀልድ ነው መቀለድ አይቻልም እንዴ?” ተባለና ወደ ስድስት አመት ተኩል ነው ወደ ሰባት አመት አደገ። ከዚህ ጋርም የተያያዘ ጨዋታ አናጣም፤

ነብሱን ይማረውና ይህንን ጨዋታ ስብሀት ገብረ እግዚአብሄር ነበር የሆነ ቦታ የከተባት። ይችትልዎ፤

በአንድ ወቅት አንድ ሰውዬ ይኖር ነበር። ብቻውን ሳይሆን ከሚስቱ ጋር ነበር የሚኖሩት። እነዲሁ ቁጭ ብለው ሳይሆን ደግሞ አንሶላ እየተጋፈፉም ነበር። ሲኖሩ፣ ሲኖሩ፣ ሲጋፈፉ፣ ሲጋፈፉ በአንዱ ቀን ሚስት ፀነሰች። ባልም “አባት ደስ ይለዋል ልጅ ሲወለድለት” የሚለውን ሙዚቀ እያንጎራጎረ፤ ለልጁ አልጋ ሊያሰራ አንድ እውቅ አናጢ ቤት ሄደ። “ሚስቴ አርግዛልኝ ደስ ብሎኛል እስክትወልድ ድረስ ቀስ ብለህ በጥሩ ሁኔታ አንድ የህፃን አልጋ ታዘጋጅልኛለህ?” ብሎ ቢጠይቀው፤ አናጢውም “ሁሉ ሰው እንዳተ ብልብ ቢሆን ምንኛ መልካም ነበር? እንዲህ ቀደም ብለው ማዘዛቸውን ትተው ደረሰ አልደረሰ ብለው ይጨቃጨቃሉ!” ብሎ ቀድሞ ማዘዙን አመሰገነ።

ከወራት በዋላ ልጁ ሲወለድ አባት ሚስቱን “ሰርፕራይዝ” ሊያደርጋት አናጢው ዘንድ ሄደ። አልጋው አልደረሰም። “ትንሽ ቀናት ብትጨምርልኝ ይደርሳል” አለው። አባወራው እያጉተመተመ ተመለሰ። ከተጨማሪው ትንሽ ቀናት በኋላም ድጋሚ ሄዶ ጠየቀ አሁንም አናጢ ጢሙን እያሻሸ “ይቅርታ ጌታዬ ትንሽ ቀን ብንጨምርበት ጥሩ አልጋ አደርስልሃለሁ” አለው።

እያለ እያለ አልጋው ሳይደርስ የተወለደው ልጅ አደገ። ምን ማደግ ብቻ እርሱም አግብቶ አስረገዘ። ሚስቱ ማረገዟን ላባቱ ቢነግረው ግዜ አባቱም “ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ…!” ብለው አስረጋዥነቱን ካደነቁት በኋላ፤ “አንተ ልትወለድ ስትል አንድ አናጢ ዘንድ አልጋ አዝዤ ነበር ሂድና አመጣው ለልጅህ ይሆንሃል ሌላ አልጋ እንዳትገዛ” አሉት። ልጅም “ጎሽ ከወጪ ተገላገልኩ” እያለ በደስታ ሄደ።

አናጢውም የልጁን የወራሽነት መብት በተለያየ ማውጣጫ ካረጋገጡ በኋላ፤ ችግር የለም በጥሩ ሁኔታ ይደርስልሃል ብቻ ትንሽ ግዜ ስጠኝ አሉት ጢማቸውን እያሹ። ልጅም አንድም በአናጢው ሁኔታ፤ አንድም ይሄ ካልደረሰ የሚጠብቀውን ወጪ በማሰብ ብስጭቱ መጣ እና፤ “አባቴ እኔ ስወለድ ያዘዘው አልጋ እንዴት ለልጄ እንኳ አይደርስም? የምን ተጨማሪ ግዜ ነው የሚጠይቁኝ…?” ብሎ በቁጣ ተናገራቸው። አናጢ ሆዬ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ነውና፤ “አይ እንግዲህ… እኔ በስራዬ ላይ ሲያጣድፉኝ አልወድም” አሉት። ብሎ ስብሐት ነግሮናል። የጋሽ ስብሐትን ነብስ ጥሩ ቦታ ያስቀምጥልን!

በአምስት አመት ያልቃል የተባለው አባይ ግድብ እዛው አይናችን እያየ ወደ ሰባት አመት አደገ። “እንዴ ገና ሰባት አመት ሙሉ ደሞዛችን ሊቆረጥ” ብሎ ማጉረምረም አይገባም መልሱ “ይቅርታ ሲያጣድፉን አንወድም ነው!”

ሶስት

የመዋጮው ነገር፤ “አባይን በራሳችን አቅም እንገድባለን!” ብለን ከህፃን እስከ አዋቂ ሁላችንም ፎክረናል። አንዳንዶቻችንም “ፎግረናል” በነገራችን ላይ በቴሌቪዥን እና በመስሪያ ቤታቸው ስብሰባዎች ላይ፤ “እኔ ለአባይ ዘራፍ እላለሁ!” ብለው ፊታቸውን አስመትተው በአለቆቻቸው ዘንድ ሞገስ ያገኙ በርካቶች እንደሆኑ ባለፉት ግዚያት አይተናል። እነዚህ ወዳጆቻችን በመስሪያ ቤታቸው ሰዎች ዘንድ “አስተኳሽ” የሚል የማዕረገት ስምም ተሰጥቷቸዋል።

እኔ የምለው ወዳጄ አንዳንዶች የሚሰጡትን አስተያየት ልብ ብላችሁልኛል? “አባይን በራሳችን አቅም ገድበን ከአምስት አመት በኋላ ድህነትን ማጥፋት እና ካደጉት ሀገሮች ተርታ መቀላቀል አለብን!” እያሉ ነው።

ቆይ ቆይ እዝች ጋ ትንሽ ፍሬን ያዝ እናድርግ…

አባይ በራሳችን አቅም በእኛው መዋጮ ለማለቅ ስንት አመት እንደሚፈጅበት እናስላ፤ ባለፈው አመት ሰባት ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። በመነሻው ሞራል እንቀጥላለን፤ “ምናባቱ የመጣው ይምጣ!” ብንል እንኳ፤ ሰማኒያ ቢሊዮን ለማግኘት… (ሰማኒያን ለሰባት ማካፈል ነው።) አስራ አንድ አመት ይፈጃል።

ታድያ “በአምስት እና በስድስት አመት ያልቃል” የሚሉን ወዳጆቻችን የሚያውቁት ሌላ ምስጢር ካለ ቢነግሩን ጥሩ ነው። የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። የምር ግን መንግስታችን ራሱ በሰባት አመትም ይሁን በስድስት አመት የሚያልቀው በምን ስሌት እንደሆነ፤ ድህነትንስ ሙልጭ አድርጎ የሚያጠፋው በምን መልኩ እንደሆነ የማስረዳት ኃላፊነት ያለበት አይመስልዎትም…?

አንድ ወዳጃችን አባይን ገድበን ድህነትን እናጠፋለን ተብሎ በቴሌቪዥን ሲነገር ሰምቶ ምን አለ መሰልዎ “እነዚህ ሰዎች ድህነት በኤሌክትሪክ ተንጨርጭሮ የሚጠፋ መሰላቸው እንዴ…?” ብሎ ጠየቀን። በዙሪያው ያለን ሰዎችም “ፖለቲካ አናወራም” ብለን ዝም ብንለው፤ “የኔ ጌታ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድህነት ፕላስቲክ ለበስ ነው። ኤሌክትሪክ አይዘውም!” አለና ከት ብሎ መሳቅ፣ ከዛም ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ።

የሆነ ሆኖ እያለቀስንም ሆነ እየሳቅን እናዋጣለን። “አናዋጣም” ብለን ከሚመጣው ጣጣ አዋጥተን የሚመጣውን ችጋር መቻል ይሻለናል።

አረስቼው ዋናው ከዚህ ከመዋጮ ጋር ተይዞ ልነገግርዎ የፈለግሁት፤ ልብ ብለው እንደሆነ መዋጮው መጀመሪያ በስጦታ ተብሎ ነበር ከዛ ደግሞ ወደ ቦንድ ግዢ ተለውጦላችኋል አታስቡ መንግስት ሰርቶ ይከፍላችኋል ትብሏል። በርግጥ ለርሱም እስካሁን ማረጋገጫ ያገኘ የለም። (ካለ እጁን ያውጣ!)

እንግዲህ አባይ ይገደባል በተባለ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ በርካታ ነገሮችን አይቷል። ጠዋት የተነገረለት ከሰአት ከበርጫ ሰዓት መልስ ይቀየራል። እስከ አሁን እንኳ ሶስት ዋና ዋና ለውጦቹን አየን? በአዲስ መስመር አንድ እንጨምር፤

አራት

አባይ ግድብ ሊጀመር ጠዋት አካባቢ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ኋይል ያመነጫል ተብሎ ነበር። ትንሽ ረፈድ ሲል በቃሚዎች ቋንቋ፤ “ኢጃባና” ከተቃመ በኋላ አባይ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት አመነጫለሁ ብሏል ተባለ።

ይሄ ነገር የደህናውን ግዜ የጉሊት ገበያ ያስታውሰኛል። በተለይ ክረምት አካባቢ የስሙኒ ተብሎ የሚታሰረው ጎመን በደንብ ከተከራከሩ ሌላ እሱኑ የሚያክል ይመረቅ ነበር። (በጥጋቡ ግዜ ነው) ታድያ አሁንም አባይ ጥሩ የጉሊት ነጋዴ ነው የመሰለኝ። አምስት ሺህ ነው የማመነጨው ብሎ ሲያበቃ “አረ ባክህ አወጥተን እኮ ነው ገንዘብ እንኳ የለንም እባክህን መርቅልን!” ብለው አስተዛዝነው ነግረውት ነው መሰለኝ፤ መረቅረቅ አድርጎ ስድስት ሺህ ገብቶልናል።

እኔ የምለው ግን “የሚያመነጨው ሃይል ስለጨመረልን “ቲፕ” እናድርገው” ተብሎ መዋጮው ላይ እንዳይጨመርብን አይሰጉም?

እናልዎ ወዳጄ አባይ ግድብ ከተጀመረ አንድ አመት ሞልቶታል። በአንድ አመት ውስጥ እኛም እርሱም ብዙ ነገር አሳልፈናል። እርሱም ከላይ እስከ አራት የገለፅናቸውን ለውጦች እና ከስር እስከ አርባ አራት ያልገለፅናቸው ድንገተኛ ለውጦች ተከናውነውበታል። (እንደውም በቅንፍ፤ ለውጪ ሃይሎች እና የሀገሪቱን መልካም ለማይሹ ሰዎች አይናገሩ እንጂ… ለሙያው ቅርበት ያላቸው ወዳጆቻችን እንደሚሉት ከሆነ፤ “አባይ ከስያሜው ጀምሮ ይሄን ሁሉ ለውጥ ያስተናገደበት ምክንያት ያለ ዕቅድ መሰራቱ ነው።”) ከቅንፍ ውጪ እኛን በእቅድ ኑሩ እያለ የሚመክረን መንግስት ራሱ ያለ ዕቅድ የሚሰራው የሚከተለውን ጦስ አያውቅምን? ብዬ እጠይቃለሁ።

የሆነው ሆኖ አባይ አንድ አመት ሞልቶታል። ልጅ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ድክ ድክ የሚልበት ግዜው ነበር። እርሱም ድክድክ እያለ እንደሆነ በቴሌቪዥን አይተናል! እኛም ለአባይ እናዋጣለን ብለን “በሞራል” ከተንቀሳቀስን አመት ሞላን። እኛም በዝች አንድ አመት ውስጥ ብዙ አሳልፈናል። ድጋሚ ኑሮ ውድነቱ ከፍቶ የዋጋ ተመኑም ቀርቶ መኖር ይሉት ጣጣ ብርክርክ አድርጎናል። እንዲህም ሆኖ ለቀጣይ ስንት አመት ለአባይ እናዋጣ ይሆን…? እስቲ እንበርታ… ባንበረታስ…? ብንበረታም እንበርታ!

በመጨረሻም

አማን ያሰንብተን!

About abetokichaw

ራሱን አቤ ቶኪቻው እያለ የሚጠራ አንድ ግለሰብ በአዲሳባ ከተማ ይኖር ነበረ። በአዲሳባ ከተማ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትን ያልተስተካከለ አስራር ሲያሽሟጥጥ መንግስት ተቀየመው። ምን መቀየም ብቻ… ከሀገር እንዲሰደድ ሁሉ አደረገው እንጂ! ይህ ግለሰብ… ከዚህ በፊት ሁለት ሽሙጣዊ መፅሐፍትን ያሳተመ ሲሆን “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” እና “ስላቆች” ይሰኛሉ። አሁንም ቢሆን የማይሆን ነገር ካየሁ ከማሽሟጠጥ አልመለስም የሚለው ይህ ስደተኛ… እነሆ በዚህ ብሎግ ላይ ደግሞ በሽሙጥ የአፃፃፍ ብልሃት ቢያንስ በሳምንት አንድ ግዜ ልከሰት ብሎ “ሀ” ብሏል።

4 responses »

 1. Eyobè Brehane says:

  ተግባር ተግባር ተግባር ለዘላለም ትኑር!ለእስክንድር ነጋ
  ይህንን የሀገር ጌጥ ወልደው የሰጡ እናት፣
  እኩል ይሆን እንዴ እንደ መለስ ወላጅ ምጡ የጠናባት፣
  ይህኛው ለማፍረስ ሲጥር መሰረቱ፣
  ያኛው ሊገነባ ከላይታች መውጣቱ፣
  የባሻ አስረስ ልጅ መሰረቱ ባንዳ፣
  አይግረምሽ ኢትዮጵያ ሀገሩን ቢከዳ።
  31/03/2012

 2. Messaye says:

  abei,
  poverty will be extended for two more years, OMG

 3. በለው! says:

  አዎን ..ብርር ..ክክ ርር ክክክ አልን እስቲ የአማርኛ ፎንት አዘጋጅልን እና እኛም እናዋጣ!
  ሰዎቹ ምን መፍጨርጨር ብቻ “ተፈነጫጨሩብን” የአባይ ግድብ መሠረቱ ሳይጣል በጭፋሮ ተደለደለ..ለመሆኑ ሰውዬው ባንዲራ ዘቀዘቁ ያልከው ሁሉ የግልብጥ ነው ። ድሮ “ላሟ” ይባል ነበር
  ዛሬ “ላሙ”ሆኗል፡ ደቀቁ ተፈጩ አላልኩም እና አሸባሪ ብለህ እንዳትጠቁምብኝ አደራ።የሚሊኒየም
  ግድብ እንዳይባል ወጪው ቢሊየን ነው በመቶ ዓመት ታሪክ ሚሊኒየም ሲከበር የከረመው በሒሳብ ት/ ክፍለ ጊዜ ፎርፌ ሲመቱ የኖሩ በኩረጃ ያለፉ በመሆናቸው ነው፡አባይን የደፈሩት ጠ/ሚ ዋኝተው ነው ?አዲስ ባሰሩት ድልድይ ላይ ቆመው ወደ ታች አይተውት? የግድቡ አሠራር የሚለው ሲወጠን ሁለት ዓመት ሲለፈፍ ሁለት ዓመት መሠረቱ ሊጣል ሦስት ዓመት የመጀመሪው ሰባት መቶ ኪ.ዋት በአምስት ዓመት ተገምግሞ ከአሥር ዓመት በሗላ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገር ዜጎች ሲመጡ ከጎናቸው ተሰልፈን ፎቶ እንነሳለን።አምስት ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ሲጠናቀቅ ግን እንደ አሁኑ ድህነት ሳይሆን የሚቀንሰው ድሆች እንዲቀነሱ ከግድቡ ሥር ሳይቀብሯቸው አይቀርም!
  የምድሩስ አሸባሪ ሆኗል የሰማዩ ጌታ የመኸሩንም የበልጉንም ዝናብ ከላይ ገደበው እሱስ የትኛው የሕዳሴው ችሎት ይከሰሥ ይሆን? አባይ አንድ ዓመት ካስጨፈረን መች አነሰው ዜማ ቅኝቱ ወጣ
  ቅኔውም ተዘረፈ ቃለ መሐላው ተለፈፈ እሱም ተገርሞ አልቆመ በመገረም አለፈ ..በቸር ይግጠመን

 4. tom says:

  hello Mr.Abe

  it is good to start this blog.but post donation like as well as sell PDF versition of your book in Amazone and reach to many readers man.be fast now.you have a potencial to write many online books.don’t be lazy.you can generate many.contact me for more.we can think it and make business too.

  thanks

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s